የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ “የሰላም እሴትና መቻቻል ለሀገርና ለትውልድ ግንባታ ያለው ፋይዳ” በሚል መሪ ሀሳብ የማጠቃለያ ኮንፈረንስ አካሂዷል፡፡
በማጠቃለያ ፕሮግራሙ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ብርሃኑ ረታ፣ በህብረተሰቡ ውስጥ ጤናማ መስተጋብር እንዲኖርና የሰላም እሴት የበለጠ እንዲገነባ የግጭት መንስኤዎችን ቅድሞ ማድረቅ ይገባል ብለዋል፡፡
ምክትል ቢሮ ሀላፊው አክለውም፣ የሀይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ተፅእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች በመዲናችን ሰላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት የውይይቱ ተሳታፊ መላከ ሀይል አባ ሀይለገብርኤል በሰጡት አስተያየት፣ በተለያዩ እምነቶች ውስጥ የሚገኙ ምዕመናን ስለ ሰላም የሀይማኖት አባቶች የሚሰጧቸውን ምክሮችና ትምህርቶች በአግባቡ በመረዳት በተግባር ላይ ማዋል ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሼህ መሀመድ ሼሪፍ በበኩላቸው፣ አዲስ አበባ ሰላሟ የተረጋገጠች ከተማ አንድትሆን ሳንታክት ስለ ሰላም ማስተማር ይገባናል ብለዋል፡፡
የቱለማ ፊንፊኔ አባ ገዳ ሰብሳቢ አባ ገዳ ሰቦቃ ለታ በበኩላቸው፣ በሰላምና በፍቅር በአንድነት የኖረውን ህዝብ በቀጣይም አብሮ እንዲኖር ለማድረግ ግጭቶች እንዳይከሰቱ መምከርና ማስተማር እንደሚገባ ገልጸው፣ ግጭቶች ሲከሰቱ ደግሞ ማስታረቅና ማግባባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ሰላም በግለሰቦች ደረጃ፣ በህዝቦች መካከል እና በመንግስትና በህዝብ መካከል እንዲሰፍን መደማመጥ አለብን ያሉት ደግሞ ሌላኛው የውይይቱ ተሳታፊ ፓስተር ቤኩማ ሱራ ናቸው፡፡
አርቲስት ሙሉነህ ዘለቀ በበኩላቸው፣ በመዲናችን ሰላም እንዲሰፍን ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የእድር ዳኞች፣ አርቲስቶችና የመንግስት ሚዲያዎችና ማህበራዊ አንቂዎች የየራሳቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡
በአስማረ መኮንን