“አዲስ አበባ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች መናኸሪያ መሆኗ ለጋራ መግባባት እንደ ትምህርት ቤት ያገለግላል”
በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህሩ ጉተማ ኢማና
የቻይና ዋና ከተማ የሆነችው ቤጂንግ በዋነኝነት የሃን ብሔር የሚኖርባት ብትሆንም ልክ እንደ ቻይና ሁሉ የተለያዩ ብሔረሰቦችን የያዘች ህብረ ብሔራዊት ከተማ ናት። የተለያዩ ሀገራት ዜጎችን ጨምሮ እንደ ሁይ፣ ማንቹ፣ ሞንጎል ያሉ ብሔሮችን በውስጧ የያዘችው ቤጂንግ እያንዳንዱ ብሔረሰብ የራሱን ባህል፣ ወግ፣ ምግብ፣ ቋንቋ እና የአለባበስ ዘይቤ ወደ ከተማዋ ያመጣል። ይህ ደግሞ ቤጂንግን የበለፀገች እና ዓለም አቀፋዊ ከተማ እንድትሆን አድርጓታል።
ከኢኮኖሚ አስተዋጽኦ አንጻር ከተመለከትነው የቤጂንግ ብሔረሰቦች በተለያዩ ዘርፎች ማለትም በንግድ፣ በትምህርት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ውስጥ በመስራት ለከተማዋ የኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። በሌላም በኩል ቤጂንግ የቻይና ፖለቲካዊ ማዕከል እንደመሆኗ መጠን፣ የሁሉም ብሔረሰቦች ተወካዮች እና ምሁራን መኖራቸው የብሔራዊ አንድነት ስሜት እንዲጎለብት ያደርጋል። የቤጂንግ ብሔረሰቦች ብዝሃነት የከተማዋን ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መሠረት በማጠናከር ዓለም አቀፋዊ ከተማ እንድትሆን ትልቅ ሚና ይጫወታሉ፡፡
ይህ የቤጂንግ ተሞክሮ ታዲያ በሪቻርድ ፍሎሪዳ ወደተፃፈው “ዘ ራይዝ ኦፍ ዘ ክሬኤቲቭ ክላስ” (The Rise of the Creative Class) መጽሐፍ ወደያዘው ጽንሰ ሀሳብ ያመራናል፡፡ ይህ መጽሐፍ እ.ኤ.አ በ2002 ለህትመት ሲበቃ ይዞት የመጣው ሀሳብ በተለይ በከተማ ልማት ዘርፍ አዲስ የአስተሳሰብ አዝማሚያ የፈጠረ ነበር። መጽሐፉ የዘመናዊ ከተሞችን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና ስኬት የሚወስነው የፋብሪካዎች ወይም የባንኮች መኖር ሳይሆን፣ ከተሞች ፈጠራ ያላቸውን ሰዎች ለመሳብና ለማስቀረት ባላቸው አቅም ላይ መሆኑን ይሞግታል።
ደራሲው ሪቻርድ ፍሎሪዳ እንደሚሉት አንድ ከተማ የፈጠራ ሰዎችን መሳብና ማቆየት የምትችለው ደግሞ ሦስት ዋና ዋና ነገሮች ሲሟሉ ብቻ ነው። እነዚህም የቴክኖሎጂ አቅርቦትና መሠረተ ልማት፣ ከፍተኛ የሰለጠነና የተማረ የሰው ኃይል ብዛት እና የከተማዋ ክፍትነትና የብዝሃነት ተቀባይነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ደራሲው ሪቻርድ ፍሎሪዳ ያብራራሉ፡፡ በተለይም ከተሞች ዘር፣ ኃይማኖት፣ የጾታ ዝንባሌ ወይም የአኗኗር ዘይቤ ሳይለይ ማንኛውንም አይነት ሰው በደስታ የምትቀበል መሆን አለባት ይላሉ ደራሲው።
ከላይ በአስረጅነት ከተጠቀሰችው ቤጂንግ በተጨማሪ እንደ ለንደን፣ ኒው ዮርክ እና ቶሮንቶ ያሉ ከተሞችም ብዝሃነትን በብቃት በመምራት ዓለም አቀፍ የንግድና የፋይናንስ ማዕከል ሆነው መቀጠል ችለዋል። የኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሕይወት ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ ከዚህ አንጻር ስትመዘን የዘር፣ የኃይማኖት፣ የጾታ ዝንባሌ ወይም የአኗኗር ዘይቤ ሳይለይ ማንኛውንም አይነት ሰው ከሚኖርባቸው ከተሞች መካከል ሆና እናገኛታለን፡፡
መዲናዋ የሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መኖሪያ መሆኗ ለከተማዋ እድገት ትልቅ ሀብት እንደሆነ ምሁራን ይስማማሉ። የባህል ብዝሃነት ደግሞ የከተሞችን ምርታማነት፣ የፈጠራ አቅም እና ማህበራዊ ጥንካሬ በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል ይላሉ።
አዲስ አበባ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ (Economic Powerhouse) ስትሆን፣ ከሀገር የከተማ ጠቅላላ ምርት (Urban GDP) ከፍተኛውን ድርሻ ትይዛለች። ይህ ስኬት ከከተማዋ የብዝሃነት ባህሪ ጋር በቅርብ የተሳሰረ ነው ተብሎ ይታሰባል። ለመሆኑ የሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች መኖሪያ የሆነችው አዲስ አበባ የሁሉም ቤት መሆኗ ምን አስገኝቶላታል? እንደ አዲስ አበባ አይነት አወቃቀር ያላቸው ከተሞችስ ከዚህ አንጻር እንዴት ይታያሉ? የሚሉ ጉዳዮችን መዳሰስ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡
የስነ ልቦና ምሁራን እንደሚጠቁሙት፣ የተለያየ አስተሳሰብና ባህል ያላቸው ሰዎች በአንድ ቦታ ሲሰባሰቡ፣ የፈጠራ እና አዲስ ሥራ የመጀመር አቅም ይጨምራል። ከተለያየ ብሔር የመጡ ግለሰቦች የራሳቸውን የንግድ ልምድና ፍላጎት ይዘው ሲመጡ፣ የተለያዩ የንግድ ዓይነቶችና አገልግሎቶች እንዲፈጠሩ ያደርጋል። ለምሳሌ የባህል ምግብ ቤቶች፣ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውና የንግድ አቅርቦት ሰንሰለቶች ከብዝሃነት ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያገኙም “ዘ ራይዝ ኦፍ ዘ ክሬኤቲቭ ክላስ” (The Rise of the Creative Class) መጽሐፍ ደራሲው ሪቻርድ ፍሎሪዳ ይገልጻሉ።
ከተለያየ ባህልና አስተዳደግ የመጡ ሰዎች አብረው ሲሰሩ፣ ለተለያዩ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት አዳዲስና ፈጠራ የሞሉባቸው ሀሳቦችን ለመፍጠር ያግዛል የሚሉት ደግሞ በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህሩ ጉተማ ኢማና ናቸው። በአዲስ አበባ ያለው እውነታም እንደሚያሳየው የተለያዩ የንግድ ዓይነቶች፣ ሬስቶራንቶች እና አገልግሎቶች (ለምሳሌ፡- የየብሔሩ ባህላዊ ምግቦች) መኖራቸው የፈጠራ ውጤት እና የገበያ ተፈላጊነት ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
ከተለያዩ ክልሎች የመጡ ሰዎች ልዩ ልዩ ክህሎቶችን፣ የንግድ ልምዶችን እና የፈጠራ ሀሳቦችን ይዘው ይመጣሉ። ይህ የሰው ኃይል ብዝሃነት የሥራ ፈጠራን ያበረታታል፤ የገበያ ተወዳዳሪነትን ይጨምራል፤ ከተማዋን ለተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ማዕከል እንድትሆን ያደርጋታል ይላሉ። እንደዚሁም የብዝሃነት ባህሪው የተለያዩ ምርቶች እና አገልግሎቶች እንዲፈጠሩ ያደርጋል። የብሔረሰብ ምግቦች፣ የባህል አልባሳት፣ እደ-ጥበብ እና የቋንቋ አገልግሎቶች በስፋት ይገኛሉ። ይህ የገበያ ብዝሃነት የከተማዋን የንግድ እንቅስቃሴ ያሳድገዋል።
በሌላም በኩል መዲናዋ የኢትዮጵያ ማዕከል ከመሆኗም ባሻገር የአፍሪካ ህብረት እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ በመሆኗ ዓለም አቀፍ ትኩረት አላት። የብሔረሰቦች ባህላዊ ልዩነትና ብዝሃነት ይህን ዓለም አቀፋዊ ገፅታ ያጠናክረዋል፤ ቱሪስቶችና የውጭ ባለሀብቶችን የመሳብ አቅሟን ከፍ ያደርጋል። ከተማዋ ከተለያዩ ክልሎች የመጡ ሠራተኞችንና ባለሙያዎችን ስለሚስብ፣ የንግድ ድርጅቶች ሰፊ የክህሎት ምርጫ ያገኛሉ። ይህም የሥራ ገበያውን የበለጠ ተለዋዋጭ እና ጠንካራ ያደርገዋል። የተለያዩ የምግብ አይነቶች፣ ጥበቦች እና የአኗኗር ዘይቤዎች ለቱሪስቶች ልምድ የሚያበለፅጉ ሲሆን ለከተማዋ የኢኮኖሚ ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ያደርጋሉ።
አዲስ አበባ የየብሔረሰቡን ሙዚቃ፣ የጥበብ ስራዎች፣ ክብረ በዓላትና የአለባበስ ዘይቤ በአንድነት የምታስተናግድ ማዕከል ነች። ይህ የባህል ብልፅግና የከተማዋን ነዋሪዎች የሕይወት ጥራት ያሳድጋል፤ እንዲሁም ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ትልቅ መደላድል ይፈጥራል። የማህበራዊ ሳይንስ ተመራማሪዎች እንደሚሉት አዲስ አበባ የብሔረሰቦች መናኸሪያ መሆኗ ለማህበራዊ መሳሳብ እና ለጋራ መግባባት እንደ ትምህርት ቤት ያገለግላል። ከተለያዩ ብሔሮች የተዋቀረ ማህበረሰብ ውስጥ ግለሰቦች የሌላውን ባህል፣ ቋንቋ እና ልማድ በየዕለቱ በመስተጋብር ይማራሉ።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሀቢታት (UN-Habitat) በተዘጋጀው “State of Addis Ababa 2017 Report” ላይ እንደተገለጸው፣ የከተማዋ ነዋሪዎች የማህበራዊ መረቦችን ሳያጡ በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ እያደገ መጥቷል። የተለያዩ ብሔረሰቦች ጎን ለጎን ሲኖሩ፣ የግድ የባህል ልውውጥ ይፈጠራል። ይህ መቻቻልን፣ መግባባትን እና ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ለከተማዋ ማህበራዊ መረጋጋት እና ሰላማዊ ዕድገት አስተዋጽኦ እንዳለውም ሪፖርቱ ያትታል።
በቻርለስ ላንድሪ እና ፊል ውድ የተጻፈው ‘The Intercultural City:- Planning for Diversity Advantage’ የተሰኘውን መጽሐፍ ጠቅሰን ጉዳያችንን እንቋጭ፡፡ ከተሞች ብዝሃነትን እንደ ችግር ሳይሆን እንደ ስልታዊ ጠቀሜታ (Strategic Advantage) መውሰድ እንዳለባቸው የሚመክረው መጽሐፉ የባህል እና የብሔረሰቦችን ልዩነት እንደ ችግር ወይም እንደ ግዴታ ከማየት ይልቅ እንደ ዋና የኢኮኖሚና ማህበራዊ ሀብት በመጠቀም ለከተማዋ ጥቅም ማዋል እንደሚቻል ያብራራል፡፡ ይህን የተረዳችው የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባም የሁሉም አቃፊ ቤት መሆኗ ከተማዋን የበለጠ ዓለም አቀፋዊ ገፅታ እንድትይዝ አስችሏታል።
በሳህሉ ብርሃኑ