ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቲዩት ሃገሪቱን በአለምአቀፍ የቴክኖሎጂ ውድድር በንቁነት መሳተፏን በሚያረጋግጥ መንገድ ከፍታ ላይ መድረሱን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልዕክት የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቲዩት ዋና ጽሕፈት ቤቱን ቀድሞ ከነበረበት በመለወጥ መሃል ከተማ ወደ ቀድሞው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ሕንፃ አዛውሯል።
በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ አስደናቂ የግንባታ ለውጥ እና ዘመናዊ የመሥሪያ ሥፍራ ጥበብን በማሳየት ለሠራተኞቹ እጅግ ምቹ የሆነ ስፍራንም መፍጠር ችሏል ብለዋል።

ተቋሙ በአምስት አመታት ጊዜ ውስጥ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ሕይወታችንን በፍጥነት በመቅረጽ ውስጥ ያለውን ስፍራ በሚያንፀባርቅ እና ሀገራችንም በዚህ አለምአቀፍ የቴክኖሎጂ ውድድር በንቁነት መሳተፏን በሚያረጋግጥ መንገድ ከፍታ ላይ ደርሷል ብለዋል።
ኢንስቲቲዩቱ በጤና፣ በግብርና፣ በአገልግሎት ዘርፍ እያደረገ ያለው የመሪነት አስተዋፅኦውን እየተወጣ ሲሆን በክላውድ ኮምፒውቲንግ፣ ትላልቅ የመረጃ ቋቶች፣ የመረጃ ፍለጋ፣ ሮቦቲክስ እና ኢመርሲቭ ቴክኖሎጂዎች አቅሙን በማጎልበት ላይ ይገኛል።
በቅርቡ የተጀመረው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ስታርት አፕ መዐከል ደግሞ ይኽንን ከባቢ የበለጠ ያጠናክረዋል ብለዋል።
ዜጎች ሀሳብ ብቻ ይዘው በመምጣት ፕሮቶታይፕ ለመፍጠር፣ ለማባዛት ብሎም ከግሉ ዘርፍ ኢንቬስተሮች ጋር እንዲገናኙ እድል ያመቻቻል።
እስከ አሁን 200 ሀሳብ ፈጣሪዎች በዚህ እድል ተጠቅመዋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።