ኪነ ጥበብ የአንድን ማህበረሰብ ሁለንተናዊ ጉዳዮች በማጉላት እና ሰዎች እንዲያስቡ፣ ያሰቡትን እንዲተገብሩ እና እንዲለወጡ በማነሳሳት ትልቅ ሚና ይጫወታል። የህይወት ልምዶችን በማንፀባረቅ በህብረተሰብ ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ይፈጥራል። በአጭሩ በሰውነት እንቅስቃሴ፤ በቁስ፤ በስዕል፣ በድምጽ፣ በጽሑፍ፣ በአለባበስና አመጋገብ፤ በብልሀት ተቀናብሮ የሚቀርብ የሚታይ፣ የሚደመጥ፣ የሚዳሰስ ውበት ነው። ጀሚል ከድር የተባለ ጸሐፊ “ኪነ ጥበብ እና ፍሬዎቹ” በሚል ባሰፈረው ጽሑፍ ላይ እንዳተተው ኪነ ጥበብ ማህበረሰቡን ስለማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ እና ሌሎች ጉዳዮች በማስተማር የበኩሉን አስተዋፅዖ ያበረክታል፡፡ እንዲሁም ሰዎች ለሀገራዊ ጉዳዮች መፍትሔ እንዲሰጡ እና በህብረተሰቡ ውስጥ አዎንታዊ ለውጦች እንዲያድጉ ያነሳሳል። በማህበረሰብ ውስጥ አንድነትና አብሮነትን ከሚሸምኑ፣ ያለ ቃላት በአዕምሮ ውስጥ የሚቀር ትምህርትን ከሚቀርጹ የኪነ ጥበብ ስራዎች ውስጥ አንዱ ስዕል ነው፡፡ የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍልም በነገው ዕለት የሚከበረውን ዓለም አቀፍ “የአብሮነትና መቻቻል ቀን” መነሻ በማድረግ ስዕል ለአብሮነት፣ አንድነትና የጋራ ትርክት ያለውን ሚና በተመለከተ በአጭሩ ዳሰሳ አድርጓል፡፡
ኪነ ጥበብ፣ በተለይም ስዕል፣ የሰው ልጅ ታሪክ፣ ስሜትና ተስፋ መገለጫ እንደመሆኑ መጠን፣ ከግለሰባዊ ውበት ፍለጋ የላቀ አቅም አለው። ምክንያቱም ስዕል ቋንቋ ሳይገድበው፣ ኃይማኖት ሳይለየው እና ፖለቲካ ሳይከፋፍለው የሰዎች ልብና አዕምሮ ጋር በቀላሉ የመድረስ ልዩ ኃይል አለው። በተጨማሪም በቀለም የተሳለ ምስል የጋራ ታሪክን፣ የጋራ ማንነትን እና የጋራ ርዕይን የማንጸባረቅ፣ የመቅረጽና የማጠናከር ታላቅ አቅም በውስጡ ይዟል።
ስዕል የተለያዩ ባህሎችና ማንነቶች ያሉትን ማህበረሰብ አንድ ላይ አምጥቶ፣ በልዩነት ውስጥ ያለውን ውበት እንዲያይና እንዲያከብር ያግዛል። አብሮነትና መተሳሰብን ያጎላል፡፡ በተጨማሪም ስዕል ያለፉትን የጋራ ድሎች፣ መስዋዕትነቶችና እሴቶች በምስል በማስቀመጥ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚያካትት ጠንካራና ዘላቂ የሀገር ትርክት እንዲገነባ ያግዛል። እንዲሁም የማህበረሰቡን ሀገራዊ ስሜት፣ አብሮነት፣ አዕምሯዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ይደግፋል።
ስዕል “የጋራ ትውስታን የመጠበቅና የማስተላለፍ የረጅም ጊዜ ታሪክ አለው” የሚባለውም ለዚሁ ነው። በኢትዮጵያ የጥንት ስዕሎች ላይ የሀገር ታሪክ፣ የእምነትና የባህል ዘይቤዎች ተቀላቅለው ይገኛሉ። ይህ የሚያሳየው ስዕል ዘመን ተሻጋሪ የሆነ የማህበረሰብ ምሰሶ መሆኑን ነው።
“ስዕል በቀለምና ብሩሽ ብቻ ያለቋንቋ ትልቅ የአብሮነትና የአንድነት መልዕክት ማስተላለፍ ይችላል፡፡ የማህበረሰብ ነጸብራቅ ነው” የሚለው በአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች፣ መንገዶችና ህንጻዎች ላይ የተለያዩ የስዕል ስራዎችን በመስራት የሚታወቀውና በአሁኑ ጊዜም በመስራት ላይ የሚገኘው ሰዓሊ ቢኒያም አበበ፣ አንድ ስዕል ከብዙ ገጽ መጽሐፍ በላይ የሕዝቦችን በአብሮነት የተሞላ ህይወት ይገልጣል። ሰዎችን ስለአንድነትና አብሮነት ያስገነዝባል፡፡
ይህን የተገነዘቡ ሀገራት በስዕል አንድነትን ሰብከዋል፡፡ አብሮነትን አስተምረዋል፡፡ ማህበረሰብን ለልማት አነሳስተዋል፡፡ ልማትን አፋጥነዋል፡፡ ሀገራዊ ትርክትም እየገነቡበት ይገኛሉ፡፡
ሌሎች ሀገራት ስዕልን ለጋራ ትርክትና ለአብሮነት ግንባታ በስፋት ተጠቅመውበታል። ዲቦራ ገስትሊን የተባሉ የዘርፉ ባለሙያ “Mexican Murals and Social Art” በሚል እ.ኤ.አ በ2024 ለንባብ ባበቁት ጽሑፍ ላይ እንደገለጹት፣ ሜክሲኮ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ከረጅም የእርስ በርስ ግጭት በኋላ ብሔራዊ ማንነቷን እንደገና ለመገንባት የስዕል ጥበብን በስፋት ተጠቅማለች፡፡
እንደ ዲያጎ ሪቬራ ያሉ ታላላቅ ሰዓሊዎች በትምህርት ቤቶች፣ በመንግስት ህንፃዎች እና በህዝባዊ ቦታዎች ላይ ግዙፍ ስዕሎችን ሰርተዋል። እነዚህ ስዕሎች አብሮነትንና አንድነትን የሚያሳዩ የጋራ ትርክትን የሚገነቡና ለብሔራዊ ጥቅም በጋራ መቆምንም የሚያስተምሩ ነበሩ። ስዕሎቹ የሜክሲኮን ጥንታዊ ታሪክ፣ የአብዮቱን ሂደት፣ የገበሬዎችን ሕይወት እና የሀገሪቱን ብዝሃነት ያሳዩ ነበር። ይህም የብሔራዊ ኩራትና የመግባባት ስሜት ተጠናክሮ የጋራ ሀገራዊ ትርክት እንዲገነባ አድርጓል።
ለአብሮነትና አንድነት፣ ለጋራ ትርክትና ለብሔራዊ ጥቅም በጋራ መቆምን በስዕል አማካኝነት ግንዛቤ ፈጥሮ ውጤታማ ከሆኑ ሀገራት መካከል ደቡብ አፍሪካና ጀርመን ዋነኛ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ዓለም አቀፍ ልምዶችና ተሞክሮዎች ለሀገራችን ትልቅ ትምህርት ሰጪ ናቸው። ኢትዮጵያ በታሪክ የበለጸገች፣ በባህል የረቀቀችና በሥነ- ስዕል ጥበብ ጥንታዊና ዘመናዊ ቅርሶች ያሏት ሀገር ነች። ይህንን ውድ ሀብት ለጋራ የሀገር ትርክትና አብሮነት ለመጠቀም ከላይ በተጠቀሱት ሀገራት ልምዶች በመነሳት ተጠቃሚ መሆን ትችላለች፡፡ የሰዓሊ ቢኒያም አስተያየትም ይህን የሚያጠናክር ነው፡፡
እንደ ሰዓሊ ቢኒያም ገለጻ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ ብራዚልና ሜክሲኮ “Mural Art” የተባለው የአሳሳል ዘዴ ለአንድነት፣ ለአብሮነትና ለጋራ ትርክት ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ ኢትዮጵያም የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሀገር እንደመሆኗ የተለያዩ ጸጋዎችን በስዕል በማንጸባረቅ አብሮነትን ማጠናከር ይቻላል፡፡ ይህም ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ፣ በውበት የታጀበና እያዝናና የሚያስተምር ብሎም ኢትዮጵያዊ አንድነትን የሚያጠናክር ይሆናል፡፡
ከአርታዊ ጋለሪ መስራቾች ከሆኑት አንዱ የሆነው አብነት ተሾመ ከዚህ ቀደም ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በሰጠው አስተያየት፣ “ወደ ጀርመን ባቀናሁበት ወቅት በአንድ ትንሽ ከተማ በርካታ የስዕልና የፎቶግራፍ ማሳያ ማዕከላት መኖራቸውን አይቻለሁ፡፡ ጀርመኖች ስዕልን ለስራ ፈጠራ፣ ለገጽታ ግንባታ፣ ለአብሮነትና ለባህል እድገት፣ ስልጣኔን እና የውጭ ምንዛሬን ለማግኘት ተጠቅመውበታል፡፡ እኛም ከእነሱ ብዙ የምንማረው ነገር አለ” በማለት ልምዱን አጋርቶን ነበር፡፡
የኢትዮጵያን የብዝሃነት ውበት፣ የጋራ ድሎች (እንደ የዓድዋ ድል እና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ)፣ የሁሉም ክልል ህዝቦች የጋራ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶችን የሚያንጸባርቁ ግዙፍ የሕዝብ ስዕሎችን በየክልሉ ዋና ከተሞች፣ አደባባዮችና በትላልቅ የመንግስት ህንፃዎች ላይ እንዲሰሩ በማድረግ አብሮነትን ማጉላትና የጋራ ትርክትን መገንባት ይቻላል።
ስዕልን በቀላሉ ከመሳል አልፎ የሀሳብ መግለጫና የትንታኔ መሳሪያ እንዲሆን በማድረግ የትምህርት ቤቶች ሥርዓተ-ትምህርት ውስጥ ማካተት አስፈላጊ መሆኑ ይነሳል። ይህም አስተሳሰብን የማስፋትና የፈጠራን አቅም የማጎልበት ፋይዳ አለው። የስነ-ስዕል ተማሪዎች የሀገሪቱን ባህላዊ፣ ኃይማኖታዊና ዘመናዊ የስዕል ዘይቤዎች ጠልቀው እንዲያውቁ እና በዘመናዊ ስራዎቻቸው ውስጥ አብሮነትን፣ የጋራ ታሪክና ትርክትን እንዲጠቀሙ ማበረታታት የሚለውም ዋነኛው ጉዳይ ነው፡፡
በተጨማሪም የግልና የመንግስት ጋለሪዎችን ቁጥርና ጥራት በማሳደግ ሰዓሊዎች አብሮነትን የተመለከቱ ስራዎቻቸውን ለብዙሃኑ እንዲያቀርቡ ዕድል መፍጠር እና በቱሪዝም ዘርፍ ውስጥ የኪነ-ጥበብ ስራዎችን ግብይት በማበረታታት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን ማሳደግ ሀገሪቱ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን ያስችላታል፡፡
“በተለይ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ ብዙ ባህል እና ቋንቋዎች የሚገኙባት ከተማ ነች፡፡ ከተማዋ በስዕል ትዕይንት አብሮነትን ማጉላት አለባት። የአንድነት መልክንም ልታንጸባርቅ ይገባል፡፡ የስዕል ጥበብ ከተማዋን የሰላም፣ የመቻቻል፣ የአብሮነትና የአንድነት መገለጫ ሊያደርጋት ይገባል” ሲል ሰዓሊ ቢኒያም ያብራራል፡፡
ቢኒያም እንደሚለው፣ ሰዓሊዎች ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ማኅበራዊ ፋይዳን የሚያንፀባርቁ ስዕሎችን መስራት አለባቸው። ለምሳሌ፦ የዓድዋ ሙዚየምን ጨምሮ የዓድዋን ጦርነት መንፈስ፣ ጀግንነትና አንድነት የሚያሳዩ ስራዎች ሊሠሩ ይችላሉ። እንደዚህ አይነት ስራዎች የጋራ አብሮነትን ከፍ በማድረግ ረገድ የማይተካ ሚና አላቸው፡፡
በአጠቃላይ ስዕል ከውበት ያለፈ፣ የሀገርን ሕልውና፣ አብሮነትና የጋራ ዕድገት የሚደግፍ ስልታዊ መሳሪያ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ ትርክት በብዝሃነታቸው ውበትና በመቻቻላቸው ታሪክ ላይ የተመሰረተ ነው። ሥነ-ስዕል ይህንን ታሪክና ብዝሃነት በምስል በማቅረብ፣ በአድማስና ቀለማት ልዩነት ስር ያለውን አንድ የጋራ መልክ ለማየት ያስችላል።
ኢትዮጵያም ከሜክሲኮ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ጀርመን ልምድ በመማር፣ ጥበብን ከመንግሥት እስከ ኅብረተሰብ ባሉ ተቋማት ውስጥ ስልታዊ በሆነ መንገድ መተግበር አለባት። የጋራ አብሮነትን የሚተርኩ የስዕል ፕሮጀክቶች መጀመር፣ የኪነ ጥበብ ትምህርትን ማጠናከር እና ለባለሙያዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠር የዛሬ ተግባራት መሆን አለባቸው።
የኢትዮጵያ ነገ የሚገነባው የጋራ ታሪኳንና ተስፋዋን በሚያንጸባርቅ አንድ የጋራ ትርክትና አብሮነት ላይ ነው። ይህ ትርክት ደግሞ በብሩሽና በቀለም ተመስሎ፣ በአደባባይ ተሰቅሎ፣ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ልብና አይን እንዲደርስ በማድረግ ማጠናከር ይቻላል። በስዕል የሚገለጽ አብሮነት ለጠንካራ፣ ለሰላማዊና ለበለጸገች ኢትዮጵያ መሠረት መሆን ይችላል፡፡
ምክንያቱም ስዕሎች የሀገርን አንድነት፣ የቴክኖሎጂ ዕድገት፣ የከተሜነት መስፋፋትና የማህበራዊ ለውጦችን በማንፀባረቅ ስለ ሀገሪቱ የወደፊት አቅጣጫ ፍንጭ ይሰጣሉ። ኢትዮጵያም በስዕል ጥበብ ቀደምት ከሚባሉና ራሳቸውን በአብሮነት ውበት፣ ለዓለም በስዕል መግለጥ ከሚችሉ ሀገራት መካከል ተጠቃሽ ነች፡፡
በጊዜው አማረ