በመዲናዋ የሚከናወን ህገ-ወጥ እርድ ለህብረተሰቡ ከፍተኛ የጤና ስጋት እንዳይሆን በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ገለፀ።
ባለሥልጣኑ ከቄራዎች ድርጅት እና ከአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ኮሚሽን ጋር በህገ-ወጥ እንስሳት እርድ እና በህገ-ወጥ የስጋና የእንስሳት ዝውውር ዙሪያ የውይይትና የግንዛቤ ማስጨበጥ መድረክ በአድዋ ድል መታሰቢያ መሰብሰቢያ አዳራሽ እያካሄደ ይገኛል ።
የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ እንደተናገሩት፤ ጤንነቱ የተጠበቀ እርድ ማከናወን ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል።
ህገወጥ እርድ ከሚያመጣው የጤና ችግር በተጨማሪ የከተማዋን ንፅህና በከፍተኛ ደረጃ የሚበክል በመሆኑ ይህንን ለመከላከል ግንዛቤ መፍጠርና ተጠያቂነትን ማስፈን ላይ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በመዲናዋ የሚከናወን ህገወጥ እርድ ለህብረተሰቡ ከፍተኛ የጤና ስጋት እንዳይሆን ተቋማቱ በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተመላክቷል።
ህገ ወጥ እርዱ ከጤና ስጋትነቱ በተጨማሪ ከተማ አስተዳደሩ ማግኘት ያለበትን ገቢ እያሳጣው መሆኑም በመድረኩ ተገልጿል።
በአዲስ አበባ እየተባባሰ የመጣውን ህገወጥ እርድ እና የእንስሳት ዝውውርን መከላከል የሚቻልባቸው ጉዳዮች አቅጣጫም ተመላክቷል።
በመሀመድኑር ዓሊ