በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተደረገ የግብርና ምርታማነትን የማሳደግ ንቅናቄ ወረዳዎች አዳዲስ ምርቶችን እያመረቱ ይገኛል ።
በክልሉ በተለያዩ ዞኖች የሚገኙ በርካታ ወረዳዎች ከዚህ በፊት የማያመርቷቸውን አዳዲስ የጥራጥሬ፣ የሰብል፣ የፍራፍሬ እና የእንስሳት ምርቶች በስፋት ወደ ማምረት ተሸጋግረዋል፡፡
መንግስት ግብርናን በማዘመን ምርታማነትን ለማሳደግ በሰጠው ልዩ ትኩረት የክልሉ ግብርና ቢሮ ለአካባቢው ሥነ ምህዳር ተስማሚ የሆኑ አዳዲስ ምርቶችን በጥናት በመለየትና ማስተዋወቅ በርካታ ወረዳዎች ከዚህ ቀደም የማያለሟቸውን ምርቶች ወደ ማልማት እንዲገቡ እና ምርታማ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል።
ጥሩ ተሞክሮዎች ወደ ሁሉም አካባቢዎች በፍጥነት እንዲስፋፉ በተሰራው የቅንጅት ሥራ ቀደም ሲል በሶስት ወረዳዎች ብቻ ይመረት የነበረው የሙዝ ተክል በአሁኑ ወቅት ወደ 16 ወረዳዎች እንዲስፋፋ እንዲሁም 24 ወረዳዎች ላይ ብቻ የነበረው ፓፓያ ምርት ከ44 ወረዳዎች በላይ እንዲያመርቱ እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተድርጓል።
በክልሉ በአቮካዶ ምርት ላይም የታየው ዕምርታ ክልሎች ጸጋቸውን በመለየት ለአካባቢያቸው ሥነምዳር ተስማሚ የሆኑ ምርቶች ላይ በማተኮር በአጭር ጊዜ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ያመላከተ ነው።
በክልሉ አደዲስ ምርቶችን በተናጥል ከማምረት ይልቅ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በቀላሉ ማሳደግ በሚቻልበት በኩታ ገጠም እርሻ መጠቀም መጀመሩ የአርሶ አደሩን ምርታማነትን የሚጨምር ከመሆኑም በላይ ለሌሎች አካባቢዎችም ማሳያ ሆኖ የሚቀርብ ተሞክሮ መሆኑን ከመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡