ሀገርን ያፀኑት ፍልስፍናዊ ዕሳቤዎች

You are currently viewing ሀገርን ያፀኑት ፍልስፍናዊ ዕሳቤዎች

ቫን ደር ቬልደን የተባሉ ምሁር “ፊሎሶፊ ናው” በተባለ መጽሔት ላይ በ2018 አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ አሳትመው ነበር። “Indigenous Philosophies” የሚል ርዕስ ያለው ይኸው ጽሑፍ ሀገር በቀል ፍልስፍናዎች የአንድን ማህበረሰብ የሕይወት ዓላማ፣ እውቀት፣ ማህበረሰባዊ መስተጋብርና የወል እሴቶች እንደሚቀርፁ በጥልቀት ያብራራል። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ እንደሰፈረው ሀገር በቀል ፍልስፍናዎች ማህበረሰቦች ዓለምን የሚረዱበትን፣ ህይወትን የሚመሩበትን እና የወል ተግባቦት ላይ የተመሰረተ ማህበራዊ ሥርዓት እንዲኖር ጉልህ ሚና ይጫወታሉ፡፡

እዚህ’ጋ ርዕሰ-ጉዳዩን ይበልጥ ለማብራራት የአፍሪካ ፍልስፍና የሆነው ኡቡንቱን (Ubuntu) እንደ አብነት እንጥቀሰው፡፡ ኡቡንቱ “ሰው በሌሎች ሰዎች አማካኝነት ነው ሰው የሚሆነው” በሚል ጥልቅ ፍልስፍናዊ እሳቤ ላይ ይመሰረታል፡፡ ይህ እሳቤ ጥልቅ ፍልስፍናዊ አተያዮችንና ትግበራዎችን በውስጡ ይዟል። የማህበረሰባዊ ትስስር፣ የጋራ መግባባት እና ለሌሎች ሰዎች ማሰብን አጉልቶ ያንጸባርቃል፡፡

የኡቡንቱ ፍልስፍናዊ እሳቤን መነሻ በማድረግ የጋራ አኗኗር ላይ የተመሰረተ፣ ማህበረሰባዊ አሰራሮችንና ደንቦችን ባማከለ መንገድ የወል እሴቶች ከትውልድ ትውልድ እንዲሸጋገሩ ፍልስፍናው ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ ፍልስፍናው በግለሰብ እና በማህበረሰቡ መካከል ያለውን ጥልቅ ትስስር፣ የጋራ ኃላፊነት፣ ርህራሄ፣ ክብር እና የጋራ ደህንነትን ትልቅ ትኩረት ስለሚሰጥ በጋራ ህልም ላይ የተመሰረተ ማህበረሰብ እንዲኖር አድርጓል፡፡ እንዲሁም እያንዳንዱ ሰው ተፈጥሮአዊ ክብር እንዳለው እና የእሱ ማንነት ከሌሎች ጋር ባለው ግንኙነት እና ለመላው ማህበረሰብ በሚያበረክተው አስተዋፅኦ ላይ እንደሚመሰረት ትውልዱ ላይ ዘርቷል፡፡ ከዚህ አንጻር ሀገር በቀል ፍልስፍናዎችና ዕውቀቶች የተረጋጋና ለሥርዓት የሚገዛ ማህበረሰብ እንዲኖር ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ አምድም ባሳለፍነው ሳምንት ሃሙስ ህዳር 11 ቀን የተከበረውን ዓለም አቀፍ የፍልስፍና ቀንን መነሻ በማድረግ ስለ ኢትዮጵያ ሀገር በቀል ፍልስፍናዎችና ዕውቀቶች እንዲሁም አንድነትና ለጋራ ዓላማ መተባበርን ይበልጥ አጉልተው የሚያሳዩ ሀገር በቀል እሴቶች ላይ አጭር ዳሰሳ አድርገናል፡፡

ኢትዮጵያዊ ገር በቀል እሴቶችና ፍልስፍናዎች

እያንዳንዱ ማህበረሰብ የራሱ የሆነ ፍልስፍና እና እውቀት አለው። ፍልስፍናው በጽሑፍ ብቻ የሚገለጽ አይደለም፡፡ በአኗኗር ይትበሃሉ፣ በማህበራዊ መስተጋብሩ፣ በዕለት ተዕለት ድርጊቶቹና በቃላዊ ተረኮቹ አማካይነት ጎልቶ ይንጸባረቃል፡፡ እንደ አፍሪካ ያሉ ማህበረሰቦች የፍልስፍናቸው መሰረት በቃል የሚተላለፍ ልምድ (Oral Tradition) ላይ ይበልጥ ይመሰረታል። አብዛኛው የሀገር በቀል ፍልስፍና እና ዕውቀት በጽሑፍ ሳይሆን በአፈ ታሪክ፣ በተረት፣ በዘፈኖች፣ በሥርዓቶችና በሽማግሌዎች የቃል ትውፊት ከትውልድ ትውልድ ይተላለፋል። በየዘመኑ የሚነሱ የፍልስፍና ሰዎችም እነዚህን የቃል ትውፊቶች በመተርጎም፣ በማብራራትና ዋጋ በመስጠት ቀጣይነታቸውን ያረጋግጣሉ፡፡ ዕውቀቶቹም ከዘመኑ ሁኔታ ጋር እንዲስማሙ በማድረግ ትውልዱ እንዲማርባቸው ያደርጋሉ፡፡

የፍልስፍና ምሁር ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ በፈረንጆቹ 2005 ለንባብ በበቃው ‘Africa’s Quest for a Philosophy of Decolonization’ መጽሐፋቸው ከአፍሪካውያን ፍልስፍና አንጻር የኢትዮጵያን አስተዋፅኦ ዳስሰዋል፡፡ በዚህ መጽሐፍ መሰረት የኢትዮጵያ ሀገረሰባዊ ፍልስፍና ከተለያዩ ማህበረሰቦች እና ኃይማኖቶች የመጡ ልዩ ልዩ አስተሳሰቦችን ያቀፈ ነው። በዋናነት ግን በኃይማኖት (ክርስትና፣ እስልምና እና በሌሎች ሀገር በቀል እምነቶች)፣ በማህበራዊ እሴቶች እና በጥንታዊ የእውቀት ስርዓቶች ላይ ይመሰረታል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና በእስልምና እምነት ዙሪያ የተገነቡት ፍልስፍናዊ አስተሳሰቦች፣ በዋናነት ስለ ፍትህ፣ ስለ መልካምነት፣ ስለ ጽድቅና ኩነኔ ትምህርቶችን ያንጸባርቃሉ። እንደ ዘርአ ያዕቆብ እና ወልደ ሕይወት ያሉ ፈላስፎች በ17ኛው ክፍለ ዘመን የጻፏቸው ጽሑፎች (በተለይ “ሐተታ ዘዘርዓ ያዕቆብ” እና “ሐተታ ዘወልደ ሕይወት”) በምክንያት (reason) ላይ የተመሰረተ ፍልስፍናን፣ የህሊናን እና የነጻ ምርጫን (free will) አስፈላጊነትን ያብራራሉ። እንዲሁም በተለያዩ የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች የጋራ መሰባሰቢያዎች (ለምሳሌ እንደ እድር፣ እቁብ ያሉ ስርዓቶች)፣ የግጭት መፍቻና የዕርቅ ስርዓቶች፣ ከተፈጥሮ ጋር ጥብቅ መስተጋብር የመፍጠር አስፈላጊነት፣ ለአዛውንቶች ክብር መስጠት እና የጎረቤቶችን መከባበር የሚያጎሉ ፍልስፍናዎች እንዳሏቸው ምሁሩ በመጽሐፋቸው አብራርተዋል፡፡ 

 እንዲሁም አካባቢያዊ የእውቀት ስርዓት (Indigenous Knowledge Systems) በተመለከተ ሀገር በቀል ማህበረሰባዊ ፍልስፍናዎች ጥልቅና ከተፈጥሮ ጋር መስተጋብር መፍጠር ላይ እንደሚመሰረት ፕሮፌሰር መሳይ ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፋቸው ላይ አስፍረዋል፡፡ ከምዕራቡ ዓለም ዘመናዊ ፍልስፍና ጋር በማነጻጸር ምሁሩ እንዳስቀመጡት፣ የምዕራቡ ዓለም ስልጣኔና ፍልስፍና ተፈጥሮን ከማስገበር ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው። በሌላ አገላለጽ ተፈጥሮን አስገብሮ ለራስ ጥቅም ማዋል የሚል ራስ ወዳድነት እንደሚጎላበት አብራርተዋል፡፡ በአንጻሩ የአፍሪካም ሆነ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል ፍልስፍናዎች ከተፈጥሮ ጋር ሚዛን ጠብቆ መኖር ላይ ያተኩራሉ፡፡ ተፈጥሮ ከማህበረሰቡ ህልውና ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው በመሆኑ፣ ተፈጥሮን መበዝበዝ እንደሚቃወም ጽፈዋል፡፡

የባህልና የሰላም ተመራማሪው ወሰን ባዩ (ዶ/ር) ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ ብዝሃ ማህበረሰቦችና ባህሎች ያሉባት ሀገር መሆኗን በማውሳት በርካታ ሀገር በቀል እሴቶችና እውቀቶች አሉ፡፡ በእነዚህ ማህበረሰቦች ውስጥ ለዘመናት የታነጹና ከትውልድ ትውልድ ተሸጋግረው አሁን ያለንበት ዘመን ላይ የደረሱ ጥልቅ የህይወት ፍልስፍናዎችም እንዲሁ። አንድነትን የሚያበረታቱ፣ መተባበርን አጉልተው የሚያንጸባርቁ፣ ራስ ወዳድነት አጥብቀው የሚተቹ፣ ፍትሐዊ መሆንን በተግባር የሚያሳዩ፣ ጥላቻን የሚጠየፉ፣ የሴቶች መብት መከበር እንዳለበት በተግባር የሚያሳዩ፣ የእውቀት አስፈላጊነትንና እንዴት እንደሚገኝ የሚያብራሩ እሴቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

ወሰን (ዶ/ር) የጋሞ አባቶች ከጥቂት ዓመታት በፊት ለተቃውሞ የወጡ ወጣቶች ተቋማት ላይ ጉዳት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ በእጃቸው እርጥብ ሳር በመያዝ ያስቆሙበትን ስርዓት እንደ አብነት በመጥቀስ የሀገር በቀል እሴቶችና የሕይወት ፍልስፍናዎች ሚናን አስረድተዋል። በከፍተኛ ስሜት ውስጥ ሆነው የተንቀሳቀሱት ወጣቶች ከድርጊታቸው የታቀቡት አጋጣሚ የጋሞ ማህበረሰብ የግጭት መፍቻ ሥርዓት ጥልቀት ጥሩ አስረጅ ነው። ማህበረሰቡ ግጭቶችን የሚፈታበትና የተበደለውን የሚክስበት የራሱ የሆነ ዕውቀትና እሳቤ እንዳለው አመላካች ነው፡፡ እንደነዚህ አይነት ሀገር በቀል እሴቶች በተለያዩ የሀገራችን ማህበረሰቦች ውስጥ አሉ። ትውልዱ እንዲያውቃቸው ማድረግ ላይ ይበልጥ መሰራት አለበት። አሁን ካለው በላቀ ሀገር በቀል ፍልስፍናዎችና ዕውቀቶች በትምህርት ተቋማትና ማህበረሰባዊ በሆኑ የዕውቀት ማስተላለፊያ መድረኮች ላይ መወያያ ርዕሰ ጉዳዮች መሆን አለባቸው። ምክንያቱም  ወጣቱ ትውልድ የራሱን እሴቶች እንዲያውቅና እንዲጠብቅ ያደርጋል። ይሄ ደግሞ በእጅ አዙር ቅኝ ግዛትና በሉላዊነት ምክንያት የሚመጣውን የባህል መሸርሸር ለመከላከል ያግዛል ብለዋል፡፡

ሌላው የሀገር በቀል ባህሎችና ፍልስፍናዎች ሚና ማህበረሰቦች ከዘመናዊነት፣ ከሉላዊነትና ከውጭ ጫናዎች ጋር በተያያዘ ለሚገጥሟቸው ፈተናዎች ትርጉም ያለው ምላሽ እንዲሰጡ እንደሚያግዝ ምሁሩ ተናግረዋል። ባህላዊ እሴቶች ከዘመናዊ ሕይወት ጋር እንዴት ሊጣጣሙ እንደሚችሉ በመተንተን፣ የባህሉን ዋና ማንነት ሳይለቁ እንዲለወጡ ያስችላል። ሀገር በቀል ፍልስፍናዎች ማህበረሰቡ ከተፈጥሮ ጋር የጠበቀ መስተጋብር እንዲኖረን ያበረታታሉ፡፡ ይሄ ደግሞ የትውልዱን ሥነ-ምህዳራዊ ዕውቀት ለማሳደግ ቁልፍ ሚና እንዳለው  ወሰን (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡

ሌላው የኢትዮጵያ ባህላዊ የዕርቅ ስርዓት ጥልቅ የሆኑ የፍትህ እሳቤዎች በውስጣቸው እንደያዙ ያወሱት ዶ/ር ወሰን ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች የተለየ ገጽታ እንዳላቸው አብራርተዋል፡፡ መደበኛው ፍርድ ቤት ከሳሽና ተከሳሽን ያከራክራል። ጥፋተኛውን ይቀጣል፡፡ ተጎጂውን ህጉ ባስቀመጠው መሰረት ይክሳል፡፡ ከዚህ በኋላ ያለው ጉዳይ ግን መደበኛ ፍርድ ቤቶች ብዙም አይመለከታቸውም። ሀገር በቀል የእርቅ ስርዓት ግን ከዚህ የተሻገረ ፍልስፍናዊ የፍትህ እሳቤ አለው። አጥፊውን ከቀጣና ተጎጂውን ከካሰ በኋላ በከሳሽና በተከሳሽ መካከል ቂም በቀልን በሚያስቀር መልኩ ችግሩን ከስር መሰረቱ መፍታት ላይ እንደሚያተኩር አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይ በኢትዮጵያ የፍትህ ሥርዓት ውስጥ ሀገር በቀል የግጭት አፈታትና የእርቅ ስርዓቶች አስፈላጊነታቸውን በመገንዘብ ተገቢው ዕውቅና እንደተሰጣቸው የገለጹት ወሰን (ዶ/ር)፣ በአካባቢው የግጭት መፍቻ ስርዓት መፈታት የሚችሉት ግጭቶች እዚያው እንዲፈቱ ያበረታታል ብሏል፡፡

ስለሀገር በቀል እሴቶችና ፍልስፍናዎች ካነሳን ዘንድ በኦሮሞ ባህል ውስጥ ስለሚታወቀው ስለ ሲንቄ በጥቂቱ እናውጋ፡፡ በገዳ ሥርዓት ዙሪያ የተጻፉ ሰነዶች እንደሚያመለክቱት፣ ከገዳ ስርዓት ውስጥ ሲንቄ አንዱ ነው። ሲንቄ  ለአንዲት ኦሮሞ ሴት በጋብቻዋ ቀን በወላጅ እናቷ እንደ ክብር መገለጫ ተደርጎ የሚሰጣት ቀጭን በትር አለ። ሴቶች በማህበረሰቡ ውስጥ የመብት ጥሰት በሚፈጸምባቸው ወቅት ተሰባስበው ሲንቄያቸውን በመያዝ ተቃውሞአቸውን ያሰማሉ፡፡ ስለዚህ ሲንቄ የኦሮሞ ሴቶች በደል ሲደርስባቸው መብታቸውን ለማስከበር የሚጠቀሙበት ተምሳሌታዊ የፍትህ ፋይዳ ያለው በትር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሁለት ወገኖች መካከል ግጭት ሲፈጠር በትሩን ይዘው መሀል በመግባት የተፈጠረውን ግጭት ለማብረድ ይጠቀሙበታል፡፡

በጅማ ዩኒቨርስቲ የማህበራዊ ሳይንስ መምህር ዋርዮ ዋኮ በዚሁ ጉዳይ ላይ ከዚህ ቀደም ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አስተያየት ጎረቤታሞች ከተጋጩ ሴቶች ሲንቄ ይዘው መሃል ይገባሉ፡፡ ወዲያው ግጭቱ ይቆማል፡፡ የሴቶቹን ጣልቃ ገብነት አልፎ በጥሉ የሚቀጥል ካለ ነውር ፈፀመ ይባላል፡፡ ሲንቄ የያዘች ሴት ክቡር ናት። ክብር ይሰጣታል፡፡ ይሄ ማለት ደግሞ ጠንካራ መብት አላት በማለት እንደ ሲንቄ ያሉ ሀገር በቀል ዕውቀቶች ያላቸውን ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ አብራርተዋል፡፡

ከዚህ አንጻር ሀገር በቀል ዕውቀቶችና ፍልስፍናዎች ለዛሬው ህይወታችን ጭምር ጉልህ አስተዋጽኦ የማድረግ ዕምቅ አቅም አላቸው፡፡ ለሀገር በቀል እውቀቶችና ፍልስፍናዎች ተገቢውን ትኩረት በመስጠትም ከውጭ የሚመጡ የባህል ወረራዎችን ለመከላከል ኹነኛ መፍትሔ ነው፡፡

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review