ከሸማችነት ወደ አምራችነት

You are currently viewing ከሸማችነት ወደ አምራችነት

• በከተማዋ በግቢና በጓሮ አትክልት ልማት 625 ሺህ 725 ተጠቃሚዎች የተሰማሩ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት በጓሮ አትክልት 20 ሺህ 790 ቶን እንዲሁም በማሳ አትክልት ደግሞ  46 ሺህ 160 ቶን ምርት ይገኛል ተብሏል

አቶ አረጋ ታደሰ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ነዋሪ ናቸው፤ የአካል ጉዳተኝነት ሳይበግራቸው በዶሮ እርባታ ስራ ተሰማርተው ውጤታማ ሆነዋል፡፡ እኒህ አባት በመኖሪያ ቤታቸው ባለቻቸው ውስን ቦታ የዶሮ ኬጂዎችን በማዘጋጀት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ኑሮአቸውን አሻሽለዋል፡፡

ዶሮ የማርባት የቆየ ፍላጎት እንደነበራቸው የሚያስታውሱት አቶ አረጋ ከሚያውቋቸው ደጋግ ሰዎችና ቤተሰቦቻቸው ባገኙት የገንዘብ ድጋፍ የመኖሪያ ቤታቸውን ከፍለው የዶሮ ቤት (ኬጅ) በመስራት የጀመሩት ስራ፣ የጉለሌ ክፍለ ከተማ አርሶ አደርና የከተማ ግብርና ጽህፈት ቤት ባደረገላቸው የ65 እንቁላል ጣይ ዶሮዎች ድጋፍ የበለጠ እንደተጠናከረላቸው ተናግረዋል፡፡

በጀመሩት የዶሮ እርባታ ስራ ውጤታማ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ አረጋ፣ በየቀኑ ከሚያገኙት 55 እንቁላሎች የተወሰኑትን ለቤት ውስጥ ፍጆታ በማዋል ቀሪዎቹን ለገበያ ያቀርባሉ፤ አንዱን እንቁላል በ17 ብር ሂሳብ በመሸጥ ኑሮአቸውን መደጎም መቻላቸውን ገልፀውልናል፡፡

ሆኖም የዶሮ መኖ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመሩ በስራቸው ላይ እንቅፋት እንደሆነባቸው አቶ አረጋ ገልፀው፣ ለቀጣይም የዶሮ እርባታ ስራቸውን በማስፋፋት ከዘርፉ ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን ጠንክረው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

በተመሳሳይ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 በተለምዶ ቀጨኔ ተብሎ የሚጠራ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ወይንሸት ሰብስቤ የወተት ላሞችን በማርባት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ የወተት ላሞችን ማርባት ከ30 ዓመት በፊት እንደጀመሩ የሚጠቁሙት ወይዘሮ ወይንሸት ስራውን በተደራጀ መንገድ መስራት የጀመሩት ግን ከሁለት ዓመት በፊት በተጀመረው የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም አማካኝነት ነው፡፡

ወይዘሮ ወይንሸት አሁን 30 የወተት ላሞች እንዳሏቸው ገልፀው፣ በግላቸው ተጠቃሚ ከመሆን አልፈው ለሶስት ወጣቶችም የስራ እድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል፡፡

በከተማ ደረጃ ዘርፉን በተደራጀ እና በዘመናዊ መንገድ በመስራታቸው እውቅና ማግኘታቸውን ወይዘሮ ወይንሸት ጠቁመው፣ በአንድ ቀን እስከ 150 ሊትር የወተት ምርት ያገኛሉ፡፡

ወይዘሮ ወይንሸት ወተት እና የወተት ተዋጽኦ ከሀገር ውስጥ ገበያ ባለፈ ለውጭ ገበያ ያቀርባሉ፡፡ በዚህም በወተት እና ወተት ተዋጽኦ ሽያጭ ገቢያቸውን ማሳደግ መቻላቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከላሞች የሚወጣውን ተረፈ ምርት ለባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ በማዋል ለምግብ ማብሰያነት ይጠቀማሉ፡፡ የወተት ልማት ዘርፉን ደስተኛ ሆነው እና በፍላጎታቸው የሚሰሩት ወይዘሮ ወይንሸት የመስሪያ ቦታ እጥረት እንዲሁም በየጊዜው የመኖ ዋጋ መጨመር በስራቸው ላይ ፈተና እንደሆነባቸው ሳይገልፁ አላለፉም፡፡

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 የሚገኘው ‘ዓለማችን የካቶሊክ የአካል ጉዳተኛ ህጻናት ማገገሚያ ማዕከል’ ደግሞ በግቢው የሚገኙ አካል ጉዳተኛ ህጻናት የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ባላቸው ትርፍ ቦታ የተቀናጀ የከተማ ግብርና የእጽዋት እና የእንስሳት እርባታ በማከናወን ለምግብ ፍጆታነት ያውላሉ።

በማዕከሉ 300 ዶሮዎችን በማርባት በቀን 300 እንቁላል በማግኘት ለህጻናት ምግብነት ያውላሉ፡፡ በቀጣይ በተቀናጀ የከተማ ግብርና ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን የተጀመሩ ስራዎችን ይበልጥ በማጠናከር እንዲሁም በበግ ማድለብ ስራ ዘርፍ እንደሚሰማሩ  አስታውቀዋል።

የከተማ ግብርና በከተሞች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረግ ወሳኝ ጥረት ነው፡፡ ይህ ዘርፍ በውስን ቦታ ላይ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚከናወን ሲሆን፣ የእንስሳት፣ የዶሮ፣ የዓሳ እርባታ፣ ንብ ማነብ፣ ወተትና የወተት ተዋፅኦ ምርትን፣ ፍራፍሬ፣ የጓሮ አትክልት ማምረት እና የተመረቱ ምርቶችን ማቀነባበርንም እንደሚያካትት እሙን ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በከተማ ግብርና የሚያገኙትን ምርት ለቤት ፍጆታ ከማዋል ባሻገር ለገበያ በማቅረብ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ማግኘት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ የግብርና ምርትና ምርታማነት በመጠንና በጥራት በማሳደግ ኢኮኖሚን በማሻሻል በከተማና በከተማ ዙሪያ የሚኖረው የህብረተሰብ ክፍል የምግብ ዋስትና እንዲሻሻል እያደረገ ያለ ዘርፍም ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች በዶሮና በወተት ልማት፣ በከብት ማድለብ፣ በንብ ማነብ፣ በሰብል እና በሌሎችም ዘርፎች ተሰማርተው ውጤታማ እየሆኑ መጥተዋል። ነዋሪዎች በመኖሪያ ቤት ቅጥር ግቢ፣ ትምህርት ቤትን ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት የጓሮ አትክልቶችን በመትከል የምግብ ፍጆታቸውን በመሸፈን እንዲሁም የስራ ዕድል እየፈጠሩ ነው፡፡

በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 4 አስተዳደር የእንስሳት ሃብት ልማት ባለሙያ አቶ ጌታሁን ጉተታ በወረዳው የተቀናጀ የከተማ ግብርና ተግባራዊ እንዲሆን ሙያዊ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸው፣ በዘርፉ የተሰማሩት ውጤታማ እንዲሆኑ የቅርብ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ የተቀናጀ የከተማ ግብርና ተሳታፊዎች የተሻሻሉ ዝርያዎችን እንዲጠቀሙና ህክምና እንዲያገኙ ያደርጋሉ፡፡

ባለሙያው ለተጠቃሚዎች የህክምናና የተሻሻሉ ዝርያዎችን በአግባቡ እንዲጠቀሙ የቅርብ ሙያዊ ድጋፍ በማድረጋቸውም ተጠቃሚዎች የሚያገኙት ምርት እያደገ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ የተመጣጠነ መኖ በተመጣጣኝ ዋጋ ገዝተው እንዲጠቀሙ የገበያ ትስስር መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡

በጉለሌ ክፍለ ከተማ የአርሶ አደርና የከተማ ግብርና ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሳልፋኮ ሻኖ የመኖሪያ ግቢ እና ክፍት ሰፋፊ ቦታ ያላቸው ተቋማት እና ነዋሪዎች በተቀናጀ የከተማ ግብርና እንዲሳተፉ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በክፍለ ከተማው የተቀናጀ የከተማ ግብርና በመንግስት እና በግል ተቋማት እንዲሁም በትምህርት ቤቶች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ ነው። በእንጦጦ አምባ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዶሮ እርባታ፣ የጓሮ አትክልት፣ እንዲሁም በመድሐኒዓለም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደግሞ የበግ እና የዶሮ እርባታ እንዲሁም የጓሮ አትክልት በመትከል ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከትምህርት ቤቶች በተጨማሪ በጤና ተቋማት የተቀናጀ የከተማ ግብርና ስራ በመስራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን አቶ ሳልፋኮ ጠቅሰው፣ በእንጦጦ የተቀናጀ የመኖሪያ መንደር ሼድ በመገንባት 40 ወጣቶችን በማደራጀት በወተት ላም እና በጓሮ አትክልት ልማት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡

የተቀናጀ የከተማ ግብርና ስራ በክፍለ ከተማው ውጤታማ እንዲሆን ብድር ማመቻቸት፣ የምርጥ ዘር፣ የመስሪያ ቦታ አቅርቦት፣ የመኖ ትስስር፣ የባለሙያ ድጋፍ፣ የህክምና እና የገበያ ትስስር ድጋፎች በማድረግ ላይ መሆናቸውን አቶ ሳልፋኮ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም በክፍለ ከተማው የተቀናጀ የከተማ ግብርና ስራን አጠናክሮ ለማስቀጠል የ90 ቀናት እቅድ ከወዲሁ በማቀድ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ በከተማ ግብርና በሌማት ትሩፋት እየተሰሩ ያሉ የተቀናጀ የከተማ ግብርና ስራዎች ውጤታማ መሆን ችለዋል፡፡ አዲስ አበባ ላይ የከተማ ግብርና ስራ አይቻልም የሚለው አመለካከት መቀየሩን እና የነዋሪዎች የይቻላል አስተሳሰብ በተግባር የተረጋገጠ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

በጉለሌ ክፍለ ከተማ በተቀናጀ የከተማ ግብርና ስራ በእንስሳት ዘርፍ 23 ሺህ 474 ተሳታፊዎች መሰማራታቸውን የጽህፈት ቤቱ መረጃ ያመላክታል። በመረጃው መሠረት፣ በእንቁላል ጣይ ዶሮዎች 22 ሺህ 678 ተሳታፊ ግለሰቦች የተሳተፉ ሲሆን፣ በቀን 18 ሺህ 142 እንቁላል ይመረታል፡፡ በወተት ከብት ደግሞ 280 ተሳታፊዎች አሉ፡፡ በዚህም በቀን 9 ሺህ 360 ሊትር ወተት ይመረታል፡፡ በጓሮ አትክልት ልማት 41 ሺህ 416 ተሳታፊዎች ተሰማርተዋል። በዚህም በቀን በአማካይ 1 ነጥብ 1 ቶን ምርት ይገኛል፡፡ በክፍለ ከተማው በቀጣይ በጓሮ አትክልት ምርት ከ1 ሺህ 377 ቶን በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በተቀናጀ የከተማ ግብርና ስራ በእንስሳት ዘርፍ 423 ሺህ 113 ተጠቃሚዎች እንደሚሳተፉ የከተማዋ አርሶ አደርና የከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን መረጃ ያመላክታል። በመረጃው መሠረት፣ በእንቁላል ጣይ ዶሮዎች 414 ሺህ 892 ግለሰቦች  የሚሳተፉ ሲሆን፣ በ2017 ዓ.ም ብቻ 820 ሚሊዮን 58 ሺህ 469 የእንቁላል ምርት ተገኝቷል፡፡

በስጋ ዶሮ 1 ሺህ 174 ነዋሪዎች ተሳታፊ ሲሆኑ፣ 8 ሺህ 531 ቶን የዶሮ ስጋ ምርት ተገኝቷል፡፡ በተያዘው ዓመትም 10 ሺህ 665 ቶን የዶሮ ስጋ ምርት እንደሚገኝ ከወዲሁ ይጠበቃል፡፡

በወተት ከብት ደግሞ 5 ሺህ 246 ተሳታፊዎች አሉ፤ በ2017 ዓ.ም 70 ሚሊዮን 869 ሺህ 552 ሊትር ወተት ምርት ተገኝቷል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመትም 99 ሚሊዮን 217 ሺህ 372 ሊትር ወተት ምርት እንደሚገኝ የከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን መረጃ ያሳያል፡፡

በግቢና በጓሮ አትክልት ልማት 625 ሺህ 725 ተጠቃሚዎች ተሰማርተዋል፤ ከጓሮ አትክልት 20 ሺህ 790 ቶን ምርት ተገኝቷል፡፡ በዚህ ዓመት በከተማዋ በጓሮ አትክልት ምርት 20 ሺህ 790 ቶን እንዲሁም በማሳ አትክልት ደግሞ 46 ሺህ 160 ቶን ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በይግለጡ ጓዴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review