•ኢትዮጵያን በ2022 ዓ.ም በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ቀዳሚ ሀገር ለማድረግ እየተሰራ ስለመሆኑ ተመላክቷል
በአንድ ወቅት ከዕለታዊ የሕይወት እንቅስቃሴ የራቁ፣ ምናባዊ እና የማይጨበጡ ይመስሉ የነበሩ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂዎች ዛሬ ላይ በሰው ልጆች ህይወት ላይ ተጽዕኖአቸው ቀጥተኛ ሆኗል፡፡ ከጤና አጠባበቅ እስከ ፋይናንስ፣ ከትራንስፖርት እስከ ንግድና ግብርናው ዘርፍ ጭምር ያላቸው ሚና ወሳኝ እየሆነ መጥቷል፡፡ በዓለም ገበያ ውስጥ ያለው ድርሻም እያደገ መጥቶ ከ350 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል፡፡
የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዓለም አቀፉን ፐብሊክ ፈርስት የተባለ አማካሪ ድርጅት ዋቢ አድርጎ ባወጣው መረጃ መሠረት ከሠሃራ በረሃ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ቴክኖሎጂውን በመጠቀም በመጪዎቹ 10 ዓመታት ውስጥ 30 ቢልዮን ዶላር ሊያገኙ ይችላሉ፡፡
ሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) እንደ ዘመናዊ የሳይንስ መስክ የተጀመረው በ1950ዎቹ አጋማሽ አካባቢ ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ሆኖም በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ ከዚያ ቀደም ብሎ እንደነበርና በተለይም በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሂሳብ ሊቃውንት ለዘመናዊ ሰው ሰራሽ አስተውሎት መሠረት የጣሉ ጽንሰ ሀሳቦችን ስለማምጣታቸውም ይነገራል።
እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር 1950 በወርሃ ጥቅምት እውቁ እንግሊዛዊ የሂሳብ ሊቅና የኮምፒውተር ሳይንስ ተመራማሪ አለን ቱሪንግ “ኮምፒዩቲንግ ማሽነሪ ኤንድ ኢንተለጀንስ” (Computing Machinery and Intelligence) የተሰኘ ታሪካዊ ጽሑፉን “Mind” በተባለው ጆርናል ላይ አሳተመ። ይህ ጽሑፍ ታዲያ የኮምፒውተሮችን የማሰብ ችሎታ ለመገምገም የሚያገለግለውን “ቱሪንግ ቴስት” አስተዋወቀ። ብዙዎችም የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ዘርፍ መጀመር ከዚህ ጽሑፍ ጋር ያያይዙታል።
የሰው ሰራሽ አስተውሎት መስክ በይፋ የተመሠረተውና ስሙን ያገኘው ግን እ.ኤ.አ በ1956 በዩናይትድ ስቴትስ በዳርትማውዝ ኮሌጅ በተካሄደው የክረምት ወርክሾፕ ወቅት ነበር። “አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ” የሚለውን ስም የሰጠው ጆን ማካርቲ፣ ማርቪን ሚንስኪ፣ ናታኒኤል ሮቼስተር እና ክላውድ ሻኖን ጨምሮ ሌሎችም ተመራማሪዎች በዚህ ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል። ይህ ስብሰባ “አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ” የሚለውን ስም በይፋ በመስጠት ዘርፉ ራሱን የቻለ የጥናት መስክ እንዲኖረው እንዳስቻለ ይነገራል።

አብዛኛዎቹ ዓለም አቀፍ ጥናቶችና ሪፖርቶች በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ አሜሪካ እና ቻይናን በቀደምትነት ያስቀምጣሉ፡፡ አሜሪካ በብዙ መስፈርቶች በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ ቀዳሚዋ ሀገር ተደርጋ ትወሰዳለች። እንደ ጉግል፣ ማይክሮሶፍት፣ አማዞን፣ ሜታ እና ኦፕንኤአይ ያሉ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የሰው ሰራሽ አስተውሎት ፈጠራን ይመራሉ።
ቻይና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ የአሜሪካ ቀጥተኛ ተፎካካሪ ስትሆን፣ በተለያዩ መስኮች ላይ የላቀ ቦታ ትይዛለች። እ.ኤ.አ በ2030 የዓለም የሰው ሰራሽ አስተውሎት መሪ የመሆን ብሔራዊ ስትራቴጂን በመከተል መንግሥት ከፍተኛ የመዋዕለ ንዋይ ድጋፍ ያደርጋል። ከአሜሪካና ከቻይና በተጨማሪ ሌሎች ሀገሮች በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረጉ ካሉ ሀገራት መካከል ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ እና እስራኤል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
እንደ ሳይ ቴክ ዴይሊ ድረ-ገጽ መረጃ በእነዚህ ሀገራት በጤና አጠባበቅ ዘርፍ ሰው ሰራሽ አስተውሎት የታካሚ ውጤቶችን ለማሻሻል እና ወጪዎችን ለመቀነስ ጥቅም ላይ ይውላል። በተለይም በሜዲካል ኢሜጂንግ ቴክኖሎጂ እንደ ኤም.አር.አይ እና ሲቲ ስካን ምርመራዎች የሰው ሰራሽ አስተውሎት አልጎሪዝም በመጠቀም በሽታን በከፍተኛ ጥራት መለየት ይችላሉ።
የፎርብስ መጽሔት ጸሐፊው ጊል ፕረስ እንደሚያስረዳው አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አስተውሎት) አንዱ ወሳኝ ተጽዕኖ ያለው በፋይናንስ ዘርፍ ሲሆን። በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የሚታገዙ አልጎሪዝሞች መረጃ ለመተንተን እና የፋይናንስ ተቋማት ተአማኒነት ያለው እና ትክክለኛ ውሳኔ ለመወሰን ያስችላል። ለምሳሌ ሰው ሰራሽ አስተውሎት የተጭበረበረ ግብይትን ለመለየት እና የገበያ አዝማሚያን ለመተንበይ ይጠቅማል። ከዚህ በተጨማሪም ለግለሰቦች የኢንቨስትመንት ምክረ ሃሳብ ያቀርባል።
እንደዚሁም የሰብል ምርትን ለማሳደግ እና ብክነትን ለመቀነስ ጥቅም ላይ ይውላል። በሰው ሰራሽ አስተውሎት የጎለበተ መሳሪያ የአፈርን እርጥበት ደረጃ፣ የሙቀት መጠን እና ሌሎች የአካባቢ ሁኔታዎችን በመከታተል አርሶ አደሮች ለመዝራት እና ለማጨድ መረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ እንዲወስኑ የሚያግዝ እውነተኛ መረጃን ያቀርባል። ለሰው ሰራሽ አስተውሎት ምስጋና ይግባውና የሒሳብ ሙያም ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ ነው፡፡
የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ተቋማት ዋና ዋና የስራ ሂደቶቻቸውን ለማስተዳደር እና ለማቀላጠፍ በሚጠቀሙባቸው የሶፍትዌር ሥርዓቶች ውስጥ የሚገኙ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሞዴሎች 40 በመቶ ጊዜን ለመቆጠብ እንዲሁም 94 በመቶ ድረስ የስህተት መጠንን ለመቀነስ መቻላቸውን አረጋግጠዋል።
የፎርብስ መጽሔት በድረ ገፁ ባወጣው መረጃ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ስራዎችን በማቀላጠፍ፣ አዳዲስ ሀሳቦችን በማምጣት እና ወጪን በመቀነስ አፍሪካን የዲጂታል ኢኮኖሚ ባለቤት ማድረግ ያስችላል፡፡ በአህጉረ አፍሪካም እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ናይጄሪያ እና ጋና በአንጻራዊነት ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ከመጠቀም አንጻር የተሻሉ ቢባሉም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያም ዘርፉን ለማሳደግ የጀመረቻቸውን ጥረቶች አድናቆት አስገኝተውላታል። ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ አብዮት እና በሌሎች ጉዳዮች ያጋጠማት መዘግየት በሰው ሰራሽ አስተውሎትም እንዳይደገም በፍጥነት ዘርፉን ተቀላቅላለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና መስሪያ ቤት የምረቃ መርሃ ግብር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢንስቲትዩቱ በ5 ዓመታት ውስጥ እዚህ ደረጃ ደረሰ ብሎ መገመት እንደሚከብድ ገልጸው፣ ተቋሙ በአፍሪካም ጭምር በግንባር ቀደምትነት የሚታይ ነው ብለዋል። በዓለም ዙሪያ በርካታ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ተቋማትን የመጎብኘት ዕድል እንደገጠማቸውና የኢትዮጵያው ኢንስቲትዩት ደረጃ ፈጽሞ የማይናቅ መሆኑን ጠቁመው፣ እጅግ ከፍተኛ አቅም እንደያዘ አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከ100 በላይ አገልግሎቶች የሚሰጠው የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ሥርዓት የተሠራው በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት መሆኑን ተናግረዋል። የኢንስቲትዩቱ የፈጠራ ሥራዎች ከሮቦት አካላት ማምረትም በላይ የሆነ የሮቦት ሶፍትዌሮችን ጭምር የሚያካትቱ ናቸው። ይህ ይበል የሚያሰኝ ምርምር ድሮኖችን ከማምረት ባሻገር፣ የማነጋገር እና የተሻለ ሥራ እንዲሠሩ የማድረግ አቅምን ፈጥሯል። በጤናው ዘርፍም የጡት ካንሰርን መለየት የሚያስችል ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኘ ሥራ ተሠርቷል።
በግብርናው መስክ በሰብል በሽታ ልየታ፣ በሎጂስቲክስ ቁጥጥር ላይ ኢንስቲትዩቱ የምርምር ውጤቱን አውጥቷል። ኢንስቲትዩቱ በተለያዩ ዘርፎች አጋዥ ውጤቶችን እያሳየ ቢሆንም፣ ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሪ ሐሳቡ “AI for All” ወይም “ኤ.አይ ለሁሉም” ማገዝ እና መጥቀም እንዲችል ማድረግ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የሀገርን ጥቅም የሚያስከብሩ የፈጠራ ስራዎችን ከመስራት ባሻገር የሰለጠኑ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት እየሰራ መሆኑን የሚገልፁት ደግሞ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን በ2022 ዓ.ም በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ቀዳሚ ሀገር ለማድረግ እየተሰራ ስለመሆኑም ወርቁ (ዶ/ር) ይገልጻሉ፡፡
ኢንስቲትዩቱ የክላውድ ኮምፒውቲንግ እና ግዙፍ ዳታ ላይ በስፋት እየሠራ ነው። ትልቅ አቅም ያለው የዳታ ማዕከል መገንባት ብቻ ሳይሆን፣ መረጃውን መሰብሰብ፣ ማቀናበር እና መረጃዎችን ለተጨማሪ ጥቅም እንዲውሉ የማድረግ አቅም በኢንስቲትዩቱ ተፈጥሯል። ከዳታ አጠቃቀም ጋር ተያይዞም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የሆኑትን አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ሶማልኛ፣ ትግርኛ እና አፋርኛ ቋንቋዎችን በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ምርምር በማበልፀግ ሰዎች ከሌላው ጎረቤታቸው ጋር ያለቋንቋ ችግር እርስ በርስ መግባባት የሚችሉበትን መንገድ መፍጠር ተችሏል።
በዚህም አፋርኛ ተናጋሪው የሎጊያ ሰው ከሶማሊኛ ተናጋሪው የጎዴ ሰው ጋር፣ ትግርኛ ተናጋሪው የመቐሌ ሰው ደግሞ ከአማርኛ ወይም ከሌላው ቋንቋ ተናጋሪ ጋር ቴክኖሎጂውን ብቻ ተጠቅሞ ሶስተኛ ሰው ሳያስገቡ መግባባት ይችላሉ። በተጨማሪም የሀገር ውስጥ ቋንቋዎችን ከጽሑፍ ወደ ድምፅ የመቀየር እና ድምፁን ወደ ጽሑፍ የመቀየር ሥራም በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እየተሠራ ነው።
እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገሮች አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በፍጥነት ለማደግ እና ተወዳዳሪ ለመሆን እድል የሚፈጥር ሲሆን፣ በተለይም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ደህንነትን ለማረጋገጥ፣ ልማትን ለማፋጠን፣ የኢኮኖሚ እድገትን ለማገዝ በእጅጉ እንደሚጠቅም እሙን ነው፡፡ ቴክኖሎጂው የኮሙኒኬሽን አገልግሎትና ሀብት አስተዳደር ጨምሮ የትራንስፖርት፣ የቤቶች ግንባታና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሳለጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ ዘመኑን ተረድታ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንሱ ዘርፍ ጠንካራ ተሳትፎ እያደረገች ሲሆን፣ ዘርፉን በተቋም ደረጃ የተደገፈ ማድረጓ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳድራ ዘርፉ ከሚያስገኘው በረከት ለመቋደስ ብርቱ ጥረት እያደረገች ስለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡
በሳህሉ ብርሃኑ