በስራ ላይ ያሉ የደንብ ማስከበር ሰራተኞችን ፎቶ በማንሳት ያልተረጋገጡ መረጃዎችን የሚያጋሩ ግለሰቦች ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል

You are currently viewing በስራ ላይ ያሉ የደንብ ማስከበር ሰራተኞችን ፎቶ በማንሳት ያልተረጋገጡ መረጃዎችን የሚያጋሩ ግለሰቦች ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል

AMN ህዳር 8/2018

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን በመዲናዋ በመንግስትና በህዝብ ሀብት የተገነቡ መሠረተ ልማቶችን፣ የኮሪደርና የወንዝ ዳር ፕሮጀክቶችን ደህንነት በመጠበቅ እና እንዲጠበቁ በማድረግ ከከተማ አስተዳደሩና ከህዝብ የተሰጠዉን ሃላፊነት በመወጣት ላይ ይገኛል፡፤

ደንብ ተላልፈዉ በተገኙ ግለሰቦችና ተቋማት ላይም በተቀመጠዉ ደንብ መሰረት አግባብነት ያለዉና ሌሎችን ሊያስተምር የሚችል አስተዳደራዊ የቅጣት እርምጃዎችን በመዉሰድ ላይ ይገኛል፡፡

በተለይ አሽከርካሪዎች በመሰረተ ልማቶች ላይ ከሚፈጽሙት የደንብ ጥሰት ጋር በተያያዘ የባለስልጣኑ የደንብ ማስከበር ኦፊሰሮች አንድ ሾፌር በደንብ ቁጥር 167/2017 የተገለፁ ጥፋቶችን ፈጽሞ ከተገኘ ተገቢውን ቅጣት ሊቀጡት እንደሚችሉ በደንቡ ተጠቅሷል፡፡ ይህንን ደንብ አስመልክቶም ባለስልጣኑ በተለያዩ አግባቦች ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ተፈጥሯል፡፡

የተደነገገዉ ደንብ ይህንን ቢፈቅድም አንዳንድ ግለሰቦች ግን አግባብነት የሌለዉ ተግባር በመፈጸማቸዉ ምክንያት በህግ ተጠያቂ በመደረግ ላይ እንደሚገኙ ባለስልጣኑ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አስታዉቋል፡፡

ለአብነትም ከአሁን ቀደም በኮልፌ፣በየካ እና በቂርቆስ ክፍለ ከተሞች በስራ ላይ ያሉ ሰራተኞቹን ያለ-ፈቃድ ፎቶ በማንሳት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያጋሩ ግለሰቦች በወንጀል ተጠያቂ ተደርገዋል፡፡

ሌሎች ተመሳሳይ ድርጊት የፈፀሙ ግለሰቦችንም ከአዲስ አበባ እና ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመነጋገር መረጃ በማጣራት ላይ ይገኛል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ህዳር 5 ቀን 2018 ዓ.ም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በወረዳ 2 ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት ኦፊሰሮች ላይ አግባብነት የሌለዉ ድርጊት መፈጸሙን ባለስልጣኑ አስታዉቋል፡፡

ከላይ በተጠቀሰዉ እለት አንዲት አሽከርካሪ ከደምበል ወደ ቦሌ በሚወሰድው በኮሪደር ልማት በለማ የመናፈሻ ሳር ላይ በመኪና በመሄድና ጉዳት ታደርሳለች፡፡ ባለስልጣኑም ጥፋት የፈጸመችዉን አሽከርካሪ አምስት ሺ ብር በመቅጣት አስተዳደራዊ እርምጃ ይወስዳል፡፡

ጉዳት ያደረሰችው አሽከርካሪ በጊዜው ልጅ ታሞብኛል በማለት እዛው አከባቢ እንደምትሰራ ፤ ለጥፋቱም የሚቀጡትን ቅጣት ለመክፈል ፈቃደኛ መሆኗን በቦታው ተመድበው ለሚሰሩ የደንብ ማስከር ኦፊሰሮች ትገልጻለች፡፡

በዚህ መሃል ታዲያ ማንነቱ ያልታወቀ አንድ ግለሰብ የተቋሙን ገጽታ ለማጥፋትና የደንብ ማስከበር ስራውን ለማስተጓጎል ቪድዮ በመቅረጽ በማህበራዊ ሚዲያዎች ይለቃል፡፡

በማህበራዊ ሚዲያ የተለቀቀዉን ቪዲዮ የተመለከተዉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣንም በግለሰቡ የተፈጸመዉ ደርጊት የደንብ ማስከበር ስራውን ለማስተጓጎል የተፈጸመ በመሆኑ አግባብነት የለዉም ብሎታል፡፡

በከተማዋ ደንብ በሚተላለፉ ግለሰቦችና ተቋማት ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስታወቀዉ ባለስልጣኑ በማህበራዊ ሚዲያ የተቋሙን ስም የሚያጠለሽ ያልተረጋገጠ መረጃዎችን በማጋራት ህብረተሰቡን የሚያሳስቱ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስቧል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችም በከተማዋ ውስጥ በመንግስትና በህዝብ ሀብት የተገነቡ መሠረተ ልማቶችን፣ የኮሪደርና የወንዝ ዳር ፕሮጀክቶችን ደህንነት በመጠበቅ መገልገልና መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review