“ኮፕ 32ን ያካተተ ጠንካራ እና ትርጉም ያለው ውጤት ለማምጣት ቁርጠኛ ነች”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
ኮፕ (Conference of the parties-COP) በየዓመቱ የሚካሄድ እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚደረግ ትልቅ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ነው። ይህ ጉባኤ የሚካሄደው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት (United Nations Framework Convention on Climate Change- UNFCCC) ስር ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያም ከሁለት ዓመት በኋላ ይህን ጉባኤ ለማካሄድ የተመረጠችው ከሰሞኑ ብራዚል ውስጥ በተካሄደው የዘንድሮው ስብሰባ ላይ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አፍሪካ በብራዚል ቤሌም በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት የ2025 የአየር ንብረት ጉባዔ (ኮፕ 30) ላይ በአንድነት ድምጿን አሰምታለች። በዓለም ደረጃም ተደምጣለች ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2027 ኮፕ 32ን በአዲስ አበባ ለማስተናገድ ያቀረበችውን ጥያቄ የአፍሪካ ቡድን ተደራዳሪዎች በሙሉ ድምፅ በማፅደቃቸው ልባዊ ምስጋናዋን ታቀርባለች ሲሉም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት በሰው ልጅ ላይ ከሚጋረጡ ፈተናዎች አንዱ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቅረፍ የጋራ ጥረት የሚጠይቀውን ጉባኤ እንድንመራ ለተሰጠን እድል እናመሰግናለን ብለዋል።
ይህ ዕውቅና ዓለም በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ርምጃ መሪነት እና ዋና ዋና ዓለም አቀፍ ዝግጅቶችን የማስተናገድ አቅም ላይ እምነት እንዳለው ያሳያል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የጋራ ዕርምጃዎችን የሚያራምደውን ኮፕ 32ን ያካተተ ጠንካራ እና ትርጉም ያለው ውጤት ለማምጣት ቁርጠኛ ነች” ሲሉ አስታውቀዋል።
እ.ኤ.አ. በ2027 የሚደረገውን ኮፕ 32 ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ የተመረጠችው ናይጄሪያን በመብለጥ ነው። በጉባኤው የዓለም አገራት እና ሌሎችም በሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የሚካፈሉ ሲሆን፣ ወሳኝ ድርድሮች እና ስምምነቶችም ይደረጉበታል። ለመሆኑ ኢትዮጵያ ለዚህ ጉባኤ የተመረጠችበት ምክንያት ምንድን ነው? ጉባኤው በአዲስ አበባ መካሄዱ ምን እንደምታ እና ጥቅም ይኖረዋል?

ረዳት ፕሮፌሰር ደረጄ በቀለ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ ሰፊ የተፈጥሮ ጥበቃ ስራዎችን የምታከናውን ሀገር ናት፡፡ በአረንጓዴ አሻራና በደን ልማት ለብዙ ሀገራት ምሳሌ መሆንም ችላለች፡፡
ስለዚህ ኮፕ 32 አዘጋጅ ሆና እንድትመረጥ በማድረጉ ረገድ ባለፉት አመታት የተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሮች ከፍተኛ አስተዋጽ አላቸው፡፡ ምክንያቱም አንድ ሀገር የኮፕን ጉባኤ ለማስተናገድ ከመመረጡ በፊት በሀገርና አህጉር ደረጃ ያለው ሚናና የሰራው ስራ ከግምት ይገባል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ጥበቃ የምትታወቅና በካይ ጋዝ እንዲቀንስ በአለም የአፍሪካን ድምጽ የምታሰማ ሀገር መሆኗ ከሁለት አመት በኋላ የሚካሄደውን ትልቅ ጉባኤ እንድታስተናገድ ለመመረጥ ረድቷታል ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ እንደ የአረንጓዴ አሻራ (Green Legacy Initiative) ያለ ትልቅ እና ስኬታማ የአካባቢ ጥበቃ ስራን በማካሄድ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ያላትን ቁርጠኝነት አሳይታለች። እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሉ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ላይ ያላት ንፁህ የኃይል ፍላጎትን የሚያሳዩ ፕሮጀክቶች ለጉባኤው አዘጋጅነት በሙሉ ስምምነት እንድትመረጥ አወንታዊ ተፅዕኖ አሳድረዋል ማለት ይቻላል።
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ስራ አስፈጻሚና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ ጸሃፊ አቶ ፋኖሴ መኮንንም በረዳት ፕሮፌሰር ደረጄ ሃሳብ ይስማማሉ፡፡
አቶ ፋኖሴ ኢትዮጵያ ሰፊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርና የተፈጥሮ ጥበቃ ስራን እያከናወነች ነው፡፡ ይህም ስራን ጨምሮ የኢኮኖሚ እድልን ፈጥሯል፡፡ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት አስገኝቷል። ይህ ስራ ኢትዮጵያ ለኮፕ32 ጉባኤ አዘጋጅነት እንድትመረጥ አድርጓል ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ በተለይም የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤን (Africa Climate Summit) በማዘጋጀት ያገኘችው ልምድ እና የመዲናዋ የመሰብሰቢያ ቦታዎችና የሆቴል አቅም እያደገ መምጣትም ለጉባኤ አዘጋጅነት እንድትመረጥ የረዳት ሌላኛው ጉዳይ ነው፡፡
አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት (AU) እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (UN) የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (UNECA) መቀመጫ በመሆኗ ምክንያት፣ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን እና ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስብሰባዎችን የማስተናገድ ረጅም እና የተረጋገጠ ልምድ አላት። ይህም ለኮፕ32 (የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ) አስተናጋጅነት እንድትመረጥ ትልቅ አበርክቶ አለው፡፡
የአዲስ አበባ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ማዕከልነት፣ ዓለም አቀፍ ተሳታፊዎችን በብቃት የማስተናገድ፣ የሎጂስቲክስና የፀጥታ አቅምዋን ያሳያል። በቅርቡ በሀገራችን በስኬት የተካሄደው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን ለዚህ እንደ ማስረጃ መጥቀስ ይቻላል፡፡

ጉባኤው በአዲስ አበባ መዘጋጀቱ አንድምታውና ጠቀሜታ እጅግ በርካታ ነው፡፡ የኮፕ ጉባኤ አስተናጋጅ ሀገር በስብሰባው የፕሬዝዳንትነት ሚና አለው። የጉባኤውን ግቦች መቅረጽ ይችላል፡፡ የራሱን የአየር ንብረት ለውጥን የተመለከቱ ስራዎችን የማስተዋወቅ እድልና መብትም አላቸው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ በጉባኤው ወቅት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ጨምሮ ለሌሎች የተፈጥሮ ጥበቃ ስራዎችንና አየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እየሰራች ያለውን ስራ ለዓለም ማስተዋወቅ ትችላለች። በጉባኤው በርካታ የሀገራት መሪዎች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የሚገኙ በመሆኑ ለኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል፡፡
ስለዚህ በርካታ የዓለም መሪዎች፣ ሳይንቲስቶች እና ባለድርሻ አካላት ወደ ሀገሪቱ ሲመጡ፣ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ልምድ የመቅሰም እና የራሷን የልማት ፕሮጀክቶች (ለምሳሌ አረንጓዴ አሻራ) ስራዎችን የማሳየትና የማስተዋወቅ፣ የቱሪስት መዳረሻዎችን የማስጎብኘት ዕድል ታገኛለች።
ረዳት ፕሮፈሰር ደረጄ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ስታራምደው የነበረውን የአየር ንብረት ለውጥ አቋም በጉባኤው ለማንጸባረቅና በእድገት ላይ የሚገኙ ሀገራትን ድምጽ ለማሰማት እድል አላት። ምክንያቱም የአደጉ ሀገሮች በካይ ጋዝን ለመቀነስ የሚስችሉ አማራጮችን ለማድረግ ቃል ቢገቡም ወደ ተግባር ለመለወጥ ግን ቁርጠኝነት ይጎድላቸዋል፡፡
ስለዚህ ኢትዮጵያ እንደ አዘጋጅ ሀገር በጉባኤው ላይ የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ በሚደረጉ ድርድሮች ወቅት የሚከሰቱ አለመግባባቶችን የመሸምገል እና መፍትሄ የማስቀመጥ ስልጣን ያላት በመሆኑ ጉባኤውን ማስተናገዷ እንድምታውና ጥቅሙ ከፍተኛ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ጉባኤውን ማስተናገዷ የአፍሪካን አቋም እና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች እንድታቀርብ ያስችላል፡፡ በአየር ንብረት ለውጥ ድርድር በግንባር ቀደምትነት እንድትሳተፍ ትልቅ እድል ይሰጣል። የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ስጋት እና ፍትሐዊ የፋይናንስ ድጋፍ ጥያቄዎች ላይ ያላትን ተጽዕኖና የመደራደር አቅም ይጨምራል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር ትምህርት ክፍል ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር ደረጄ በቀለ ጉባኤው ከሚሰጠው ጥቅም አንዱ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ እየሰራች ያለችውን ስራ በሚገባ ለማስተዋወቅ እድል የሚፈጥር መሆኑ ነው፡፡ የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ ከዚህ በፊት የተደረጉ አለም አቀፍ ስምምነቶችና ፖሊሲዎች ወደ ትግበራ እንዲመጡ ግፊት ማሳደር ትችላለች ይላሉ፡፡
በአጠቃላይ ለጉባኤው አዘጋጅነት መመረጥ ለኢትዮጵያ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ክብርና የዲፕሎማሲ አቅም ያጠናክራል። እንዲሁም ኢትዮጵያ በአፍሪካ የአየር ንብረት ጉዳዮች ላይ ያላትን መሪነት ያጎላል። በተለይ በቅርቡ በአዲስ አበባ የተካሄደው 2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ባስገኘው ውጤት መሠረት፣ የአፍሪካን የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄዎች ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ ለማምጣት ያስችላታል።
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ስራ አስፈጻሚና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ ጸሃፊ አቶ ፋኖሴ እንደሚሉት፣ አትዮጵያ ለኮፕ32 አዘጋጅነት መመረጧ ትልቅ እድልና ተስፋ ነው፡፡ ይህ ጉባኤ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅሙ ከፍተኛ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአለም መድረክ ያላትን ተሰሚነት ከፍ ያደርጋል፡፡ ለጉባኤው እንግዶች ሲመጡ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ከፍ ይላል። የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለዓለም ለማሳየት ይረዳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በአዲስ አበባ የተካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ የፈጠረውን መነቃቃት መሰረት በማድረግ አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ የመፍትሔ አህጉር ሆና እንድትቀጥል ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናዋን አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉ አረጋግጠዋል።
በጊዜው አማረ