አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የምትታትረው መዲና

You are currently viewing አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የምትታትረው መዲና

‎AMN- ህዳር 11/2018 ዓ.ም

‎በኢትዮጰያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ጨምሮ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች በመሰራት ላይ ይገኛሉ፡፡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሀገር አቀፍ ስትራቴጂ መፅደቅም እንደ አብነት የሚጠቀስ ነው፡፡

‎የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በትብብር ያዘጋጀው ይህ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሀገር አቀፍ ስትራቴጂ፣ ኢትዮጵያ ለቀጣይ አምስት ዓመታት የምትመራበት ስትራቴጂ ሆኖ ነው የፀደቀው፡፡

‎ ስትራቴጂው የፀደቀው የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን በማስፋፋት ኢትዮጵያ የጀመረችው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ አንዱ አካል በመሆኑ ነው፡‎

‎ኢትዮጵያ ያላትን በቂ የሆነ ታዳሽ ኃይል በመጠቀም ለነዳጅ የሚውለውን ከፍተኛ ወጪ ለማስቀረትና ለሌሎች መሠረተ ልማት ግንባታዎች ለማዋል እና ሀገርን ለማበልፀግ የሚያግዝ በመሆኑ ታምኖበት እየተሰራም ይገኛል፡፡

‎የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ስትራቴጂ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ከመቋቋም ባለፈ በኢኮኖሚ፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ በጽዱ ከተማ ግንባታ እና በሌሎችም ዘርፎችም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡

‎ይህን ስትራቴጂ ተግባራዊ እያደረገች የምትገኘው የአዲስ አበባ ከተማ፣ ለስትራቴጂው ተግባራዊነት የሚያስፈልጉ የኤሌክትሪክ ቻርጅ ጣቢያዎች ግንባታ እየተከናወነ ሲሆን፣ በከፊል አገልግሎት መስጠት የጀመሩ መኖራቸውን ኤ ኤም ኤን ዲጂታል በቅኝቱ ወቅት አረጋግጧል።

‎ ቅኝት ካደረገባቸው ስፍራዎች አንዱ በካዛንቺስ አከባቢ የተሰራው የኤሌክትሪክ ኃይል መሙያ ይገኝበታል።

‎በአገልግሎቱን ሲጠቀሙ ያገኘናቸው አቶ አየነው ታደሰ፣ አገልግሎቱ አስፈላጊ እና ጊዜውን የዋጀ መሆኑን ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ተናግረዋል።

‎የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎቱ ከዋጋ አንፃር እጅግ ቅናሽ መሆኑን የገለጹት አቶ አየነው፣ ከዚህ ቀደም ለነዳጅ በትንሹ ከ5 ሺህ እስከ 6 ሺህ ብር እንደሚያወጡ አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ ለኤሌክትሪክ መኪናቸው ፈጣን ቻርጅ ግን ከ5 በቶ እስከ 7 መቶ ብር ድረስ እንደሚያወጡ ነው የተናገሩት።

‎መኪናቸውን አንድ ኪሎ ዋት በ20 ብር እንደሚያስሞሉ የገለጹት አቶ አየነው፣ ገንዘብ እና ጊዜያቸውን ለመቆጠብ በጣቢያው መሙላት ምርጫቸው ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።

‎በቤት ውስጥ ቻርጅ ሲጠቀሙ እስከ ሰባት ሰዓታት እንደሚወስድባቸው የገለጹት አቶ አየነው፣ ነገር ግን በኃይል መሙያ ጣቢያ ሲጠቀሙ ከአንድ ሰዓት ባነሰ ጊዜ አገልግሎቱን እንደሚያገኙ ተናግረዋል።

‎የፖወር አፕ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መስራች አቶ ወንደሰን ለማ በበኩላቸው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

‎የኤሌትሪክ ኃይል መሙያ በቤት ውስጥ ረዥም ሰዓታትን እንደሚወስድ የተናገሩት መስራቹ፣ በፈጣን ቻርጅ ግን ከአንድ ሰዓት ባነሰ ጊዜ ቻርጅ ማድረግ ስለሚያስችል በህብረተሰቡ ዘንድ ቅቡልነቱ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ይገኛል ሲሉም አቶ አክለዋል።

‎ስራውን ለመጀመር ከውጭ ሀገራት ልምድና ተሞክሮ መውሰዳቸውን እና የሀገር ውስጥ የገበያ ጥናትም መስራታቸውን የገለጹት አቶ አየነው፣ አሁን ላይ እንደ ጀማሪ ውጤታማ መሆናቸውን አንስተዋል።

‎የኃይል መሙያ ጣቢያው ቴክኒሻን ወጣት ረታ ሁርጌሳ በበኩሉ፣‎ የኤሌትሪክ ኃይል መሙያው በአንድ ጊዜ 16 መኪናዎችን ቻርጅ የማድረግ አቅም እንዳለው ነው የገለጸው።

‎መንግስትም ይህንን ለማበረታታት ‎የኤሌትሪክ ኃይል መሙያውን ወደ ሀገር ውስጥ በብዛት እያስገባ ስለሆነ፣ አገልግሎቱን ማስፋፋት በጣም ወሳኝ መሆኑን ወጣት ረታ ተናግሯል፡፡

‎ፓወር አፕ ኢነርጂ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ ቻርጀሮችን እያስመጣ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ እና ተጠቃሚዎችም አገልግሎቱን እየለመዱት መምጣታቸውንም ወጣት ረታ ገልጿል።

ወጣቱ አክሎም፣ በቀን በአማካይ እስከ 200 መኪናዎች የፈጣን ቻርጅ አገልግሎት የሚሰጡበት እድል መኖሩንም አመልክቷል።

‎የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን የፓርኪንግ መሰረተ ልማት ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቢንያም ጌታቸው በበኩላቸው፣ አዲስ አበባ ከተማ ስማርት ሲቲ ለመሆን ተግታ እየሰራች መሆኗን ገልፀዋል።

‎የስማርት ሲቲ አንዱ መገለጫ ደግሞ በቂ የሆነ የተሽከርካሪዎች ማቆየሚያ ስፍራ መኖር ሲሆን፣ ከ152 የሚበልጡ ማቆሚያዎች ተዘርግተዋል ሲሉ ተናግረዋል።

‎ከዚህ ጎን ለጎን ከተማዋ ጭስ አልባ የሆነ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት አንዱ የስማርት ሲቲ መገለጫ መሆኑን ነው ያመላከቱት።

‎በዚህም መሰረት መዲናዋ ወደ ሀገር ውስጥ ለሚገቡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እያከናወነች ትገኛለች ብለዋል።

‎ከዚህ ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል መሙያ ጣቢያ ማቋቋም አንዱ ተግባር መሆኑን ያነሱት አቶ ቢኒያም፣ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን በተሰጡት የኮሪደር ልማቶች ላይ የመኪና ማቆሚያዎች አገልግሎት ሲሰጥ ጎን ለጎን ደግሞ የኤሌትሪክ ኃይል መሙያ ጣቢያዎች ማቋቋሙን ተናግረዋል ።

ባለስልጣኑ 9 የኤሌክትሪክ ኃይል መሙያ ጣቢያዎችን የመስራት እቅድ ይዞ እየሰራ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

በሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review