በአውሮፓ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ አምስት ሀገራት በቀጥታ ለማለፍ ይፋለማሉ

You are currently viewing በአውሮፓ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ አምስት ሀገራት በቀጥታ ለማለፍ ይፋለማሉ

AMN-ጥቅምት 9/2018 ዓ.ም

የአውሮፓ ሀገራት የዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጠናቀቃል፡፡ ዛሬ በሚከናወኑ ጨዋታዎች አምስት ሀገራት በቀጥታ ለማለፍ ይፋለማሉ፡፡

በምድብ ሁለት ስዊዘርላንድ ከሜዳዋ ውጪ ከኮሶቮ የምታደርገው ጨዋታ ይጠበቃል፡፡ ስዊዘርላንድ ምድቡን በ13 ነጥብ ስትመራ ኮሶቮ በ10 ትከተላለች፡፡

ስዊዘርላንድ ምድቧን በበላይነት አጠናቅቃ የዓለም ዋንጫ ተሳታፊነቷን ለማረጋገጥ አንድ ነጥብ በቂዋ ነው፡፡ ኮሶቮ በአንፃሩ ቀዳሚ ሆኖ በቀጥታ ለማለፍ ስዊዘርላንድን 6ለ0 ማሸነፍ ይጠበቅባታል፡፡

በምድብ ሦስት ስኮትላንድ ከዴንማርክ በሃምፕደን ፓርክ የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል፡፡ ዴንማርክ 11 ነጥብ ዛሬ በሜዳዋ የምትጫወተው ስኮትላንድ ደግሞ 10 ነጥብ ይዘዋል፡፡

ዴንማርክ አቻ ስኮትላንድ ደግሞ ማሸነፍ ዓለም ዋንጫ የመሳተፍ ህልማቸውን እውን ያደርግላቸዋል፡፡ ሁለቱ ሀገራት በመጀመሪያ ዙር ያደረጉት ጨዋታ 0ለ0 ነበር የተጠናቀቀው፡፡

በምድብ አምስት ስፔን ከቱርኪዬ ሌላው የምሽቱ ተጠባቂ ጨዋታ ነው፡፡ ስፔን በ15 ቱርኪዬ ደግሞ በ12 ነጥብ ቀዳሚውን ሁለት ደረጃ ይዘዋል፡፡

ስፔን 14 የግብ ክፍያ እና የሦስት ነጥብ ልዩነት በመያዟ በቀላሉ ታልፋለች የሚል ግምት ተሰጥቷታል፡፡ ሁለቱ ሀገራት በቱርኪዬ ያደረጉት የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ በስፔን 6ለ0 አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡

በምድብ ስምንት ኦስትሪያ ቦስኒያ ሄርዞጎቪናን ታስተናግዳለች፡፡ ሁለቱ ሀገራት በሁለት ነጥብ ብቻ በመለያየታቸው ጥሩ ፉክክር ይጠበቃል፡፡

በሜዳዋ ኤርነስት ሀፔል ስታዲየም የምትጫወተው ኦስትሪያ ምድቡን በ18 ነጥብ ስትመራ ቦስኒያ በ16 ትከተላለች፡፡

በምድብ 10 ቤልጂየም ከሊችተንስታይን ፤ ዌልስ ከሰሜን መቄዶንያ ይጫወታሉ፡፡ አስገራሚ ፉክክር እየታየበት የሚገኘው ይህ ምድብ ሦስት ሀገራትን በሁለት ነጠብ ብቻ ለይቷል፡፡

ቤልጂየም 15 ነጥብ ስትይዝ ሰሜን መቄዶንያ እና ዌልስ እያንዳንዳቸው 13 ነጥብ ሰብስበው የዛሬውን ጨዋታ እየተጠባበቁ ይገኛል፡፡ ሁሉም የዛሬ ጨዋታዎች ምሽት 4፡45 ሲል ይጀምራሉ፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review