የአዲስ አበባ ከተማ ዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ በመዲናዋ ከህንጻዎችና ወንዞች የሚለቀቅ ፍሳሽን በማጣራት መልሶ መጠቀም የሚያስችል ቴክኖሎጂ ይፋ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
ቢሮው ዘመናዊ ፍሳሽ ማጣሪያ እና በከተማዋ የሚከናወኑ ግንባታዎች ጊዜንና ገንዘብ መቆጠብ የሚያስችሉ አማራጭ ቴክኖሎጂዎችን አስተዋውቋል።
ቢሮው የግንባታ ኢንዱስትሪውን ለማዘመን የሚያስችሉ አዳዲስ አማራጭ ቴክኖሎጂዎችን እንዲያጠናና እንዲተገብር በዓዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ከግንባታ ጥራትና ቅልጥፍና ጋር በተያያዘ ከቀረቡለት 16 አማራጭ ቴክኖሎጂዎች 3 በመምረጥ ይፋ አድርጓል።
አዋጭነታቸው ታምኖበት ልየታ የተደረገባቸውን ቴክኖሎጂዎችን ቢሮው በዛሬው ዕለት የኢንዱስትሪው ተዋንያን በተገኙበት አስተዋውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ ኃላፊ ኢ/ር አያልነሽ ሐብተማርያም በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት መዲናዋ የተያያዘቸውን እጅግ ፈጣንና ሰፊ የልማት እንቅስቃሴ የሚደግፍ ኢንዱስትሪ ዕውን ለማድረግ አሰራሮቻችንን ማዘመን እንዲሁም በአዳዲስ ዕሳቤዎች የተቃኘ ስርዓት መዘርጋት ጊዜ የማንሰጠው ተግባር ነው ብለዋል፡፡
ተግባሩን ተጨባጭ ለማድረግና ጊዜንና ገንዘብን በመቆጠብ ጥራት ያለው ስራ ለመስራት አማራጭ ቴክኖሎጂዎችን የማፈላለግና የማስረፅ ስራዎችን በስፋት ይሰራል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ይፉ የተደረጉት ቴክኖሎጂዎች ከህንጻና ወንዞች የሚለቀት የቆሻሻ ውሀ ማጣሪያና መልሶ መጠቀሚያ ቴክኖሎጂ እና የአልሙኒየም ፎርም ዎርክ ቴክኖሎጂ እንዲሁም ተንቀሳቃሽ መጸዳጃ ቤቶች ናቸው፡፡
ቴክኖሎጂዎቹ ጊዜንና ገንዘብ በመቆጠብ የመንግስትና ህዝብ ሀብት እንዲቆጠብ ከማድረግ ባለፈ ከተማዋ ዘመናዊ የፍሳሽ አወጋገድና የህንጻ ግንባታ አሰራር እንዲኖራት የሚያስችሉ መሆናቸው ተገልጿል።
ሌሎች የተመረጡ ቴክኖሎጂዎችም በዚሁ መልክ ከተዋወቁ በኋላ ወደ ኢንዱስትሪው የማስገባት ስራ እንደሚሰራ በመድረኩ ተመላክቷል፡፡
በአንዋር አህመድ