ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ ያደረጉት የ5 ሚሊየን የኮደርስ ስልጠና እየተተገበረ ይገኛል፡፡ በዚህም በርካታ ዜጎች ስልጠናውን በመውሰድ ወደ ስራ መግባታቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የኮደርስ ስልጠና በተለይ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎትን ተደራሽ እንዲያደርጉ በማስቻል ረገድ ሚናው ላቅ ያለ ነው፡፡
ይህንን መሰረት በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ ተግባራዊ የተደረገው የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል የሚሰጠውን አገልግሎት ዘመናዊና ከእጅ ንክኪ የፀዳ ለማድረግ በስነ-ምግባር እና በሞያ የበቁ ባለሞያዎችን ይዞ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል፡፡
በአዲስ ሞሰብ አንድ ማዕከል ከ18 በላይ የከተማ አስተዳደሩ ተቋማት አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ የማዕከሉ ባለሞያዎችምን በሙያና በክህሎት ብቁ ለማድረግ ወቅቱን የዋጀ ስልጠና እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል፡፡
በዚህ መሰረት የኮደርስ ስልጠና ሲከታተሉ ለነበሩ 151 ሰራተኞች የሰርተፊኬት የምረቃ እና የዕውቅና መርሃ ግብር ተካሂዷል ፡፡ በመርሃ ግብሩ የስራ ስምሪት እና መልእክት ያስተላለፉት የአዲስ መሶብ አንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናሰ አለማየሁ፣ ተመራቂዎች የወሰዱትን ስልጠና ሕብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለመቅረፍ በተግባር ሊያወሉት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በዕውቅና መርሃ ግብሩ የከተማ አስተዳደሩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችም ተገኝተዋል፡፡
በያለው ጌታነህ