ኢትዮጵያውያን ታላቁን የአፍሪካ ግድብ ያለምንም የውጭ እርዳታ እውን በማድረግ ታሪክ ሰርተዋል ሲል ጋናዊው ዩቱበር ዎዴ ማያ ገለጸ።
በማህበራዊ ትስስር ገጾች በተለይም በዪቱብ ስራዎቹ አለም ላይ በመዘዋወር የተለያዩ ፕሮግራሞችን በመስራት የሚታወቀው ጋናዊው ዎዴ ማያ፣ታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ በመጎብኘት ዘጋቢ ፊልም አሰናድቷል።
በፕሮጀክቱ አጠቃላይ ስራ እጅግ መደመሙን የገለጸው ዎዴ ማያ፤ታላቁ የህዳሴ ግድብን ሰርቶ ለማጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን ያሳዩት አንድነት ለመላው አፍሪካ ትልቅ ትምህርት ነው ይላል።
ኢትዮጵያውያን ያለ ምንም የውጭ እርዳታ እንዴት ታላቁን የአፍሪካ ግድብ ገነቡ? የሚለው ጥያቄም አንድ ሀገር ያለውን ሀብት በአግባቡ ከተጠቀመ ታሪክ መስራት እንደሚችል ይህ ግድብ ማሳያ ነው ብሏል።

በመሆኑም አፍሪካውያን ያለንን ሀብት ለሀገራዊ እድገት እና ብልጽግና በአግባቡ ከተጠቀምን ተራራ ማንቀሳቀስ እንችላለን በማለት አስረድቷል።
ኢትዮጵያውያን የገነቡት ይህ ግድብ በአህጉሪቱ ግዙፍ እና በአፍሪካውያን ዘንድም እንደ ልህቀት የሚታይ ፕሮጀክት መሆኑን ነው የገለጸው።
እንደ አንድ አፍሪካዊ ይህንን በማየቴ ኩራት ተሰምቶኛል የሚለው ዎዴ ማያ፤ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁሉም አፍሪካዊ ሊያየው የሚገባ ፓን አፍሪካዊ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጿል።
እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አሻራውን ያሳረፈበት መሆኑን ገልጾ፥ አፍሪካዊያንም ከውጭ እርዳታ ሳንጠብቅ በትብብርና በጋራ ከሰራን አህጉራችንን ማበልጸግ እንችላለን ሲልም ተናግሯል።
ዎዴ ማያ አክሎም፥ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ሁለተኛው ዓድዋ ነው ማለት ይቻላል ምክንያቱም በዓድዋ ጦርነት ወቅት ኢትዮጵያዊያን ተባብረው ጠላትን ድል እንዳደረጉት ሁሉ ይህ ፕሮጀክትም አፍሪካዊያን በምዕራባዊያን ላይ የነበራቸውን ጥገኝነት ያስቀረ እና በራስ አቅም የተሰራ ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑን መግለጹን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያውያን በጽናት በመቆም ተባብረው ታላቁን የአፍሪካ ግድብ ያለምንም የውጭ እርዳታ እውን በማድረግ ታሪክ መስራት መቻላቸውን መስክሯል።