የእንጉዳይ ምርትን በማላመድና በስፋት በማልማት በፕሮቲን የበለፀገ አማራጭ የምግብ አቅርቦትን ማሳደግ እንደሚቻል በመስኩ የተከናወነ ጥናት ያመላክታል።
የእንጨት ውጤቶች ያልሆኑ በደን ውስጥ ከሚገኙ የምርት አይነቶች ውስጥ አንዱ እንጉዳይ ሲሆን አስተማማኝ የምግብ ምንጭነት የሚያገለግል የእፅዋት ዝርያ ነው፡፡ የእንጉዳይ ዝርያዎች በውስጣቸው ፕሮቲኖች እና አስፈላጊ አሚኖ አሲዶችን በመያዛቸው ምክንያት ለምግብነት ጥቅማቸው ከፍ ያለ ግምት ይሰጣቸዋል።
እንጉዳይ የምግብ ዋስተና ለማገዝ በጠባብ ቦታዎች እና በየጓሮ በቀላሉ በማልማት የተመጣጠነ የምግብ ፍጆታን ለማሟላት የሚረዳ ነው፡፡ ይህንን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው የሚነገርለትን እንጉዳይን በአዲስ አበባ ከተማ ግብርና በአዲስ መልክ መስፋፋት ጀምሯል።
እንጉዳይ ለምግብነት፤ ለመድኃኒትነት፤ ለመሬት ለምነትና ለሌሎች እፅዋቶች ምርታማነት የሚያገልግል ሲሆን የእንጉዳይ ምርትን በማላመድና በማስፋፋት የምግብ አቅርቦትን ማሳደግ የሚያስችል እንደሆነ የአዲስ አበባ ከተማ ግብርና ሰርቶ ማሳያ ግብአት ብዜት ማዕከል ስራ አስኪያጅ አቶ አብደታ ደሜ ለ ኤ ኤም ኤን ተናግረዋል ።

ምርቱ በስፋት እንዲጠቀመው ለማድረግ ስለእንጉዳይ ጠቀሜታ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ስራ በአስራ አንዱም ክፍለከተማ እየተሰራ ይገኛል። እንጉዳይ ምርት በአነስተኛ ቦታ ላይ መስራት የሚያስችል የከተማ ግብርና ምርት ነው ያሉት አቶ አብደታ ፣ በሌሎች አገሮች የተለመደ ነገር ግን ለኢዮጰያውያን አዲስ መሆኑን አስረድተዋል ።
ምርቱ ለጤና የሚሆን የምግብ ይዘት እና ሌሎችም ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ እንደ አዲስ እያስተዋወቁት እንደሚገኙ ነው የተናገሩት ። እንጉዳይ የፈንገስ ዝርያ ሆኖ ለምግብነት የሚውል ሲሆን በውስጡ የምግብነት ይዘቱ ከፍተኛ እንደሆነ ነው የተናገሩት ።
ለምግብነት ሲባል ፕሮቲን፣ ማዕድናት ፣ ለጤና የሚጠቅሙ ይዘት ጭምር ያለው መሆኑን ገልፀዋል ። በአለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ዝርዎች ያሉት የእንጉዳይ ምርት ኦይስተር የተሰኘው የእንጉዳይ ዝርያ ለምግብነት ከሚውሉት ውስጥ ተጠቃሽ ነው።
ኦይስተር የእንጉዳይ ዝርያ በቀላሉ በትንሽ ቦታ በግብርና ተረፈ ምርቶች በመጠቀም በቀላሉ ማምረት እንደሚቻል ነው ዋና ስራ አስኪያጁ የተናገሩት ። ለጤና የሚሰጠው ጠቀሜታ ለተለያዩ የካንሰር አይነቶች ዜጎች እንዳይጋለጡ የሚያደርግ ሲሆን ግፊት፣ ስኳር ተጋላጭነት እንደሚቀንስ ነው የገለፁት።

እንጉዳይ ምርት የበሽታን መከላከል አቅምን ከፍ የሚያደርግ መሆኑን፣የሰውነት ክብደት እንዳይመጣ ለማድረግ የሚያግዝ ነው ብለዋል ። አቶ ነብዩ በቀለ የማዕከሉ የእንጉዳይ ላብራቶሪ ቴክኒሻን ነው ።
የከተማዋ ብቸኛ ላብራቶሪ በሆነው ማዕከል ለምግብነት ቢውል ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለውን የእንጉዳይ ለማምረት ወደ ዘርፉ የሚገቡ ባለሞያዎች ስልጠና እንደሚሰጡ ነው አቶ ነብዩ የተናገሩት ።
እንደ ሀገር በእንጉዳይ ምርት ላይ በሰፋት ያልተሰራበት ጠቃሚ ምርት ነው ያሉት አቶ ነብዩ፣ ለከተማ ግብርና በተሰጠው ትኩረት አማካይነት በመዲናዋ በሰፊው እየተሰራበት የሚገኝ አዋጭ ዘርፍ ሆኗል ብሏል።
በተለይ በውጨ አገሮች የተለመደው ኮሌስትሮል ያላቸው ምግቦችን ከተመገቡ በኋላ እንጉዳይን ይመገባሉ ያሉት አቶ ነብዩ ኮሌስትሮልን ይዞት ይወርዳል በማለት ጠቀሜታውን ይገልፃሉ ።
የእንጉዳይ ምርትን የውጭ አገር ተሞክሮው የሚያሳየው በሾርባ መልክ፣ በሻይ እና በሌሎች ምግቦች ላይ እንደሚጠቀሙት ተናግረዋል።
በኢትዮጰያ በአብዛኛው በበርገር ላየ ብቻ እንጉዳይን እንደሚጠቀሙ፣ ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች የምግብ አይነቶች ላይ ህብረተሰቡ እንዲጠቁ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት።
በሔለን ተስፋዬ