ህፃን አግተው 1.7 ሚሊዮን ብር የተቀበሉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

You are currently viewing ህፃን አግተው 1.7 ሚሊዮን ብር የተቀበሉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

AMN ህዳር 4/2018

ህፃን አግተው 1.7 ሚሊዮን ብር የተቀበሉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የእገታ ወንጀሉ የተፈፀመው በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ስፍራው ማርያም ሰፈር ተብሎ ከሚጠራ አካባቢ ነው፡፡

የታገተው ህፃን ወላጆች የተከራዮቹን ማንነት ሳያረጋግጡ መኖሪያ ቤታቸውን ያከራያሉ፡፡ ቤቱን የተከራዩት ፊሊሞን አበራ፣ ሳምሶን ደፋሩ፣ እና አለልኝ ፍትህአለው የተባሉ ወንጀል ፈፃሚዎች በቤቱ በቆዩባቸው ሁለት ወራት ውስጥ የቤተሰቡን አጠቃላይ ሁኔታ ሲያጠኑ ቆይተው ጥቅምት 15 ቀን 2018 ዓ/ም የ8 ዓመቱን ህፃን ሚካኤል ግርማን አግተው ይሰወራሉ፡፡

ከእገታው በሗላ የህፃኑ ቤተሰቦችም መረጃውን በማህበራዊ ሚዲያ እንዳሰራጩ እና ከወንጀለኞቹ ጋር በመደራደር 1.7 ሚሊዮን ብር የከፈሉ ሲሆን አጋቾቹ ብሩን ተቀብለው ወደ ጎንደር መሄዳቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ መረጃ ይደርሰዋል፡፡

ወንጀል ፈጸሚዎቹ ህፃኑን አግተው የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 የመኖሪያ ቤት ተከራይተው አስቀምጠውት እንደነበርና ከእገታው በተቀበሉት ገንዘብ ወርቅ በመግዛትና የገዙትን ወርቅ ሸጠው ብሩን እንደተከፋፈሉ ፖሊስ ከሚመለከታቸው አካላት በመቀናጀት ባደረገው ክትትል ተጨማሪ መረጃ ያገኛል፡፡

አጋቾቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል ፖሊስ ክትትሉ አጠናክሮ በቀጠለበት ሁኔታ ወንጀል ፈፃሚዎቹ አይደረስብንም በማለት ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውን በመታወቁ ህዳር 3 ቀን 2018 ዓ/ም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና የወንጀሉ አፈፃፀምን መርተው ማሳየታቸውን እንዲሁም የወንጀሉ ፍሬ የሆኑ ኢግዚቢቶችን እና 1ሚሊዮን 4መቶ ሺህ ብር መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አስታውቋል፡፡

የህፃኑ ወላጅ አባት አቶ ግርማ ተስፋዬ በሰጡት አስተያየት የተከራዮችን ማንነት ሳያረጋግጡ ቤት ማከራዬታቸው በተለይም ወንጀሉ ከተፈፀመ በኋላ ጉዳዩ ለፖሊስ ቢያሳውቁም ምናልባት በልጄ ላይ ጉዳት ሊደርስ ይችላል በሚል ስጋት ከፖሊስ ጋር የነበራቸውን የመረጃ ልውውጥ በማቆም ይልቁንም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ስለ ህፃኑ መጥፋት ቪዲዬ መለቀቁ አጋቾቹ ህፃኑ በዋትስ አፕ ያለበትን አደገኛ ሁኔታ ለቤተሰብ እየላኩና ቤተሰቡን በማስፈራራት የሚፈልጉት ገንዘብ እንዲላክላቸው ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረላቸው ገልፀው ሌሎች አጭበርባሪዎችም ህፃኑ እነሱ ጋር እንዳለ በማስመሰል ገንዘብ እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ እንደነበር ተናግረዋል።

አያይዘውም ከእሳቸው ስህተት ሌሎች ተምረው ሊጠነቀቁ እንደሚጋባ አስገንዝበው የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ወንጀል ፈፃሚዎቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሰራው ስራ አድንቀው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review