“ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ መንገድ ነው”
የህግ ባለሙያው አቶ ኪያ ፀጋዬ
ኢትዮጵያ ለዘመናት የራሷ የሆነ የባህር በር ነበራት፡፡ ይህም ከዓለም ጋር በተሻለ የመገናኘት፣ የመነገድ፣ የማደግ… እንቅስቃሴዋ ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማድረጉን ሰነዶችና የዘርፉ ምሁራን የሚያብራሩት ሃቅ ነው፡፡ የባህር በሯን ካጣችበት ከ1983 ዓ.ም ወዲህ እያሳደረ እና በቀጣይ ሊያሳድር የሚችለውን ተጽዕኖ ከግምት በማስገባት ጉዳዩ መልስ እንዲያገኝ ማድረግ ውዴታ ሳይሆን ግዴታ እየሆነ መጥቷል፡፡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሁለት ዓመት በፊት በይፋ ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት እንዳለበት ካነሱ ወዲህ ጉዳዩ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል፡፡
አቶ ኪያ ፀጋዬ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በህግ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በጣሊያን ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቱሪን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ህግ ሰርተዋል፡፡ ላለፉት 14 ዓመታትም በህግ ዙሪያ ጥናትና ምርምር በማድረግ፣ ስልጠና፣ የማማከርና የጥብቅና አገልግሎት በመስጠት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይም ሀሳብና አስተያየት በመስጠት ይታወቃሉ፡፡ ከእሳቸው ጋር የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ አስፈላጊነት፣ የባህር በር ያጣችበት መንገድና ከዓለም አቀፍ ህግ አንጻር እንዴት እንደሚታይ ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል፤ መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ልሳን፡- የባህር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ ያለውን አስፈላጊነት እንዴት ይገልፁታል?
አቶ ኪያ፡- ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችበት መንገድ በጣም ያስቆጫል፤ ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን ለፍትህ የቆመ ማንኛውም ሰው ይህንን ይጋራዋል። በዚህ ምክንያትም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባታል። እንደአለመታደል በተለይ ከ1980ዎቹ ጀምሮ የመጣው ትውልድ በልዩ ሁኔታ በራስ ጥረትና ንባብ ከተረዳው ውጪ አብዛኛው ‘ወደብ’፣ ‘የባህር በር’፣ ‘የባህር ሀይል’ እንዲሁም ባህር ላይ ስላለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ግንዛቤ የለውም፤ እንዲያውቅም አልተደረገም፡፡ የወደብ አልባነት ትርክት ሰለባ ነበር፡፡
የባህር በር ጥቅም ተቆጥሮ አያልቅም፡፡ በዋናነት ከውጪው ዓለም ጋር የሚያገናኝ መውጫ በር ነው፡፡ ቤት ሰርተህ መውጫ በር ከሌለው ወይም መግቢያህ በሰው ቤት ወይም በሰው አጥር ውስጥ ከሆነ፤ ያ የሚያሳልፈው ሰው የሆነ ቀን ደስ ካላልከው “የምታልፍበትን በር ዘግቼዋለሁ” ሊል ይችላል፡፡ ከቤትህ ለመውጣት የግለሰቡ መልካም ፈቃድና ችሮታ የግድ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያም ትልቅ ሀገር ሆና፣ ትልቅ የህዝብ ቁጥር ይዛ፤ በታሪክም ከአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የባህር ጠረፍ የነበራት ሆና ሳለ፤ ከውስጥና ከውጭ በተደረገ ጫናና ሸፍጥ የባህር በር አጥታለች፡፡ ይህ ያስከተለው ችግር ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ በኢኮኖሚው ረገድ ብናይ ለወጪና ገቢ ንግድ መውጫና መግቢያ ጂቡቲ ላይ ጥገኛ እንድንሆን አድርጎናል፡፡ ከ90 በመቶ በላይ የወጪና ገቢ ንግዳችን በአንድ ሀገር ላይ የተንጠለጠለ ሆኗል፡፡
በዓመት ለወደብ ኪራይ 2 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንከፍላለን፡፡ እንደ ቡና፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶችን እና መሰል ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ለወደብ ኪራይ ክፍያ ይውላል፡፡ አንድ ሀገር ላይ ብቻ ጥገኛ በመሆናችንም፤ ከዚህ ቀደም እናገኛቸው የነበሩ ምቹ የወደብ ታሪፍ ህጎችና ጥቅሞች በየጊዜው እየጠበቁ መጥተዋል። ይህም የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን በአግባቡ ወደ ውጪ በመላክ፣ ከሀብቶቹ ማግኘት ያለብንን ዋጋ እንዳናገኝ አድርጎናል፡፡

ባህር የዓለም ህዝብ የተፈጥሮ ሀብት ነው፡፡ ይህንን ሀብት ለመጓጓዣነትና ለተለያየ አገልግሎት የመጠቀም መብት ነው፡፡ የባህር በር የሌለን በመሆኑ ግን ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም፡፡ ወደብ ትልቅ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር ነው፤ ለሚሊዮኖችም የስራ ዕድል ይፈጥራል፡፡
ሌላው የራሳችን የባህር በር የሌለን በመሆኑ ከደህንነት አኳያ የእኛ የምንለው ምስጢር ብዙም እንዳይኖረን አድርጓል፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዱ የምናስገባው እቃ ተፈትሾ ነው የሚገባው፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ በጦር መርከብ መሳሪያ ብታስገባ፤ ጠላት የሆነ ሀገር ጂቡቲ ላይ ቁጭ ብሎ የምታስገባው መሳሪያ ምን እንደሆነ ይቆጥራል፡፡ አንዳንድ በምስጢር መያዝ ያለባቸው እቃዎች ተጋላጭ በመሆናቸው ለደህንነት ስጋት ያጋልጠናል፡፡
ዛሬ ያለው ትውልድና አመራር ይህንን አንገብጋቢ ጉዳይ በማንሳቱ ሊመሰገን ይገባል፡፡ የባህር በር ለኢትዮጵያ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካና አፍሪካ ቀንድ ቀጣና ትልቅ ሀገር ናት፡፡ ከአላት የህዝብ ቁጥር፣ የተፈጥሮ ሀብትና ኢኮኖሚ አኳያ ከአሁን በኋላ ያለባህር በር መቀጠል ከባድ ነው። አንድ መንግስት ሲፈልግ የሚዘጋብን ወይም የሚከፍትልን ሳይሆን እኛ የምንቆጣጠረው፣ ዓለም አቀፍ ህግን በተከተለና በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ በመመስረት የባህር በር ያስፈልገናል፡፡
የባህር በር የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት መቀጠልና አለመቀጠል ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው፡፡ ዛሬ ጂቡቲ ላይ በርካታ ሀያላን ሀገራት የጦር ሰፈሮችን መስርተዋል። ቅኝ ገዥ ከነበረችው ፈረንሳይ ጀምሮ አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ቻይና፣ ጃፓን፣ ጣሊያንና ሌሎች ሀገራት የጦር ሰፈር አላቸው፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ በአካባቢው ግጭት ቢፈጠር፤ 90 በመቶ የወጪ ገቢ ንግድ በጂቡቲ ላይ በተንጠለጠለበት ሁኔታ፣ በአንድ ቀን መግባት ያለበት ነዳጅ ለአንድ ሳምንት ቢስተጓጎል የሀገሪቱ እስትንፋስ ቆመ ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት በቀጥታ ያመረትነውን ቡና የምንሸጥበት መንገድ የለም ማለት ነው፡፡ ቀይ ባህር የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ የሚወስን፤ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነው፡፡ ከደህንነት፣ ፀጥታ፣ ንግድ፣ ቱሪዝምና ጂኦፖለቲክስ አኳያ ወሳኝ በመሆኑ የባህር በር የማግኘት ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ በትኩረት መሰራት ይኖርበታል፡፡
አዲስ ልሳን፡- ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄዋ በምን መንገድ ምላሽ ሊያገኝ ይችላል?
አቶ ኪያ፡- አሁን የባህር በሩን ጥያቄ አንሻፍፈው፣ ለፖለቲካ ፍጆታ ለማዋል የሚዳዳቸው አሉ፡፡ መንግስትም በተደጋጋሚ እንዳሳወቀው፤ እኔም በግሌ እንደማምነው የባህር በር የማግኘት ጥያቄያችን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ምላሽ ማግኘት ይችላል፡፡ መነጋገር ከተቻለ ለጎረቤት ሀገራት መስጠት የምንችለው የተፈጥሮ ሀብት ብዙ ነው። ለምሳሌ፡- በኤርትራ ከአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው የባህር ጠረፍ ይገኛል፡፡ እኛ ካለን ሀይል 500 ሜጋ ዋት ሰጥተን፤ ቅንነት ካለ 20 ኪሎ ሜትር ወደ ባህር መውጫ በር ቢሰጡን ሁላችንም ተጠቃሚ እንሆናለን፡፡ በሰጥቶ መቀበል፣ መሬት ወይም ሌላ ሀብት በመለዋወጥ የባህር በር ያገኙ ሀገራትም አሉ፡፡ በቅን ልቦና እና በትብብር መንፈስ ለሚረዳ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ሸፍጥ የለበትም፡፡
ጎረቤት ሀገራት የኢትዮጵያ ጥያቄ ሰላማዊ መሆኑን በቅን ልቦናና በትብብር መንፈስ መረዳት አለባቸው፡፡ በቀዝቃዛው ጦርነት የነበረውን በጠላትነት የመተያየት የፖለቲካ ትርክት በ21ኛው ክፍለ ዘመን አስቀጥላለሁ የሚል አስተሳሰብ አሁን ቦታ የለውም፡፡ ዓለም ተለውጣለች። “ኢትዮጵያን አፍነን ወይም ዘግተን፣ በእኛ ተፅዕኖ ስርና ችሮታ እናኖራታለን” የሚለው አስተሳሰብ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ጉዳቱ ደግሞ አንድ ቦታ ብቻ የሚቆም አይደለም፡፡
130 ሚሊዮን ህዝብ ምንም ዓይነት መውጫ በር እንዳይኖረው አድርጎ አፍኖ የማኖር አስተሳሰብ በተለይ በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ገፋፊነት የሚደረገው እንቅስቃሴ ለጎረቤት ሀገራትም አያዋጣም፡፡ ዘመኑም፤ ትውልዱም ተቀይሯል፡፡ ትውልዱ መተባበርን ያስቀድማል፡፡ የትውልዱ ትልቁ ጥያቄ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ኢኮኖሚ፣ የስራ ዕድል ፈጠራ ነው፡፡ በባዶ ሽለላና ቀረርቶ፣ ወታደራዊ ሰልፍ በማሳየት የህዝብ ሕይወት አይቀየርም፡፡
ላለፉት 34 ዓመታት ኤርትራ ውስጥ ምን ዓይነት ልማት እንዳለ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ ጥያቄ በጋራ እንጠቀም ነው። ዛሬ ኤርትራ ውስጥ የሀይል ችግር ስላለ የሲሚንቶ ፋብሪካ የለም፡፡ የሲሚንቶ ችግር ካለ ደግሞ የግንባታ እንቅስቃሴ አይኖርም፡፡ ለሲሚንቶ ፋብሪካ የሚሆን ሀይል ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ፡፡ እኛ ሀይል ስንሰጥ፤ እነሱ ደግሞ የባህር በር ሊሰጡን ይገባል፡፡ ይህ ሉዓላዊነትን የሚጋፋ አካሄድ አይደለም፡፡ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ መንገድ ነው፡፡
ኤርትራና ሌሎች ጎረቤት ሀገራት መረዳት ያለባቸው “ኢትዮጵያ የሌላን ሀብት ልዝረፍ አላለችም፡፡ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች ሀገር ናት። ትላልቅ የኢኮኖሚ አውታሮችን ገንብታለች፡፡ በአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለቤት ናት፡፡ ትልቅ የንግድ መርከብ አላት፡፡ ከእነዚህ እና መሰል ፕሮጀክቶች አካፍለን በሰጥቶ መቀበል መርህ የባህር በር እንዲሰጡን ነው የምንፈልገው፡፡ አሁን ያሉት መሪዎች የባህር በርን አጀንዳ ማድረጋቸው ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ልጆቻችን “ኢትዮጵያ የባህር በር የሌላት ለምንድን ነው?” እያሉ መጠየቅ ጀምረዋል፡፡ ኤርትራም ብንሄድ አዲስ ትውልድ ተፈጥሯል፡፡ “ነፃ ሀገር በመሆናችን ምን ትርፍ አገኘን? ከኢትዮጵያ ጋር በኢኮኖሚ ተሳስረን ተባብረን ብንሰራ ምን እናጣለን?” የሚል ምክንያታዊ ጥያቄ ማንሳት ጀምረዋል፡፡
አዲስ ልሳን፡- ኢትዮጵያ የባህር በር ካጣች በኋላ የባህር በር ባለቤት እንድትሆን ሲደረግ የነበረ ጥረት አለ ወይ? ካለስ ምን ይመስላል?
አቶ ኪያ፡- በ1960ዎቹ የኤርትራ ነፃነት እንቅስቃሴ ሲጀመር ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩት በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ የአረብ ሀገራት ናቸው። ቀይ ባህርንም ‘የአረብ ባህር’ እያሉ ነው የሚጠሩት፡፡ እነ ጀብሃ ኤርትራን ለመገንጠል ሲንቀሳቀሱ የመጀመሪያ ድጋፍ ያደረገችው በትጥቅ፣ በስልጠናና ስምሪት በመስጠት ግብፅ ናት፡፡ ሬዲዮ ጣቢያ በመክፈት ፀረ ኢትዮጵያ ፕሮፖጋንዳዎችን ስታስተላለፍ ነበር፡፡
በተማሪዎች ንቅናቄም ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በስህተት በእነሱ ወጥመድ ውስጥ የገቡበት ሁኔታ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ አንድ ተማሪ ተራማጅ ለመባል የኤርትራ መገንጠልን በመደገፍ ‘የኤርትራ ጥያቄ ትክክለኛ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው፤ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ነፃ መውጣት አለባት’ በሚል ያስረዳ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዙዎቹ የተቃኙት ቀድሞ እንቅስቃሴውን በጀመሩት በአብዛኛው የኤርትራ ተማሪዎች ነበር፡፡ እነዚህ ተማሪዎች የትግራይንም ተማሪዎች በመያዝ ወደ ተማሪዎች ንቅናቄ በመግባት የኤርትራ ጥያቄ ሳይንሳዊ እንደሆነ፣ ኢትዮጵያ ከባህር ጋር ያላት ቁርኝት ግምት ውስጥ ባላስገባ መልኩ በጥራዝ ነጠቅ ሲያቀነቅኑ ነበር፡፡ ትርክቱ በመጨረሻም የኤርትራ ነፃ አውጪ ግንባር፣ የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር ፈጠረ፡፡ በሰነዶችም እንደተፃፈው፣ ህወሓት የኤርትራ ነፃ አውጪ ግንባር ታናሽ ወንድም ነው፡፡ የኤርትራ ነፃ አውጪ ግንባር ቀድሞ ነው የተመሰረተው፡፡ ከውጭ ያለውን ግንኙነት ሲመራ፣ የሚገኘውን ድጋፍ ሲያደራጅ የነበረው፣ የተሻለ ልምድና አቅም ያለው የኤርትራው ቡድን ነው፡፡ ህወሓት የኤርትራ ነፃ አውጪ ግንባር የጠየቀውን ጥያቄ ሁሉ አንድም መደራደሪያ ሳያመጣ ነው ሲቀበል የነበረው፡፡ የኤርትራን ከኢትዮጵያ መገንጠል ገና ማዕከላዊ ስልጣን ሳይቆጣጠር ነው ሙሉ በሙሉ የተስማማው፡፡ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር የነበራትን ባህር ሀይል፣ የጦር መርከቦች፣ የነዳጅ ማጣሪያ ላይ ጥያቄ ሳያቀርብ ሙሉ በሙሉ ለኤርትራ አስረክቧል፡፡
በህግ ባልና ሚስት ሲፋቱ ንብረት ይከፋፈላሉ፡፡ ንብረት ብቻ ሳይሆን እዳም ካለ ይካፈላሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ህግ ኤርትራ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ስም የመጣ ብድር ወይም እዳ ካለ እሱንም ይዛ መሄድ ነበረባት፡፡ ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ስትለይ የነዳጅ ቦታዎችን ብቻ አይደለም ይዛ የሄደችው፡፡ ሱዳን እንደሀገር ከተቀበለችው እዳ በሚደርስባት ልክ ተሰልቶ ይዛ ሄዳለች፡፡ የኢትዮጵያ መንግስታት በኤርትራ የሰሯቸው ትላልቅ ፕሮጀክቶች ነበሩ፡፡ ፕሮጀክቶቹ በኢትዮጵያ ህዝብ ስም በመጣ ብድር የተሰሩ ናቸው፡፡ በከተማ ልማት፣ የወደብ ማስፋፊያ፣ የነዳጅ ማጣሪያ እና ሌሎችም ስራዎች ከፍተኛ ሀብት ፈስሶባቸዋል። ነገር ግን ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትለይ እነዚህን ሀብቶች ምክንያት በማድረግ ድርድር አልተደረገም፡፡ ገና ህዝበ ውሳኔ ሳይደረግ ነው ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችው፡፡

አዲስ ልሳን፡- ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችበት መንገድ የህግ መሠረት እንደሌለው የሚያነሱ ወገኖች አሉ። እርስዎ ይህን እንዴት ያዩታል?
አቶ ኪያ፡- አዎ! የህግ መሰረት የለውም፡፡ በመጀመሪያ ኢህአዴግ አሸንፎ ማዕከላዊ መንግስቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ሰኔ ወር ላይ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያሳተፈ ኮንፈረንስ ተካሂዶ ነበር፡፡ በርግጥ በኮንፈረንሱ እነማን ይሳተፉ የሚለውን የወሰነው ህወሓት ነው፡፡ ያኔ የበላይነት የነበረው ህወሓት ነበር፤ ከጀርባው ደግሞ ሻእቢያ ነበረ፡፡ በሰኔው ጉባኤ የሽግግር መንግስት ተቋቋመ፡፡ አርማው ድልድይ ሲሆን ስሙ እንደሚያመላክተው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚያሸጋግር እንጂ በኢትዮጵያውያን ይሁንታ የተመረጠ መንግስት አልነበረም፡፡ በሽግግር መንግስቱ ወይም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደረጃ ወደብን በተመለከተ ምክክር የተደረገበት ቃለ ጉባኤ ወይም ደብዳቤ የለም፡፡
በዓለም አቀፍ ህግ አንድ ሀገር፣ ሀገር ለመባል አራት ነገሮች መሟላት አለባቸው፡፡ ህዝብ፣ ግዛት፣ መንግስት እና ዓለም አቀፍ እውቅና ናቸው፡፡ ብዙ ሀገራት የሚቸገሩት ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ሶማሊላንድ ሶስቱን አሟልታ ሀገር ለመሆን የጎደላት እውቅና ማግኘት ነው፡፡ ይህም የሆነው የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግስት እውቅና ስላልሰጠ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ህግ የሀገራት የግዛት አንድነት መጠበቅ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው መርህ ነው፡፡ የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መቋቋሚያ አዋጅን ብናይ የሀገራት የግዛት አንድነት ማስጠበቅ ዋና መሰረቱ ነው፡፡
ህወሓት የእውቅና ደብዳቤ ለሻእቢያ ባይሰጥ፤ ሻእቢያ አስመራንም ይዞ ዕድሜ ልክ ይዋጋል እንጂ ኤርትራ ሀገር አይሆንም ነበር፡፡ በዓለም ላይ ለሚገነጠል ሀገር ከነባህርና ወደቡ እውቅና ስጡልኝ ብሎ የለመነ ሀገር የለም፤ ከህወሓት መንግስት በስተቀር፡፡ ኤርትራ ከኢትዮጵያ የተገነጠለችበት፣ ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችበት የህግ ሂደት በጣም በብዙ ስህተቶች የተሞላ፣ የኢትዮጵያን ዘላቂ የሆነ ብሔራዊ ጥቅም ያላስከበረ፣ በአፈሙዝ ተፅዕኖ የተደረገ ነው፡፡ በጣም የሚያሳዝነው የኤርትራ ነፃነት እውቅና ሲሰጥ፣ በምላሹ ቢያንስ 20 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ወደ ባህር መውጫ በር ኢትዮጵያ እንድታገኝ በዓለም አቀፍ ህግ ተቀባይነት ያለው ገዥ የሆነ ውል መዋዋል ያስፈልግ ነበር፡፡ የባህር ጠረፉ ረዥም ነው፡፡ ከራስ ዱሜራህ እስከ ራስ ካሳር ድረስ ከ1 ሺህ 200 ሜትር በላይ ይሸፍናል፡፡
ከመነሻው የኤርትራ ጥያቄ፣ ኤርትራዊያን ነፃ ወጥተው፣ በኢኮኖሚ አድገው የተሻለ ሀገር መፍጠርን ከግምት የከተተ አይደለም፡፡ ዋና ዓላማው ኢትዮጵያ ከውጭ ዓለም ጋር የምትገናኝበትን መውጫ በር መዝጋት ነው፡፡ ከውስጥ ኤርትራውያን የመጣ ሳይሆን በውጭ ሀይሎች የተጫነ ነው፡፡
የተባበሩት መንግስታት የባህር ህግ ኮንቬንሸን በአንቀፅ 125 እና 127 ላይ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ወደ ባህር የመዝለቅ መብት ይደነግጋል፡፡ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት የባህር በር ባለው ሀገር በኩል ማንኛውንም የትራንስፖርት አማራጭ በመጠቀም ወደ ባህር መዝለቅ ይችሉ ዘንድ የባህር በር ያላቸው ሀገራት መተባበር እንዳለባቸው ያስቀምጣል፡፡ ባህር የመላው ዓለም ንብረት ነው፡፡ በዚህ ንብረት ላይ የኢትዮጵያ መርከቦች የመቅዘፍና የትራንስፖርት አገልግሎት የመስጠት ሙሉ መብት አላቸው፡፡ የባህር ጠረፍ ያላቸው ሀገራት የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ባህር እንዳይጠቀሙ መከልከል አይችሉም፡፡
ከዚህ ባሻገር በንግግር፣ በሁለትዮሽ፣ ባለብዙ ወገን ድርድር፣ ሁሉንም አሸናፊ በሚያደርግ መንገድ የባህር በር ማግኘት የሚቻልበት መንገድ አለ፡፡ ይህ ካልሆነ ኤርትራ ከኢትዮጵያ የተለየችበት መንገድ ኢትዮጵያን የባህር በር አልባ ያደረገውን፣ የህግ መሰረት የሌለውን ሂደት በማንሳት የመከራከር መብት አለን፡፡
ሌላው መታወቅ ያለበት ልክ ዓባይ ላይ ግድብ እንዳይሰራ ሲደረግ እንደነበረው፣ የትኛውም ‘የነፃነት ታጋይ ነኝ’ ከሚል፣ የኢትዮጵያን ሀገረ መንግስትና ገዥ መንግስት ከሚቃወም ቡድን ጀርባ ግብፅ አለች፡፡ ደፈር ብሎ ኢትዮጵያ ወደብና የባህር በር ይገባታል የሚል መንግስት ካለ እንደ አደጋ በመውሰድ፣ ኢትዮጵያ ሁልጊዜ በውስጥ ጉዳዮቿ እንድትጠመድ ታሪካዊ ጠላቶች ይሰራሉ፡፡ ከኢትዮጵያ በተቃራኒ የሆነን ማንኛውንም ሀይል የጦር መሳሪያ በማስታጠቅ፣ ስልጠና በመስጠት፣ በፕሮፖጋንዳ፣ በዓለም አቀፍ ተቋማት፣ በጋዜጠኞች፣ በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ጫና ለመፍጠር እንደሚሰሩ ታይቷል፡፡
አዲስ ልሳን፡- የባህር በር የማግኘት ጥያቄ እውን እንዲሆን ከኢትዮጵያውያን ምን ይጠበቃል?
አቶ ኪያ፡- ጥያቄውን አጠናክሮ መቀጠል፤ የተለያዩ አማራጮችን ማቅረብ በተለይ ደግሞ ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ አማራጮችን መከተል ያስፈልጋል። ትውልዱም የፖለቲካ አመራሩም ትኩረት ሰጥቶ፣ በውስጥ ያሉ ትናንሽ ችግሮችን፤ የብሔር ይሁን የኃይማኖት ልዩነትን ወደ ጎን በመተው፣ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር፤ ኢትዮጵያውያንን እንደህዝብ አንድ የሚያደርግ አጀንዳ አድርጎ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ የሽምግልና አማራጮችንም በደንብ መከተል ያስፈልጋል፡፡ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች (ኢትዮጵያና ኤርትራ) በባህል፣ በቋንቋና እምነት የተሳሰሩ ናቸው፡፡ መንግስታት ይቀያየራሉ፤ ህዝብ ግን ይቀጥላል፡፡ የሁለቱን ሀገራት ዘላቂ ጥቅም ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ልሳን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ
እናመሰግናለን፡፡
አቶ ኪያ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
በስንታየሁ ምትኩ