ባሳለፍነው ሳምንት በመዲናዋ አዲስ አበባ የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች እና አዳዲስ ጥበባዊ ስራዎች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም የተለያዩ ጥበባዊ መሰናዶዎች ይደረጋሉ፡፡ ከተሰናዱ ዋና ዋና ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች መካከል የመጻሕፍት ህትመትና ምረቃ፣ የሥዕል አውደ ርዕይ፣ የቴአትር መርሃ ግብር እና ሌሎች መሰናዶዎች ይገኙበታል፡፡ ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡
መጻህፍት
በ’የጦር ሜዳ ውሎ’ መጽሐፍ ላይ ውይይት ይደረጋል፡፡ ዛሬ ቅዳሜ ከ8፡00 ሰዓት ጀምሮ ‘የጦር ሜዳ ውሎ’ በተሰኘው የብርጋዴር ጄነራል ተስፋዬ ሀብተማርያም መጽሐፍ ላይ ውይይት ይደረጋል፡፡ የመጽሐፉ ደራሲ ብርጋዴር ጄነራል ተስፋዬ ሀብተማርያም የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት የአየር ሃይል አዛዥ የነበሩ ሲሆን፣ በተለይ የሀገርን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት ለማስከበር በተደረጉ ተጋድሎዎች ታላላቅ ጀብዱዎችን በመፈጸም ይታወቃሉ፡፡ መጽሐፉ ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ዳር ድንበሯን እንዳታጣ በናቅፋና በሌሎችም የጦር ሜዳዎች የተደረጉ አስደናቂ ተጋድሎዎችን ያስቃኛል፡፡ የመጽሐፉ ውይይት ያሰናዳው ዛጎል የመጻህፍት ባንክ ሲሆን፣ አዘጋጅና አቅራቢ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ነው፡፡ ዝግጅቱ ቀበና በሚገኘው ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (Fss) አዳራሽ ውስጥ ይከናወናል ተብሏል።
‘አዲስ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መዝገበ ቃላት’ ለንባብ በቃ፡፡ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የሳይንስና ቴክኖሎጂ የጽንሰ ሐሳብ አቻ ስያሜዎችን ከብያኔዎቻቸው ጋር የያዘ አዲስ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መዝገበ ቃላት መጽሐፍ ባሳለፍነው ሳምንት በይፋ ተመርቆ ለገበያ ውሏል፡፡ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕውቀት ህዝባዊ ለማድረግ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት የተነገረለት ይሄ የመዝገበ ቃላት መጽሐፍ የሀገሪቱ ታላላቅ ምሁራን ተሳትፈውበታል፡፡
ከመዝገበ ቃላት መጽሐፉ አርታያን መካከል አንዱ የሆነው ደራሲና ሃያሲ ቴዎድሮስ አጥላው በማህበራዊ የትስስር ገጹ ስለመጽሐፉ እንዲህ ብሏል፤ “በመጀመሪያ ዕትሙ ከ30 በላይ ከሚሆኑ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች የተመረጡ 11 ሺህ 600 ሙያዊ ሥያሜዎች በአቻ የአማርኛ ሥያሜዎች የተፈቱበት እና የተበየኑበት ግዙፍ መዝገበ ቃላት ነው። ይሄ ከ140 በላይ ምሁራንን ያሳተፈው መዝገበ ቃላት የሞባይል መተግበርያም እየተዘጋጀለት ነው። ይህ ደግሞ መዝገበ ቃላቱን በእያንዳንዱ ሰው ቤት ማዳረስ ከማስቻሉ በላይ፤ ሥራውን የማይቋረጥ፣ የሚያድግ፣ የሚሻሻል ያደርገዋል፡፡ እኔም በአርትዖት እና በአሳታሚነት ያቅሜን የማበረክትበት ዕድል በማግኘቴ ትልቅ ደስታ ተሰምቶኛል። ምናልባት እስከዛሬ ከተሳተፍኩባቸው የመጽሐፍ ፕሮጀክቶች ግዙፉ ይሄ ሳይኾን አይቀርም” በማለት ትልቅ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው መጽሐፍ ለንባብ መብቃቱን በገጹ አስፍሯል። የመጻሕፍት ወዳጆችም መጽሐፉ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚና በሌሎች የመጻሕፍት መሸጫ መደብሮች ውስጥ ማግኘት ትችላላችሁ ተብሏል፡፡
በተጨማሪም የታዋቂዋ የወግ ጸሃፊ የህይወት እምሻው አዲሱ መጽሐፍ ዛሬ ለንባብ ይበቃል፡፡ ‘ዥዋዠዌ’ የተሰኘው የአጫጭር ልብ ወለዶች ስብስብ መጽሐፍ ዛሬ በአዲሱ የጃፋር መጻሕፍት መደብር ውስጥ በይፋ ለንባብ እንደሚበቃ ደራሲዋ በማህበራዊ የትስስር ገጿ አስፍራለች፡፡ የደራሲዋ አድናቂዎችና የሥነ ጽሑፍ አፍቃሪያን ዛሬ ቅዳሜ 10፡00 ሰዓት ጀምሮ ለገሃር የሚገኘው የጃፋር መጻህፍት መደብር ተገኝተው ከደራሲዋ ጋር እየተጨዋወቱ ፊርማዋን ያረፈበት መጽሃፍ ማግኘት ትችላላችሁ ተብሏል፡፡
ሥዕል
‘አብሮነት’ የሥዕል አውደ ርዕይ በመታየት ላይ ነው፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት ረዕቡ ህዳር በፈንዲቃ የባህል ማዕከል ውስጥ በይፋ የተከፈተው አብሮነት የሥዕል አውደ ርዕይ የተለያዩ የሥዕል ሥራዎች የቀረቡበት ነው ተብሏል፡፡ ሰዓሊያን በቡድን ሆነው ባሰናዱት በዚህ የሥዕል አውደ ርዕይ አብሮነትና ህብረትን የሚያሳዩ የሥዕል ስራዎች ቀርበዋል፡፡ በአውደርዕዩ ላይ የሥዕል ሥራዎቻቸውን ካቀረቡ ሰዓሊያን መካከል ብሩ ወርቁ፣ ያሬድ ወንድወሰንና ዘውዱ ገብረሚካኤል ይገኙበታል፡፡ የስዕል አውደ ርዕዩ እስከ መጪው ህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ለተመልካች ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡ የስዕል አውደ ርዕዩ መስቀል አደባባይ አጠገብ በሚገኘው በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል ውስጥ ባለው በፈንዲቃ የባህል ማዕከል ውስጥ እየታየ ይገኛል፡፡
የቴአትር መርሃግብር
በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሁድ የተለያዩ ቴአትሮች ይታያሉ፡፡ 12ቱ እንግዶች የተሰኘው ቴአትር ቅዳሜ 8:30 ሰዓት በብሔራዊ ቴአትር ቤት ይታያል፡፡11፡30 ሰዓት ደግሞ ባሎችና ሚስቶች የተሰኘው ቴአትር በዚያው በብሔራዊ ቴአትር ይታያል፡፡እሁድ በ8፡30 ሰዓት ደግሞ ንጉሥ አርማህ ቴአትር፣ እንዲሁም እምዬ ብረቷ የተሰኘው ቴአትር ደግሞ በዚሁ በብሔራዊ ቴአትር 11፡30 ሰዓት ላይ ይታያል፡፡
በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ደግሞ እሁድ በ8:00 ሰዓት በዓሉ ግርማ ቤርሙዳ የተሰኘው ቴአትር ይታያል፡፡በተጨማሪም በቀጣይ ቀናት በብሔራዊ ቴአትር የሚታዩት ማክሰኞ በ11፡30 ሰዓት ሦስቱ አይጦች፣ ረዕቡ በ11፡30 ሰዓት የቅርብ ሩቅ ቴአትር፣ ሐሙስ ቀን 11:30 ሸምጋይ ቴአትር፣ አርብ በ11፡30 ሰዓት የሕይወት ታሪክ በብሔራዊ ቴአትር ለጥበብ አፍቃሪያን ለዕይታ ይቀርባሉ፡፡
በአብርሃም ገብሬ