የህዝብ ተወካዮች የሰው ሃብት ልማት ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የትምህርት ዘርፉን የ1ኛ ሩብ ዓመት ሥራ አፈፃፀም ተመልክቷል።
በዚሁ ጊዜ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በከፍተኛ ትምህር ተቋማት የክብር ዶክትሬት አሰጣጥን በተመለከተ ችግር የነበረበት በመሆኑ ወጥ አሰራር መከተል በማስፈለጉ የክብር ዶክትሬት አሰጣጥን ሀገራዊ መመሪያ ተዘጋጅቶ ለትግበራ ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል።
ሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም በመመሪያው መሰረት ተፈፃሚ ማድረግ ያለባቸው ሲሆን የክብር ዶክትሬት ማዕረግ የሚያገኙ ሰዎች ዶክተር ወይንም የክብር ዶክተር በሚል መጠሪያነት መጠቀም እንደማይቻል አሳስበዋል።
የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የክብር ዶክትሬት ማዕረግ ለመስጠት ሀገራዊ እና አለም አቀፍ መስፈርቶችን ማሟላት እንዳለባቸው በመመሪያ መመላከቱን ያነሱት ክቡር ሚኒስትሩ፤
በሙያው የተለየ ስራ ያበረከተ ኢትዮጵያዊም ሆነ ሌላ ዜጋ በመመሪያው የተዘረዘረውን መስፈርት የሚያሟላ ከሆነ የክብር ዶክትሬት ማዓረግ ማግኘት እንደሚችል ጠቅሰው ይሁን እንጂ የተሠጠውን የክብር ዶክትሬት ለመጠሪያነት መጠቀም እንደማይቻል አብራርተዋል።
ትምህርት ሚኒስቴር የክብር ዶክትሬት መስጠት የሚችሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በተመለከተ እንዲሁም የክብር ዶክትሬት የተሰጠው ግለሰብ ዶክተር፣ የክብር ዶክተር እና መሰል መጠሪያዎችን በየትኛውም ግለሰብ ወይም ድርጅት መጠቀም እንደማይችል መመሪያ አዘጋጅቶ ለሚመለከታቸው መላኩ ይታወቃል።