የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ ክህሎት ቢሮ ጋር በመተባበር በአይሲቲ ዘርፍ ለሚሰሩ ባለሙያዎች ለተከታታይ 3 ወራት ሲሰጥ የቆየውን የሙያ ማሻሻያ ስልጠና አጠናቆ አስመርቋል።
በምርቃት መርሃ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋውን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ጠቅላይ መምሪያዉ ተቋማዊ ሪፎርሙን ተግባራዊ ካደረገበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመታጠቅ የወንጀል መከላከል እና የምርመራ ስራዎችን ጨምሮ በርካታ ፖሊሳዊ ተግባራትን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባን መዘመን የሚመጥን የፖሊስ ሃይል ከመፍጠር አንፃር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የተመራቂ ሰልጣኞች ሚና አይተኬ መሆኑን ገልፀው ተመራቂ ተማሪዎች በዘርፉ ለሚሰጣቸው ተልእኮ ሀላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የሥራና ክህሎት ቢሮ ላደረገው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የሰው ሀብት ስራ አመራር ዳይሬክተር ምክትል ኮሚሽነር ዮሃንስ ጭልጆ የአዲስ አበባ ፖሊስ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በርካታ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ስራ ላይ በማዋል አገልግሎቱ እያዘመነ እንደሚገኝ በመግለፅ ቴክኖሎጂ ብቻ መታጠቁ በቂ ባለመሆኑ በዘርፉ ለሚሰራው ስራ የሰለጠነ የሰው ሀብት ማብዛት አሰፈላጊ በመሆኑ ሥልጠናው በዘርፉ ባለሙያዎች የማብዛት ዕቅዱ አካል መሆኑን ገልፀዋል።
የምርታማነት እና ልህቀት ማዕከል ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አድማሱ በቀለ በበኩላቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ የመዲናዋን ሰላም እና ደህንነት ለማስጠበቅ በቴክኖሎጂ የሄደበትን ርቀት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
ተቋሙ እራሱን በቴክኖሎጂ ለማዘመን በሚደረገው ጥረት ውስጥ መሰል ስልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።
ሰልጣኞቹ በሜንቴናንስ እና በኔትወርኪንግ፣ በCC tv ሴኩሪቲ ካሜራ ፣ ፣በፕሮግራሚንግ ፣በዳታ ቤዝ ፣ዌቭ ዴቭሎፕመንት ለተከታታይ 3 ወራት የተግባር ስልጠና የወሰዱ መሆናቸዉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አመላክቷል።