ከአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት የመካኒሳ ቅርጫፍ ፅ/ቤት ውስጥ 2.5 ሚሊየን በላይ ብር የዘረፉ ወንጀል ፈፃሚዎችን በቁጥጥር አውሎ ምርመራ ማጣራቱን የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አሰታወቀ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ወንጀሉን የፈፀሙት ጥቅምት 6 ቀን 2018 ዓ.ም ከሌሊቱ 7 ሰባት ሰዓት ገደማ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት የመካኒሳ ቅርጫፍ ፅ/ቤት ውስጥ ነው፡፡
ቅዱስ ሀይለየሱስ ፣ ዮናስ ግርማይ ፣ ኤርምያስ ሰንበት እና ኪሮስ ግርማይ የተባሉ ወንጀል ፈፃሚዎች ከድርጅቱ የጥበቃ ሰራተኞች ጋር ተመሳጥረው የድርጅቱን ካዝና በፌሮ ብረትና በሌሎች መርጃ መሳሪያ በመፈልቀቅ 2ሚሊየን 597ሺ 635ብር በመዝረፍ በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 2C አዲስ አበባ 71417 ቪትዝ እና ኮድ 2A አዲስ አበባ 79207 ሚኒባስ ተሽከርካሪዎች በማዳበሪያ ጭነው ይሰወራሉ።

የወንጀሉ መፈፀም መረጃ የደረሰው የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የክትትል እና ኦፕሬሽን ክፍሉ ከወንጀል ምርመራ ክፍሉ ጋር በመቀናጀት ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ክትትል ወንጀሉ በተፈጸመ በሁለተኛው ቀን ወንጀል ፈፃሚዎችን እና ሁለት ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር በማዋል 569ሺ,595 ብር ማስመለሱን አስታውቋል፡፡
ፖሊስ አስፈላጊውን ማስረጃ በማሰባሰብ በወንጀል ፈፃሚዎቹ ላይ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ንፋስ ስልክ ላፍቶ ፈጣን ችሎት/RTD/ ምድብ ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በመታየት ላይ መሆኑን መምሪያው ጨምሮ ገልጿል፡፡
በዚህ የወንጀል ድርጊት ላይ የተሳተፉ የጥበቃ ሰራተኞች የጠበቃ አገልግሎት በሚሰጥ ተቋም አማካኝነት የተቀጠሩ እንደሆነ ፖሊስ አስታውቆ ኤጀንሲዎች የሚቀጠሯቸው ሰራተኞች በሚፈፅሙት ወንጀል የፍትሀብሔርና የወንጀል ተጠያቂነት ከማስከተሉም ባሻገር ፍቃድ ሠጪው አካል ፍቃዳቸውን እስከ መንጠቅ የሚያደርስ ጠንካራ ዕርምጃ የሚያስከትል ጥፋት መሆኑን በመገንዘብ ሰራተኞችን ሲቀጥሩ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ፖሊስ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አሳስቧል፡፡