የመዲናዋን እድገት ይበልጥ ለማፋጠን ከአስፈጻሚ ተቋማት ጋር ተባብሮ መስራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ ተናገሩ ፡፡
ዋና ስራ አስፈጻሚው ይህን ያሉት ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ጋር በጋራ ለመስራት በተደረገው የስምምነት መርሀ ግብር ላይ ነው ፡፡
በመርሀ ግብሩ ላይ አቶ ካሳሁን እንደተናገሩት፣ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርከ በዋነኝነት የከተማዋን የልማት ስራዎች ተደራሽ ለማድረግ ራሱን የትውልድ ድምጽ በማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በዚህም በአሁኑ ጊዜ በ5 የሀገር ውስጥ እና በሁለት ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች መረጃ እያሰራጨ መሆኑን ነው አቶ ካሳሁን የተናገሩት፡፡
በተለይም በስሩ በሚገኙ የሬዲዮ ፣ ቴሌቪዥን እና ዲጂታል ሚዲየሞች የገበያ ማዕከላትን መረጃ ለሸማቾች በማሳወቅ ሕገ ወጥ ንግድ ወደ ስርዓት እንዲገባ በማድረግ የንግዱን ዘርፍ እየደገፈ ይገኛል ብለዋል፡፡
የንግድ ቢሮ የተሰጠውን ኃለፊነት እንዳይወጣ የሚያደርጉ ብልሹ አሰራሮችን በማጋለጥ በሁሉም፣ በተቀረፁ ፎርማቶች በተለይም 24 /7 በተሰኘ አዲስ ፎርማት አሁናዊ መረጃዎችን እያደረሰ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡
የከተማዋን ሁለተናዊ ዕድገት ከፍ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ሚዲያው ከሁሉም አስፈፃሚ አካላት ጋር በመቀናጀት የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል ዋና ስራ አስፈጻሚው ፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ ከሚዲያው ጋር እስካሁን አበረታች ስራዎችን እያከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው ፣የፊርማ ስነ ስርዓቱ ሁለቱ ተቋማት የመዲናዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለሚያደርጉት ትብብር አስፈላጊ ስለመሆኑንም አንስተዋል፡፡
በጽዮን ማሞ