የማሌዢያ ኩባንያዎች የኢትዮጵያን የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎች የሚጠቀሙበት ምቹ ምኅዳር አለ ሲሉ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ

You are currently viewing የማሌዢያ ኩባንያዎች የኢትዮጵያን የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎች የሚጠቀሙበት ምቹ ምኅዳር አለ ሲሉ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ

AMN ህዳር 10/2018

የማሌዢያ ኩባንያዎች የኢትዮጵያን የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎች የሚጠቀሙበት ምቹ ምኅዳር መኖሩን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ።

የኢትዮጵያና ማሌዢያ ከፍተኛ የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል በተካሄደው ፎረም ላይ የማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሴሪ አንዋር ኢብራሂም፣የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የንግድና ኢንቨስትመንት አልሚ ባለሃብቶች ተገኝተዋል።

ፕሬዝዳንት ታዬ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፥ የማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጉብኝት፥ በሀገራቱ መካከል ያለውን የንግድ ትስስር በማጠናከር የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ለማጎልበት ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።

ኢትዮጵያና ማሌዢያ ያሏቸው ብዝኅ ሕብረ ብሔራዊነትን የተላበሱ የጋራ እሴቶች ለጋራ ዕድገትና ቀጣናዊ ትብብር ልዩ ዕድል መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት እ.አ.አ በ1965 የተጀመረውን የሀገራቱን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በንግድና ኢንቨስትመንት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ፕሬዝዳንት ታዬ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ የኢንቨስትመንት ሥነ-ምኅዳር መገንባቷን አስረድተዋል።

በግብርና መስክም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትክክለኛው የልማት መንገድ ላይ እየተጓዘች እንደምትገኝ ፕሬዝዳንት ታዬ አብራርተዋል።

በዚህም ሁለቱ ሀገራት በግብርና፣በእንስሳት፣ በማዕድንና በሌሎች ወሳኝ የልማት መስኮች ያላቸውን የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።

የማሌዢያ ኩባንያዎች የኢትዮጵያን የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎች በመጠቀም የጋራ ብልጽግና እና ተጠቃሚነትን የሚወስን የልማት ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ማሌዢያ ከዲፕሎማሲ ባለፈ የንግድና ኢንቨስትመንት አጋርነቷን ለማስፋት እያከናወነች ያለው ስራ የሚደነቅ መሆኑን ማንሳታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።

የማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሴሪ አንዋር ኢብራሂም የሀገራቱን ሁለንተናዊ ትብብር ለማጠናከር ላሳዩት ቁርጠኝነት ምስጋና አቅርበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review