ለቀሪ የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች መሳካት የፖለቲካ ፓርቲዎች ንቁ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መሥፍን አርአያ (ፕ/ር) ገለፁ፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የላቀ ተሳትፎ ለሀገራዊ ምክክር ውጤታማነት” በሚል መሪ ሃሳብ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በአዳማ ከተማ እየተወያየ ነው፡፡
ዋና ኮሚሽነር መሥፍን አርአያ (ፕ/ር) በዚህ መድረክ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኮሚሽኑ ወደ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ምዕራፍ ለመሸጋገር የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ኮሚሽኑ ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ሂደት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በቅርበት ሲሠራ መቆየቱን ያስታወሱት ዋና ኮሚሽነሩ፤ በሀገራችን እየተንቀሳቀሱ ካሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መከካል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት በምክክር ሂደቱ እየተሳተፉ ነው ማለታቸው ተገልጿል፡፡

በምክክር ሂደት በተለያዩ ምክንያቶች ያልተሳተፉ የፖለቲካ ኃይሎችን ለማሳተፍ ኮሚሽኑ በራሱ መንገድ ጥረት እያደረገ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
በቀጣይ ጊዜያት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከናወኑትን ሀገራዊ ምርጫ እና የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ አጣጥሞ መጓዝ ያስፈልጋል ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ይህን ለማከናወን የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሀሳብ ማዳመጥ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
ቀሪ የምክክር ምዕራፎች በስኬት እንዲጠናቀቁ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሚናውን እንዲወጣም ዋና ኮሚሽነር መሥፍን አርአያ (ፕ/ር) ጥሪ ማቅረባቸው ተገልጿል፡፡
ስለ ትግራይ ክልል የምክክር ተሳትፎ የተናገሩት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ያሉ ችግሮች ተፈተው ወይም በችግሮቹ መካከል በማለፍ የትግራይ ክልል እንደሌሎች ክልሎች በምክክር ሂደቱ መሳተፉ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የኮሚሽኑ እምነት መሆኑን አፅንኦት መስጠታቸውም ነው የተገለፀው፡፡