የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
. የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ሀገርን በሚጠቅም ስትራቴጂ እየተመራ እና ውጤት እያመጣ መሆኑን የዘርፉ ምሁር ገልጸዋል
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካና በቀይ ባህር አካባቢ ካላት ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ፣ እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ከመሆኗ አንፃር የሀገሪቱ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ከብሔራዊ ወሰን አልፎ ቀጠናዊና እና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳው የጎላ ነው። የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ዋነኛ ዓላማዎችም የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ፣ ለዜጎች ቅድሚያ መስጠት፣ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ማረጋገጥ እና ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነት ማጠናከር ናቸው። በዚህ ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያ በሁሉም አህጉራት በሚገኙ ሀገራት ዘንድ ያላት ዴፕሎማሲያዊ ግንኙነት እያደገ ነው፡፡ ከአፍሪካ እስከ አውሮፓና እስያ ሀገራት ድረስ ትብብሮችን እያደረገች ነው። ይህ ሁኔታ የኢትዮጵያ ዴፕሎማሲ ሀገርን በሚጠቅም መንገድ እየተተገበረ እና ውጤት እያመጣ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ይላሉ፤ የዴፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያዎች፡፡ ባለሙያዎቹ ለዚህ ሃሳብ የማሌዥያና የኢትዮጵያን የሰሞኑ ዴፕማሲያሲያዊ ስምምነቶች በአስረጅነት ይጠቅሳሉ፡፡
የኢትዮጵያና ማሌዥያ ዴፕሎማሲያዊ ግንኙነት
ኢትዮጵያ እና ማሌዥያ ዓመታትን የተሻገረ የሁለትዮሽ ግንኙነትን አላቸው። እ.ኤ.አ በጥር 1965 የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በይፋ የተጀመረበት ጊዜ ነበር፡፡ ይሁንና በደርግ ስርዓት ወቅት በነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሻከር ማሌዥያ በ1982 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ዘግታ ነበር፡፡ ይህ ኤምባሲ ከመስከረም 13 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ዳግም ተከፍቶ ስራ ጀምሯል፡፡ ኤምባሲው በአዲስ አበባ ዳግም ስራ የጀመረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በጥቅምት 2017 ዓ.ም ማሌዥያን ከጎበኙ በኋላ ነው፡፡
“የኤምባሲው መከፈት ማሌዥያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት እንዲሁም የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አቅም እያደገ መሆኑን የሚያሳይ ነው። በተጨማሪም በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ላይ፣ የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያስገኙ የትብብር ዘርፎች አዳዲስ ዕድሎችን ለማሰስ ይረዳል” በሚል በወቅቱ መገለጹ ይታወሳል፡፡
የማሌዥያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ህብረት ዋና መሥሪያ ቤት መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ የኤምባሲው ዳግም መከፈት፣ ከአህጉራዊው ተቋም ጋር ለመስራት አዳዲስ መንገዶችን ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል ሲል መግለጹም አይዘነጋም፡፡
የማሌዥያ ኤምባሲ በአዲስ አበባ ዳግም መከፈት ለሁለቱ ሀገራት ሁለንተናዊ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ከማበርከቱም በላይ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እያደገ መሄዱን የሚያመላክት ተደርጎ ተወስዷል፡፡

ይህ ሂደት ተጠናክሮ የማሌዥያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሰሪ አንዋር ቢን ኢብራሂም የሶስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት በኢትዮጵያ አድርገዋል፡፡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህን ጉብኝት፤ “በማሌዢያ እና ኢትዮጵያ መካከል እያደገ ያለውን ወዳጅነት እና ትብብር የሚያሳይ፤ በሀገራችን የብልጽግና ጉዞ ውስጥም በጠቃሚ ጊዜ የተደረገ ነው” ብለውታል።
ዳያሞ ዳሌ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አገልግለዋል፡፡ በመንግስት ኮሚኒኬሽንና በሌሎች ተቋማት ሰርተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የፖለቲካና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተንታኝ ናቸው፡፡ ጉዳዩን አስመስክቶ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አስተያየት፣ “የኢትዮጵያ ዴፕሎማሲ ሀገርን በሚጠቅም ስትራቴጂ እየተመራ እና ውጤት እያመጣ ነው፡፡ ለዚህ ማሳያና ማስረጃው ደግሞ የማሌዥያ ጠቅላይ ሚኒስትር በሀገራችን ያደረጉት ሰሞነኛ ጉብኝት ነው” ብለዋል፡፡
የቢዝነስ ፎረም
የጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሴሪ አንዋር ቢን ኢብራሂም ጉብኝትን ተከትሎ የኢትዮ-ማሌዥያ ቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡ በዝግጅቱ ላይ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ ባለሃብቶች፣ አመራሮችና ሌሎችም ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡ በወቅቱ ፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያና ማሌዥያ ቢዝነስ ፎረም የሀገራቱን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር ጉልህ ሚና አለው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የኢትዮጵያ እና ማሌዥያ የንግድና እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት አሁን የተጀመረ ሳይሆን በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ ነው። በመሆኑም በአዲስ አበባ የተካሄደው የቢዝነስ ፎረም የኢትዮጵያ እና ማሌዥያን የንግድና እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት በማሳደግ የሀገራቱን የወዳጅነት ትርጉም ከፍ የሚያደርግ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አክለውም ኢትዮጵያ በንግድ፣ በግብርና፣ በማዕድን፣ በቴክኖሎጂ እና በሌሎች ዘርፎች በርካታ ስራዎችን እየሰራች መሆኗንም ገልጸዋል።
በፎረሙ ላይ ማሌዥያ በማምረቻ፣ በግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ፣ በቴክኖሎጂ፣ በጨርቃ ጨርቅ፣ በመድኃኒት፣ በሎጂስቲክስና በኢነርጂ ዘርፎች ላይ ኢንቨስት እንድታደርግ ጥሪ ቀርቧል። ከፎረሙ በተጨማሪ የፓናል ውይይትም ተደርጓል፡፡
የፖለቲካና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተንታኙ ዳያሞ ዳሌ እንደሚሉት፣ ዴፕሎማሲ የሚመሰረተው በኢኮኖሚና ቢዝነስ ዙሪያ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ትብብር ዴፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል፡፡ ከዚህ አንጻር ማሌዥያ እና ኢትዮጵያ ያደረጉት የቢዝነስ ፎረም የሚኖረው ጠቀሜታ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም በሀገራት መካከል የንግድ ልውውጥ ሲጨምር የዲፕሎማሲ ግንኙነት ያድጋል፡፡ መተሳሰብና ትብብር ከፍ ይላል፡፡ የሀገራት መተሳሰብ እና መደጋገፍ ሲያድግ ደግሞ በሁሉም መስክ የሚኖረውን ትብብርና መደጋገፍ ከፍ ያደርጋል፡፡ ለአብነትም የማሌዥያ እና ኢትዮጵያ የቢዝነስ ግንኙነት ማደግ ኢትዮጵያ ለምታነሳው የባህር በር ጥያቄና ሌሎችም ጉዳዮች ማሌዥያ ድጋፍ እንድታደርግ የሚያስችል በመሆኑ የሁለቱ ሀገራት የቢዝነስ ፎረም የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው በማለት ያስረዳሉ፡፡

የእህትማማችነት ፊርማ
የማሌዥያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጉብኝት በርካታ ጉዳዮች የተከናወኑበት ነው፡፡ ከእነዚህ ወሳኝ ጉዳዮች ውስጥ በአዲስ አበባ እና በማሌዥያ ዋና ከተማ ኳላ ላምፑር መካከል የተፈረመው የእህትማማችነት የጋራ መግባቢያ ስምምነት ተጠቃሽ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የማሌዥያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሰሪ አንዋር ቢን ኢብራሂም በተገኙበት፤ የእህትማማችነት የትብብር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመናል ሲሉም በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተንታኙ ዳያሞ ዳሌ፣ “ይህ ስምምነት አንድምታውና ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡ አዲስ አበባ እና ኳላ ላምፑር ዘመናዊ ከተሞች ናቸው፡፡ አዲስ አበባ ከኳላ ላምፑር ብዙ የምትማረው ነገር አለ፡፡ መማር ብቻ ሳይሆን ብዙ የምትሰጠው ልምድና ተሞክሮ አለ” በማለት የስምምነቱን ጠቀሜታ ያስረዳሉ፡፡
የሁለቱ ከተሞች የጋራ ሥምምነት በከተሞች የአረንጓዴ ሽፋን፣ በቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት፣ በከተማ መሬት አየያዝና አጠቃቀም ስርዓት ለመዘርጋት፣ ለወንዝ ዳርቻ ልማት፣ በከተማ ትራንስፖርት፣ በቤቶች ግንባታ፣ በአደጋ መከላከል፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በሰው ሃይል ማብቃት ዙሪያ፣ በልምድ ልውውጥ እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸው ነው። ዳያሞ ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንዳሉት፣ ይህ ስምምነት ለሁለቱ ከተሞች እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው፡፡

የመሪዎች ውይይት
የማሌዢያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሰሪ አንዋር ቢን ኢብራሂም የኢትዮጵያ ጉብኝትን ተከትሎ በርካታ መርሃ ግብሮች፣ ውይይቶች እና ስምምነቶች ተካሂደዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በወቅቱ የኢትዮጵያ እና ማሌዥያ ትብብር ለረጅም ዓመታት የዘለቀ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡ የማሌዥያው ጠቅላይ ሚኒስትር ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት መካከል በጋራ መርሆዎች ላይ የተመሠረተና እያደገ የመጣውን ጥልቅ አጋርነት የሚያንጸባርቅ መሆኑንም አክለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ የጉብኝት ልውውጥ ጥልቅ አጋርነታችንን የሚመሰክር ሲሆን ይህም በርካታ ቁልፍ ሰነዶችን በመፈረም ተጠናክሯል። የመግባቢያ ሰነዶቹ በቱሪዝም፣ በጤና፣ በአየር ትራንስፖርት አገልግሎት፣ በኳላ ላምፑር ከተማ ምክር ቤት እና በአዲስ አበባ አስተዳደር የትብብር መስክ ላይ ያተኮሩ ናቸው ሲሉ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል::
ባደረግነው የሁለትዮሽ ውይይት፣ ትብብራችንን የበለጠ ለማጠናከር እና ለማስፋት ያለንን የጋራ ቁርጠኝነት አረጋግጠናል ሲሉም አክለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሰሪ አንዋር በበኩላቸው ጉብኝታቸው ከዲፕሎማሲያዊ ጉዞ ይልቅ ቤተሰባዊ መሆኑን ገልጸው፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር ለማስፋት ያላቸውን ፍላጎት አመላክተዋል። ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ውጤታማ ትብብር ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል። ሀገራቱ ትብብራቸው ለረጅም ዓመታት የዘለቀ እንደሆነ በማንሳት ግንኙነቱ በበርካታ ዘርፎች ትብብርን ለማሳደግ አዳዲስ በሮችን የከፈተ ነውም ብለዋል።
የጉብኝት መርሀ-ግብሩ የወዳጅነት ዛፍ የመትከል ሥነ-ሥርዓት፣ የብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ጉብኝት፣ የሁለትዮሽ ውይይት፣ የሰነዶች ልውውጥ ብሎም በቱሪዝም፣ በጤና፣ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት፣ በኳላ ላምፑር ከተማ ምክር ቤት እና በአዲስ አበባ አስተዳደር የትብብር ስምምነቶችን ያካተተ ነው። መሪዎቹ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የተወያዩ ሲሆን በዚህም የወደፊት ትብብርን ብሩህ እና ጠንካራ እንደሚሆን አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ በደቡብ- ደቡብ ትብብር(South-South Cooperation) ውስጥ ያላትን ተሳትፎና እንደ ብሪክስ ላሉ ዓለም አቀፍ መድረኮች የምታደርገውን ድጋፍ አድንቀው በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ ተደማጭነት እያደገ መምጣቱንም ጠቅሰዋል።
የሀገራቱ የወደፊት ትብብር በኢንቨስትመንት፣ ንግድ፣ ትምህርት፣ ሳይንሳዊ ምርምር፣ ባህልና ክልላዊ የገበያ ውሕደት ላይ እንደሚያተኩርና ይህም የደቡብ ምሥራቅ እስያ ሀገራት ማህበር (ASEAN) እና በአፍሪካ ቀንድ ኢኮኖሚ መካከል ትስስር የሚፈጥር መሆኑም ተገልጿል፡፡
የፖለቲካና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተንታኙ ዳያሞ ዳሌ ማሌዥያ እጅግ ፈጣን ኢኮኖሚ እያስመዘገቡ ከሚገኙ ሀገራት መካከል አንዷ ነች፡፡ በራሷ መንገድና ፍልስፍና እየተቀየረች ነው። የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲም እያደገ፣ ውጤት እያመጣ እና በሁሉም አህጉራት መሰረት እየጣለ ነው፡፡ በመሆኑም በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረሰው ስምምነት የሚያስገኘው ዴፕሎማሲያዊ ጠቀሜታ እጅግ ከፍተኛ ስለሆነ ለተግባራዊነቱ በትኩረት መስራቱ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
በጊዜው አማረ