የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ለማበረታታት የሀገርን እንወቅ ክበቦች እየተጠናከሩ ነው

You are currently viewing የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ለማበረታታት የሀገርን እንወቅ ክበቦች እየተጠናከሩ ነው

‎AMN ህዳር 6/2018 ዓ.ም

‎የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቱሪዝም ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 89/2017 ራሱን ችሎ እንዲዋቀር በአዲስ አበባ ም/ቤት ፀድቆ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል።

‎ይህንንም ተከትሎ ኮሚሽኑ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማሳደግ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል።

‎በአዲስ አበባ ከተማ የውጭ አገር የጎብኚዎችን ቁጥር እንዲጨምር ከሚሰራው ስራዎች ጎን ለጎን የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራቶችን እየከናወነ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሁንዴ ከበደ ለኤ ኤም ኤን ዲጅታል ገልፀዋል።

‎የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማሳደግ ጉብኝት ባህል ለማድረግ በተለያዩ የትምህርት ተቋማት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ተጠናክረው መቀጠላቸውን ኮሚሽነሩ ገልፀዋል ።

‎በተለይም ዜጎች ሀገርን የማወቅ ጉጉት እንዲያድርባቸው ለማድረግ የሀገርህን እወቅ ክበብ እንዲቋቋሙ እና እንዲጠናከሩ ኮሚሽኑ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አቶ ሁንዴ ተናግረዋል።

የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ማበረታታት ይቻል ዘንድ የህግ ማዕቀፍ በደንብ ደረጃ መዘጋጀቱን ተናግረዋል ።

‎ኮሚሽኑ በከተማዋ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለቀጣይ አስር ዓመት የሚተገበር የቱሪዝም ልማት ስትራቴጂ መቅረፁን ነው አቶ ሁንዴ የገለፁት ።

‎የከተማዋን የቱሪዝም ሀብት የሆኑ ስፍራዎች የሚተዋወቁበት እንዲሁም የሚሸጥበት የማርኬቲንግ እና የፕሮሞሽን ስትራቴጂ ቀርፆ ወደ ስራ መገባቱን ገልፀው ፣ ለዚህ ስራ የሚያገለግሉ መረጃ ሰጪ ድረ ገፆችን መልማቱን ተናግረዋል።

‎ከዚህ በተጨማሪ ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ 376,615 የውጪ አገር ቱሪስቶች ከተማዋን የጎበኙ ሲሆን ከዚህም 61.6 ቢሊዮን ብር ወደ ኢኮኖሚው ፈሰስ መደረጉን አመላክተዋል ።

‎ኮሚሽኑ ራሱን ችሎ ወደ ስራ መግባቱን ተከትሎ በቱሪዝሙ በርካታ ለውጦችን ያስመዘገበ ሲሆን አዲስ አበባን የቱሪዝም መዳረሻና የዓለም ዓቀፍ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን እና ውጤት መመዝገባቸውንም ኮሚሽነሩ ገልፀዋል ፡፡

የኮሚሽኑ ያዘጋጀውን አዲስ የኮርፖሬት ሎጎ በባለድርሻ አካላት እንዲገመገምና አስተያየት እንዲሰጥበት በማድረግ ይፋ ማድረጉንም አቶ ሁንዴ ከበደ ገልፀዋል ፡፡

‎በሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review