በሃሳብ ከመታገል ዉጪ ብሔራዊ ጥቅምንም ሆነ ሃገራዊ ልማቶችን መቃወም አግባብነት እንደሌለዉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፖርቲዎች ገለጹ

You are currently viewing በሃሳብ ከመታገል ዉጪ ብሔራዊ ጥቅምንም ሆነ ሃገራዊ ልማቶችን መቃወም አግባብነት እንደሌለዉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፖርቲዎች ገለጹ

AMN – ህዳር 04/2018 ዓ.ም

በሃሳብ ከመታገል ዉጪ ብሄራዊ ጥቅምንም ሆነ ሃገራዊ ልማቶችን መቃወምም ሆነ ማደናቀፍ አግባብነት እንደሌለዉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፖርቲዎች ገልጸዋል፡፡

አንዳንድ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፖርቲ አመራሮች ከኤ ኤም ኤን ፕላስ ጋር በነበራቸዉ ቆይታ፤ የትኛዉም የፖለቲካ ፖርቲ ሃገራዊ ጥቅምን ከማክበር ባለፈ ሃገራዊ ጥቅም እንዲከበር እና እንዲጠበቅ ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም አለማክበርም ሆነ አለማስከበር የዘመናዊ ፖለቲካ መገለጫ አይደለም ፤ ብሄራዊ ጥቅም ከየትኛዉም አጀንዳ ሊቀድም ይገባል ብለዋል፡፡

ሃገራዊ ልማቶችንና ለዉጦችን መቃወምም ሆነ ማደናቀፍ ከጤናማ ሃሳብ የሚመነጭ አይደለም ነዉ ያሉት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ፡፡

‎የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ተወካዩ አቶ ዑመር አብዱረህማን፤ የሚታዩ ዉስንነቶችን የአፈጻጸም ጉድለቶችን በማንሳት እንዲስተካከሉ በሃሳብ እንታገላለን እንጂ በደፈናዉ ሃገራዊ ልማቶችን አንቃወምም ፤ ይህም አግባብነት የለዉም ብለዋል፡፡

‎ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በግንባታ ላይ በነበረበት ወቅት አንዳንድ የተቃዉሞ ሃሳቦች ሲደመጡ እንደነበር የሚናገሩት የኢዜማ ፖርቲ ተወካዩ አቶ ታሪኩ ድንበሩ፤ ሃገራዊ ልማቶችንና ብሔራዊ ጥቅምን መቃወም ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፖርቲዎች የሚጠበቅ ተግባር አይደለም ብለዋል፡፡

‎የሃገሪቱን እድገት የሚያረጋግጡ ሃገራዊ ልማቶችን ማደናቀፍም ሆነ መቃወም ከኋላ ቀር የፖለቲካ ባህልና እሳቤ የሚመነጭ ጤናማ ያልሆነ ፖለቲካ ነዉ ያሉት አቶ ታሪኩ ድንበሩ፤ ሃገርን መቃወም አግባብነት የለዉም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

‎ከትዉልድ ፓርቲ ከኤ ኤም ኤን ፕላስ ጋር ቆይታ ያደረጉት አቶ ስለሺ ዳበሳ በበኩላቸዉ፤ አዲስ አበባ ከአሁን ቀደም ከጽዳትና ከልማት አንጻር ከፍተኛ ዉስንነቶች የነበሩባት መዲና መሆኗን በመግለጽ፤ በአሁኑ ወቅት ግን በኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች አዲስ አበባ አዲስ ገጽታ መጎናጸፏን ጠቁመዋል፡፡

አዲስ አበባ አሁን ላይ የሃገሪቱን ዜጎች ብቻ ሳይሆን የዉጭ ሃገር ቱሪስቶችን ጭምር መማረክ ችላለች፤ የተሰራዉ ስራም ሊበረታታ የሚገባዉ ነዉ ብለዋል፡፡

መንግስት የጀመረዉን የሰላም ጥሪ በማጠናከር እና የፖለቲካ ምህዳሩን የበለጠ በማስፋት ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ያልተቀላቀሉ ሃይሎች ወደ ሰላም እንዲመጡ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

በመሳሪያ አፈሙዝ ትርፍ ለሌለዉ ፖለቲካ ህዝቡን ማሸበርና ሰላም መንሳት፤ ሃገራዊ ልማቶችንም ማደናቀፍ ህዝብንም ሆነ ሃገርን ስለማይጠቅም ሁሉም ሃይሎች ለሃገራዊ ሰላምና ልማት ቅድሚያ ሊሰጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

‎በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review