“አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ብዝሃነትን በማንፀባረቅ ተምሳሌት የሆነ ሚዲያ ነው”
የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ
ኢትዮጵያ ከ85 በላይ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መኖሪያ ሀገር ናት፡፡ ህብረ ብሔራዊነትም ዋነኛ መገለጫዋ ነው፡፡ የተለያየ ብዝሃ ማንነት ያላቸው ህዝቦቿም ለዘመናት ተሳስረውና ተጋምደው በአንድነትና በአብሮነት ኖረዋል፤ አሁንም አብረው እየኖሩ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብቶች መከበር እንዲችሉ እውቅና እና ህጋዊ ዋስትና የሰጠው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ቀን የፀደቀው ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም ሲሆን፤ በየዓመቱ “የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን” በሚል ተከብሮ ይውላል፡፡ በዓሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ20ኛ ጊዜ “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ ህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ በድምቀት ይከበራል፡፡
ከዋናው በዓል በፊትም ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ተቋማት በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበሩ ይገኛሉ፡፡ መገናኛ ብዙሃንም በተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄዱ ኹነቶችን ከመዘገብና መረጃ ከማድረስ ባሻገር በዓሉን በተለያየ መልኩ ያከብሩታል፡፡
መገናኛ ብዙሃን በተለይ ብዝሃነት ባለበት ሀገር ውስጥ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን፣ መከባበርን፣ መቻቻልንና አብሮነትን በማጎልበት ረገድ ቁልፍ ሚና ካላቸው ተቋማት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ የተለያየ ባህል፣ ቋንቋ፣ እምነት ያላቸው ህዝቦች እርስ በርስ እንዲተዋወቁ፣ አንዱ የሌላውን ባህል እንዲያደንቅና መግባባትና ትስስር እንዲጎለብት በማድረግ ጉልህ ሚና ይጫወታሉ፡፡
የትውልድ ድምፅ የሆነው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ 20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የተቋሙ አመራሮችና ሰራተኞች በተገኙበት ከትናንት በስቲያ በፓናል ውይይት አክብሯል፡፡

በመድረኩ ላይ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓትን ስትከተል ዋና መነሻው ብዝሃነትን ለማስተናገድ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታትም የፌዴራል ስርዓቱ ሲተገበር በህገ መንግስቱ የተቀመጡ ስርዓቱ የሚመራባቸውን መርሆዎች በደንብ ተረድቶ በአግባቡ ስራ ላይ እንዲውሉ በማድረግ የተገኙ መልካም ውጤቶችና ድክመቶችን መፈተሽና ወደራስ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በሀገር ውስጥ በአምስት ቋንቋዎች መረጃዎችን ለአድማጭ ተመልካችና አንባቢያን እያደረሰ ይገኛል፡፡ “አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ብዝሃነትን በማንፀባረቅ ተምሳሌት የሆነ ሚዲያ በመሆኑ የሚያኮራ ነው” ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፣ አዲስ አበባ የብሔር፣ የቋንቋ፣ የእምነት… ብዝሃነት ያለባት ከተማ እንደመሆኗ ሚዲያው ከተማዋን እንዲመስል እየተሰራ ነው። በቀጣይም አቅምን ታሳቢ በማድረግ በተጨማሪ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ለማህበረሰቡ መረጃዎችን ለመስጠት እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
ብዝሃነት ውበት ከመሆኑ ባሻገር የሀይልና ጥንካሬ ምንጭ ነው፡፡ የብዝሃነት ሀይልን በመጠቀም በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስክ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የሄደችበት መንገድ ማሳያ መሆኑን አቶ ካሳሁን አንስተዋል፡፡ ከነጠላ ይልቅ የወል ትርክት ላይ በመስራት ሀገርን ማስቀጠልና ማጽናት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሲደመሩ፣ ሲስማሙና አንድ ሲሆኑ ውብና ጠንካራ ናቸው፡፡ ለዚህም “አይቻልም” የተባለውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እውን ማድረግ የተቻለበትን መንገድ ማሳያ ነው ያሉት አቶ ካሳሁን፣ ኢትዮጵያ በራስ ተነሳሽነት፣ በራስ ሀብትና ጉልበት በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ ግዙፍ ፕሮጀክት በመገንባት ዓለምን ማስገረም ችላለች፡፡ ህዝብ ሲተባበርና አንድነቱ ሲጠናከር ዓለምን የሚያስደምም ታሪክ መስራት እንደሚቻል ግድቡ ምስክር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የተቋሙ ሰራተኞች በበኩላቸው፤ ሚዲያ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት እና ቀኑን ማክበር ለህብረተሰቡ የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ሰራተኛ ወይዘሮ ዝናሽ በቀለ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር ሚዲያው ለማህበረሰቡ በእውቀት ላይ የተመሰረተ መረጃ በመስጠት ግንዛቤ መፍጠር እንዲችል ያግዘዋል፡፡ ብዝሃነት የኢትዮጵያ ጸጋ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን የብሔር፣ የኃይማኖት፣ የእምነትና የአመለካከት ልዩነቶች ቢኖራቸውም በአንድነት ሲተባበሩ ሀገርን ወደፊት ማሻገር እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡

ሌላኛው የተቋሙ ሰራተኛ አቶ ታሪኩ ለገሰ፣ ሚዲያው ኢትዮጵያን የሚመስልና አዲስ አበባ የብዝሃነት ከተማ መሆኗን በሚያንጸባርቅ መልኩ ነው እየተሰራ ያለው፡፡ ዋና ተልዕኮውም ለህብረተሰቡ መረጃ መስጠት ነው፡፡ በመረጃ ኢትዮጵያንና አዲስ አበባን ሲያሳይ ደግሞ ብዝሃነትን በተጨባጭ በማሳየት መሆን እንዳለበት ተናግሯል፡፡
በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ኤፍ ኤም 96 ነጥብ 3 የመዝናኛ ፕሮግራም አዘጋጇ ጋዜጠኛ ሰብለወንጌል መስፍን፣ ኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ ሀገር እንደመሆኗ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር አንዱ የሌላውን ባህልና ወግ እንዲያውቅና እንዲረዳ፣ መከባበርና አብሮነት እንዲጠናከር ያግዛል፡፡ አንዱ የሌላውን የእርቅ፣ የአመጋገብ፣ የአለባበስና የሰላምታ ስርዓት የሚያውቅበትን ሁኔታ በመፍጠር አንድነታችንን እያጠናከሩ መሄድ እንደሚገባ ነው የተናገረችው፡፡
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል የእኩልነትና ተቻችሎ የመኖር ማሳያ እንደሆነ የሚገልጸው ደግሞ በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ፤ ኤ ኤም ኤን ፕላስ የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ዘርፍ ጋዜጠኛ የሆነው ሙሐመድ ቶፊቅ ነው፡፡ ህብረ ብሔራዊነታችን በአግባቡ ከያዝነውና ከተጠቀምንበት ለሀገር ልማትና እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ አለው፡፡ በህብረ ብሔራዊነት ውስጥ አንድ የሚያደርገንን ትርክት መገንባት ይኖርብናል፡፡ ልዩነታችን ውበታችን በመሆኑ ለቱሪዝም መስህብነት ልንጠቀመው ይገባልም ብሏል፡፡
በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የትግርኛ ቋንቋ ዘርፍ ጋዜጠኛ ነፃነት መብራቱ በበኩሏ፤ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር አንዱ የሌላውን ባህል እንዲያውቅ በማድረግና አንድነትን በማጠናከር ጉልህ ሚና አለው፡፡ ቱሪዝምን በማሳደግም ፋይዳ ስላለው የበዓሉ መከበር አስደሳች መሆኑን ገልጻለች፡፡
በመድረኩ ላይ “ዴሞክራሲና የፌዴራል ስርዓት በኢትዮጵያ፤ ተስፋዎቹና ተግዳሮቶች” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ የመወያያ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በስንታየሁ ምትኩ