ማህበረሰቡ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን ለማድረግ ሲቸገርበት የነበረ እና አንዱን ወረዳ ለሁለት የከፈለው ድልድይ ህብተሰቡ በየደረጃው ለሚገኙ አስተዳደሮች ጥያቄ ሲያቀርብበት አንድ አመት አስቆጥሯል፡፡
በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ የሚኘነው ሳህሉ ጫካ በመባል የሚጠራው ይህ ድልድይ፣ ለብዙ ጊዜ የአከባቢው ማህበረሰብ እንዲሰራለት ሲጠይቀው የነበረው ጥያቄ ነዉ፡፡
ኤ ኤም ኤን ከወረዳው ነዋሪዎች ጋር በነበረው ቆይታ ከረጅም ጊዜ እንግልት በኋላ፣ የማህበረሰቡን ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት ችግር ፈቺ የሆነ ተግባር መፈፀሙን ተናግረዋል፡፡
የልደታ የክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ፋንቱ ኪዳኔ ድልድዩ ከፈረሰ አንድ አመት እንዳስቆጠረ ገልጸው፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የክፍለ ከተማው አመራሮች ችግሩን በመገንዘብ ምላሽ በመስጠታቸዉ መደሰታቸዉን ገልጸዋል፡፡
የወረዳው ነዋሪ አቶ ሰለሞን ጫላ በበኩላቸው፣ የድልድዩ አገልግሎት መቋረጥ በተለይ ህፃናት፣ አካል ጉዳተኞች እና ደካማ አዛውቶች ሲቸገሩ መቆየታቸውን ገልጸው፤ ለተሰጠው ምላሽም አመስግነዋል፡፡
አቶ ቃሲም አወል የተባሉ ሌላው ነዋሪ፣ ድልድዩ በመፍረሱ ምክንያት ክረምት በጭቃ በጋ በአቧራ ሲቸገሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡
የልደታ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ዘርይሁን ሽፈርዳ በበኩላቸው፣ ድልድዩ ለረጅም ጊዜ የማህበረሰቡ እና የምክር ቤት ጥያቄ ሆኖ የቆየ ትልቅ የመልካም አስተዳደር ችግር የነበረ መሆኑን ጠቅሰው፣ አሁን ላይ በተደረገው ከፍተኛ ርብርብ ችግሩን ለመቅረፍ ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመዋል፡፡
ይህ ድልድይ በአጭር ግዜ ውስጥ ተጠናቆ ለማህበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጥ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርጉ ገልጸው የወረዳው ነዋሪዎችም ለስራው መፋጠን እና ስኬታማነት ትልቅ ሃፊነት አለባቸው ብለዋል፡፡
የልደታ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚም ወ/ሮ ልዕልእቲ ግደይ፣ የህብረተሰቡን ጥያቄ መሰረት በማድረግ ድልድዩ የሚገኝበትን ሁኔታ ካዩ በኋላ ከመንገዶች ባለስልጣን ጋር በመነጋገር በሁለት ወር ውስጥ እንዲጠናቀቅ ስራ ማስጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡
በፍሬሕይወት ብርሃኑ