መንግስት ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ እና የሀገር ውስጥ ምርትን በበቂ ሁኔታ ለማሳደግ ተኪ ምርቶች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል።
አምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለኢትዮጵያ ፍላጎት በቂ ምርት የማቅረብ አቅምና ጸጋ እንዳለው በመገንዘብ የተቀረጸው የተኪ ምርት ስትራቴጂ ኢትዮጵያ ለገቢ ምርቶች የምታወጣውን ወጪ በመቀነስ በቢሊዮን ዶላር የሚገመት የውጭ ምንዛሪ እንድታድን አስችሏታል ።
እንደሀገር የገጠሙ የኢኮኖሚ ስብራቶችን ለመጠገን እና የኢንዱስትሪ ዘርፉን ችግሮች ለመፍታት በተወሰደው ቁርጠኛ ርምጃ ዘርፉ በ2017 በጀት ዓመት 13 ፐርሰንት ዕድገት እንዲያስመዘግብ ያስቻለ አንጸባራቂ ወጤት ማየት ተችሏል ።

እንደሀገር የዘረፉ መነቃቃት ክልሎች ያላቸውን ጸጋ በመግለጥ እና ለኢንቨስትመንት ምቹ ዐውድ በመፈጠር የኢትዮጵያ ብልፅግና የሚገለጥባቸው አገራዊ አቅም እንዲሆኑ አድርጓል ።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብቻ ከ271 በላይ ፕሮጀክቶች የሚገኙ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 131 የሚሆኑት በማኑፍክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ላይ የተሰማሩ ናቸው ።
በክልሉ ጉዙፍ የሚባለው ፕሮጀክት በምስራቅ ጉራጌ ዞን እየተገነባ የሚገኘው ቡል ኤሌፋንት ፋይበር ቦርድ ማኑፋክቸሪንግ ሲሆን ፕሮጀክቱ እንደ ኤም ዲ ኤፍ፣ ኤች ዲ ኤፍ እና ፋይቨር ውድ ያሉ ተኪ ምርቶችን ሙሉ በሙሉ በራስ ዐቅም በማምረት ኢትዮጵያን ከውጪ ምንዛሬ ወጪ የሚታደግ ነው።
በቻይናያዊያን ባለሀብቶች እየተገነባ የሚገኘው እና ከ50 ፐርሰንት በላይ የተጠናቀቀው ይህ ፕሮጀክት በአጠቃላይ ከ5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል አስመዝግቧል።
በግንባታው ሂደትም ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማስረጽ ከጅምሩ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል።