የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብሩ በዲፕሎማሲው ዘርፍም ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል

You are currently viewing የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብሩ በዲፕሎማሲው ዘርፍም ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል

AMN- ሕዳር 09/2018 ዓ.ም

ባለፉት ሰባት አመታት በተሰራው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በተፈጥሮ ሀብቶች ላይ ለውጦች ከመታየታቸው ባለፈ፣ በዲፕሎማሲው ዘርፍም ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና አጠቃቀም መሪ አስተዳደር አቶ ፋኖሴ መኮንን ተናገሩ፡፡

የሰዉ ልጆች በተፈጥሮ ሀብት ላይ ባደረሱት ጉዳት ተፈጥሮም በሰው ልጆች ላይ የራሷን ቅጣት አድርሳለች ያሉት አቶ ፋኖሴ፣ እንደ ድርቅ፣ የተፈጥሮ ሀብት መጎሳቆል፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የውሃ ችግር፣ የምርትና ምርታማነት መቀነስን ለአስረጅነት ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብም ይህን የተፈጥሮ አደጋ ለመቀነስ ባለፉት 7 አመታት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡

ከ2011 ዓ.ም እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ ባሉት ሰባት ተከታታይ አመታት በተከናወነ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 48 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል እንደተቻለ የጠቀሱት አቶ ፋኖሴ፣ በዚህም በርካታ ውጤቶች ተገኝተዋል ብለዋል፡፡

ለአብነትም የደን ሸፋን ጨምሯል፤ ተጎሳቁሎ የነበረው የተፈጥሮ ሀብት መልሶ ማገገም ጀምሯል፣ የስራ እድልን ፈጥሯል፤ የአፈር ደህንነትና ለምነት እንዲጨምር ሆኗል፤ ምርትና ምርታማነት አድርጓል፤ የጠፉ ምንጮችና ሀይቆች እንደገና መፍለቅ ጀምረዋል ብለዋል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ በአብዛኛው ትኩረት ተደርጎ እየተሰራባቸው የሚገኙ ተክሎች ለምግብነት የሚያገለግሉ፣ ወደ ውጪ ኤክስፖርት ሊደረጉ የሚችሉና ለእንሰሳት መኖነት የሚውሉ መሆናቸውንም አቶ ፋኖሴ ተናግረዋል፡፡

በዚህም መሰረት በመጀመሪያው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ የአቮካዶ ተክሎች አሁን ላይ ምርት መስጠት መጀመራቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ እያካሄደችው የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ፣ በዲፕሎማሲው ዘርፍም ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል ነው ያሉት አቶ ፋኖሴ፡፡

ኢትዮጵያ የኮፕ32 የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን እንድታዘጋጅ መመረጧ በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ያከናወነችው ተግባር ውጤት እንደሆነ ያመላከቱት አቶ ፋኖሴ፣ ይህም ኢትዮጵያን በማህበራዊው፣ በፖለቲካው እና በኢኮኖሚው ዘርፍ ከፍ ሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ኮፕ32ን እንድታዘጋጅ መመረጧ፣ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ላይ የነበረውን ተገቢ ያልሆነ ስም የሚቀይርና መልካም ገጽታዋን የሚገነባ እንደሆነም ነው አቶ ፋኖሴ ያስረዱት፡፡

በአስማረ መኮንን

#አዲስሚዲያኔትዎርክ

#addismedianetwork

#GreenLegacy

#Ethiopia

#addisababa

#climatechange

#ClimateAction

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review