ተቋማት ተቀናጅተው መስራታቸው ዜጎች የሚያነሱትን የአገልግሎትና የልማት ጥያቄ በተናበበ አቅም ለመመለስ አቅም ይሆናል

You are currently viewing ተቋማት ተቀናጅተው መስራታቸው ዜጎች የሚያነሱትን የአገልግሎትና የልማት ጥያቄ በተናበበ አቅም ለመመለስ አቅም ይሆናል

AMN – ህዳር 04/2018 ዓ.ም

ተቋማት ተቀናጅተው መስራታቸው ዜጎች የሚያነሱትን የአገልግሎትና የልማት ጥያቄ በተናበበ አቅም ለመመለስ አቅም እንደሚሆን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ተናገሩ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና ለማቀላጠፍ እንዲሁም የልማት ስራዎችን ተደራሽ ለማድረግ ተቋማት ተቀናጅተው የሚሰሩበትን አደረጃጀት በመፍጠር እየተሰራ ይገኛል፡፡

በትራንስፖርት እና በማዘጋጃ ቤታዊ ዘርፍ አገልግሎት የሚሰጡ 17 ተቋማትም በክላስተር ተደራጅተው በጋራ መስራት የሚያስቻላቸውን ስምምነት አድርገዋል፡፡

ተቋማቱ የሚያከናውኗቸው ተግባራት ዘመናዊ የትራንስፖርት መሰረተ ልማትን መዘርጋት፣ የትራፊክ ድንብ ክትትል እና ቁጥጥርን ማሻሻል፣ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝን ማዘመንን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የሚሰሩ ናቸው፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አሰኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ፤ ቅንጅቱ አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን እንደሚያስችል ገልጸው፤ የተቋማቱ በትብብር መስራት የከተማዋን አቅም ለማቀናጀትና የተቋም ግንባታን ለማጠናከርም አቅም የሚፈጥር እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የተቋማቱ ቅንጅት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ ተጠያቂነትን ለማስፈን እንደሚያስችልም ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ገልጸዋል፡፡

ተቋማቱ በክላስተር መደራጀታቸው የከተማዋን ነዋሪዎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን የገለጹት የተቋማቱ አመራሮችም ለተግባራዊነቱ የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

በቴዎድሮስ ይሳ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review