በአንድ ጀንበር የስራ ዕድል ፈጠራ መርሃ ግብሩ

• 20 ሺህ 900 ዜጎች ወደ ስራ ይገባሉ
• ባለፉት አራት ወራት ብቻ 137 ሺህ 111 ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል
• ከ2013 እስከ 2017 ዓ.ም ብቻ ለ1 ሚሊዮን 841 ሺህ 532 ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል

ወጣት ይሄይስ መንግስቱ በጋርመንት አካባቢ በአንድ የኮንስትራክሽን ድርጅት በረዳት የማሽን ኦፕሬተርነት ሙያ ተቀጥሮ እየሰራ ነው፡፡ ቀደም ሲል ስራን በማማረጥ ብዙ ጊዜውን እንዳሳለፈ አስታውሶ፣ አሁን ግን በመዲናዋ እየተከናወኑ ያሉ ልማቶች በተለይም ቀንና ሌሊት የሚሰሩ ፕሮጀክቶችና በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚሰጡ ስልጠናዎች ስራን ሳይንቅ እንዲሰራ ብርታት እንደሆኑት አጫውቶናል። እሱም ሆነ ጓደኞቹ ቀንና ሌሊት በሺፍት እየሰሩ የተሻለ ገቢና የስራ ልምድ እያገኙ መሆናቸውን በመጠቆም “መስራት መሰልጠን ነውና  ወጣቶች የስራ ባህላቸውን አሻሽለን እራሳችንን ብቻ ሳይሆን ሀገራችንን ከፍ እናድርግ” ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

በአንድ ጀንበር የስራ ዕድል ፈጠራ መርሃ ግብር፣ እንደከተማ እየተከናወነ ስላለው የስራ ዕድል ፈጠራ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ እና ክህሎት ቢሮ የስራ ስምሪት አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሰበሃዲን ሱልጣን እንደገለፁት፣ ከዚህ በፊት እንደከተማ በስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትልቅ ችግር ሆነው ከሚጠቀሱ ነገሮች መካከል ደካማ የስራ ባህል ዋናው ማነቆ ነው፡፡

ወጣቱ ስራ ይፈልጋል፤ ይህንንም ተከትሎ በስራ ፈላጊ መዝገብ ላይ ስሙን ያሰፍራል፡፡ ይሁን እንጂ ስራው ሲቀርብለት ጠዋት ወጥቶ ሲሰራ ውሎ ማታ መግባትን አይፈልግም፡፡ ከባባድ ተግባራት ላይ ሳይሆን በቀላሉ ጥቂት ገንዘብ ማገኛ መንገድ ላይ መሰማራትን ይፈልግ እንደነበር አውስተዋል፡፡

አሁን ግን ይላሉ አቶ ሰበሃዲን፤ በከተማዋ በተሰሩና እየተሰሩ ባሉ ፕሮጀክቶች እየተለመደ የመጣው የቀንና የሌሊት ስራ (7/24) ትልቅ ተሞክሮ ሆኖናል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በመንግስት ደረጃ የተሰሩና እየተሰሩ ያሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ቀንና ሌሊት በሦስት ሺፍት የሚሰሩ በመሆናቸው በርካታ የስራ ዕድል መፍጠር ችለዋል፡፡ ለአብነትም በሦስት ሺፍት ሦስት የተለያየ ሰው በአንድ ፕሮጀክት ላይ የሚሰማራበት እድል መፈጠሩን ጠቅሰዋል፡፡

በመሆኑም ይህ አይነት አሰራር በአንድም በሌላም መንገድ በርካታ የስራ ዕድል እንዲፈጠር እና ስራን ሳይንቁ ቀንም ሌሊትም መስራት እንደሚቻል ማስተማሪያ መሆን በመቻሉ የብዙዎችን አስተሳሰብ እየለወጡ ነው ብለዋል። በተለይም “ለካ በማታም መስራት ይቻላል?” የሚለው አስተሳሰብ በወጣቶች የስራ ባህልና በከተማዋ ሁለንተናዊ  ዕድገት ላይ ብዙ ለውጥ እያመጣ ነው ብለዋል አቶ ሰበሃዲን፡፡

አሁን ላይ ወጣቶችን ስለ ስራ እና ተያያዥ ጉዳዮች ለማስተማር ንድፈ ሀሳብ ላይ ብቻ የተመሰረተ ስልጠና ከመስጠት ወጥቶ 7/24 መስራት የሚችሉ ወጣቶችን በተሞክሮነት ማቅረብ ተጀምሯል፡፡ ለዚህ ደግሞ በመዲናዋ እየተገነቡ ያሉ የኮሪደር ልማቶችና መሰል ፕሮጀክቶች ያላቸው ድርሻ ከፍ ያለ ስለመሆኑም ነግረውናል፡፡

ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ይንገስ አለሙ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከናወኑ ያሉ ልማቶች የከተማዋን ውበትና ዘመናዊነት ከፍ ከማድረጋቸው ባሻገር በትውልዱ ዘንድ አዲስ የስራ ባህልን እያስተዋወቁ መሆናቸውን ተከትሎ በርግጥም ከተማዋ በአዲስ የስራ ባህል የተሻለ ለውጥ እያመጣች እና ለበርካቶችም የስራ ዕድል እየፈጠረች መሆኗን የሚያሳይና  በኢኮኖሚው ዘርፍም ትልቅ እምርታ የሚያመጣ ነው፡፡

በአንድ ጀንበር የስራ ዕድል ለመፍጠር የተጀመረው ጥረትም ያሉንን ፀጋዎች በሚገባ መለየትና መጠቀም ከቻልን ለበርካቶች የስራ ዕድል መፍጠር እንደምንችል  የሚያመላክትና ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ የሚያመጣ ነው፡፡ ወጣቱ የስራ ዕድል አገኘ ማለት ኑሮውን ከማሻሻሉ ባሻገር በምርትና ምርታማነት ላይ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል፡፡

ይህ ደግሞ ከከተማዋ ከፍታ ባሻገር በሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ ጉልህ ዕድገትን የሚያመጣ በመሆኑ ሌሎች ከተሞችም የስራ ድል የመፍጠር አቅማቸውን በሚገባ በመፈተሽ መስራት ከተቻለ የሀገሪቱን ዕድገት የበለጠ ማፋጠን እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ እና ክህሎት ቢሮ የስራ ስምሪት አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሰበሃዲን ሱልጣን እንደገለፁት ቢሮው በበጀት ዓመቱ ለ350 ሺህ ዜጎች የስራ ድል ለመፍጠር አቅዶ እየሰራ ነው፡፡ ባለፉት አራት ወራት ብቻ ለ137 ሺህ 111 ዜጎች ስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል፡፡

ይሁን እንጂ አሁን በተያዘው ሁኔታ የዜጎችን ጥያቄ ምላሽ እየሰጡ ከመሄድ ጋር በተያያዘ ትንሽ ውስንነት ያለበት በመሆኑ ተቋሙ ልዩ ዕቅድ በማቀድ ከጥቅምት እስከ ህዳር 30  ቀን 2018 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ውስጥ ለ20 ሺህ 900 ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ልዩ ዕቅድ አውጥቶ እየሰራ ነው፡፡

“በአንድ ጀንበር የስራ ዕድል መፍጠር” የተሰኘው ልዩ ዕቅድ ስኬታማነትም ቀደም ብሎ ምዝገባ የማካሄድ፣ ፀጋዎችን የመለየት እና እነዚህስ ጸጋዎች በትክክል ለዜጎች ዳቦ የሚያበሉ ናቸው ወይ? የሚለውን ነገር የመፈተሽ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

አቶ  ሰብሃዲን አክለውም፣  እንደ ከተማ ባለፉት አራት ወራት 222 ሺህ ዜጎች “የስራ ዕድል ይፈጠርልኝ” በሚል ተመዝግበዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ወደስራ የገቡት 137 ሺህ 111 ናቸው፡፡ በመሆኑም በዚህ መሃል ስራ ያልተፈጠረለት ዜጋ አለ።

ስለሆነም ያደራጀናቸውና ተደራጅተውም የተቀመጡ ዜጎች በመኖራቸው አሁንም የስራ ዕድል ይፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ እንደ ከተማ የስራ ዕድል ሊፈጥሩ የሚችሉ በሚል የተለዩ 18 ስራ ፈጣሪዎች እና 5 አመቻች ተቋማት በድምሩ 23 ባለድርሻ አካላት አሉ፡፡

በመሆኑም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውን የጠቀሱት አቶ ሰብሃዲን ለአብነትም በኮንስትራክሽን፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በከተማ ግብርና፣ በአገልግሎት እና በንግድ ዘርፎች ያሉ የስራ ዕድል ጸጋዎች ተለይተዋል፡፡ ስራ ፈላጊዎችም ተደራጅተው ወደ እነዚህ ዘርፎች እንዲገቡ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ህዳር 30 ቀን 2018 ዓ.ም በአንድ ጀምበር በአዲስ አበባ ስቴዲዮም ከፍተኛ የከተማዋ የስራ ኃላፊዎች በሚገኙበት በሚደረግ ዝግጅት ለዜጎቹ ስራዎቹ በይፋ ይሰጣሉ፡፡ ወደ ስራም ይገባሉ። ይህም ዕቅዳችንን የምናሳካበት አንዱ መንገድ ነው ያሉት አቶ ሰበሃዲን፣ ይህ የአንድ ጀንበር የስራ ዕድል ፈጠራ ልዩ ዕቅድ ትኩረቱ ከቅጥር ባለፈ መደራጀትን መሰረት ያደረገ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ክፍለ ከተሞችም ቀደም ብለው ስራ ፈላጊውን እና ቀጣሪውን የሚያገናኝ አውደ ርዕይ በማዘጋጀት በቀን 1 ሺህ እና ከዚያ በላይ የስራ ዕድል እየፈጠሩ ነው። በማዕከል ደረጃም  ህዳር 30 ቀን 2018 ዓ.ም ይፋ በሚደረገው መርሃ ግብር ለ20 ሺህ 900 ዜጎች ስራ ዕድል ይፈጠራል ብለዋል፡፡

የአንድ ጀንበር ስራ ዕድል ፈጠራ ትልቁ ዓላማው በበጀት ዓመቱ የተያዘውን ዕቅድ ማሳካት ሲሆን፣ ይህም ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል እየፈጠሩ በ6 ወር ውስጥም ከተያዘው ዕቅድ በላይ በማሳካት ተደራጅተው ወደስራ ያልገቡ ወጣቶችን ፍላጎት ማሟላት የሚያስችል ነው፡፡

እንደ ቢሮው መረጃ፣ በ5 ዓመቱ ስትራቴጂክ እቅድ ክንውን መሰረት በ2013 ዓ.ም ለ345 ሺህ 62፣ በ2014 ዓ.ም ለ421 ሺህ 850፣ በ2015 ዓ.ም ለ416 ሺህ 999፣ በ2016 ዓ.ም ለ291 ሺህ 577 እንዲሁም በ2017 ዓ.ም ለ366 ሺህ 44 ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል፡፡ ከዚህ ውስጥ እስከ 2015 ዓ.ም ያለው ቋሚ እና ጊዜያዊ የስራ ዕድል ሲሆን፤ የቀሩት ሁለት ዓመታት ደግሞ ቋሚ የስራ ዕድሎች ናቸው፡፡ በእነዚህ አምስት ዓመታትም በጥቅሉ 1 ሚሊዮን 841 ሺህ 532 የስራ ዕድሎች ተፈጥረዋል፡፡

መርሃ ግብሩ ስራና ሰራተኛን የምናገናኝበት አንዱ መሳሪያችን ነው። እያንዳንዱ ተግባርም በየሳምንቱና በየአስራ አምስት ቀናቱ እንደ ከተማ በተዋቀሩ የአመራርና ቴክኒካል ቋሚ ኮሚቴዎች እየተገመገመ ሲሆን፣ እስካሁን ባለው ሂደትም ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

የአንድ ጀንበር የስራ ዕድል መርሃ ግብሩ በማዕከል ደረጃ የሚገኙ ስራ እድል የሚፈጥሩ  ባለድርሻ ተቋማት  የሚፈጠር ነው፡፡ ስራ እድሉም ትኩረት የሚያደርገው ኢንተርፕራይዝ በማደራጀት እንደሆነም አቶ ሰብሃዲን ተናግረዋል፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review