የተቋሙን ተልዕኮ በአግባቡ ለመፈፀምና የሚሰጡ አገልግሎቶችንም ለማዘምን የአመራሩንና የፈፃሚውን አቅም ማጎልበት አስፈላጊ ነው

You are currently viewing የተቋሙን ተልዕኮ በአግባቡ ለመፈፀምና የሚሰጡ አገልግሎቶችንም ለማዘምን የአመራሩንና የፈፃሚውን አቅም ማጎልበት አስፈላጊ ነው

AMN- ሕዳር 09/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር ለአመራሮቹ እና ለደንብ አስከባሪ ባለሙያዎች ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡

በስልጠና ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ፣ የተቋሙን ተልዕኮ በአግባቡ ለመፈፀምና የሚሰጡ አገልግሎቶችንም ለማዘምን የአመራሩንና የፈፃሚውን አቅም ማጎልበት አስፈላጊ መሆኑን ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል፡፡

ለረጅም ጊዜ በስራ ላይ የቆየውን የሰው ሀይል በማሰልጠንና በማብቃት ወቅቱ የሚፈቅደውን ስራ ለማሰራት ስልጠናው መሰጠቱ አስፈላጊ መሆኑንም ዋና ስራ አስኪያጁ አክለው ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ምክትል ሀላፊ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው በበኩላቸው፤ ሰልጣኖቹ በንድፈ ሀሳብ፣ በተግባር እና በቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት ያደረጉ ስልጠናዎችን እንደሚወስዱ ገልጸዋል፡፡

በስልጠናው 140 የሚሆኑ አመራሮች፣ 415 የሽፍት አስተባባሪዎችና መሪዎች እንዲሁም 5524 የሚደርሱ ባለሙያዎች በድምሩ 6079 ሰልጣኞች እንደሚሰለጥኑ አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ የአቅም ግንባታና ስልጠና መምሪያ ሀላፊ ኮማንደር ፈቃዱ ጌታቸው፣ ሰልጣኞቹ በስልጠና ቆይታቸው የአካል ብቃት፣ ስለ ሀገር መውደድ፣ የስነ ምግባር፣ እንዲሁም የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም ማጎልበቻ ክህሎት እንደሚያገኙ ጠቁመዋል፡፡

ሰልጣኞቹ በበኩላቸው፣ ከስልጠናው በኋላ ተቋማችን የሚሰጠንን ተልዕኮ በአግባቡ እንድንወጣና ለህብረተሰቡ የምንሰራቸውን አገልግሎቶችም መመሪያንና ደንብን መሰረት ባደረገ መልኩ እንድንሰራ ያስችለናል ብለዋል፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review