• በከተማዋ የ2018 ዓ.ም 532 ሺህ 199 ኪሎ ግራም የማር ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑ ተጠቁሟል
ከቅርብ ጊዜያት በአዲስ አበባ የከተማ ግብርና ስራ በስፋት የሚተገበር ሆኗል፤ በሰብል፣ በጓሮ አትክልት፣ በዓሳ ምርት፣ በዶሮና እንቁላል እንዲሁም በወተትና በወተት ተዋፅኦ ምርቶች ላይ በርካቶች ተሰማርተዋል። ነዋሪዎችም በጓሯቸው በበረንዳቸው፣ በቤቶቻቸው ጣርያና ግድግዳ አትክልቶችን በማብቀል ብቻ ሳይሆን ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን በመጠቀምም የማር ምርት ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል፡፡ በተለይ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ተግባራዊ ከሆነ ወዲህ የንብ ማነብ ተግባር ከፍተኛ መነቃቃትና ለውጥ አሳይቷል፡፡
በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 በተለምዶ አንቆርጫ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ንብ በማነብ ስራ የተሰማሩት አቶ መስፍን ሰይፉ አንድ አብነት ናቸው። ቀደም ሲል በባህላዊ ቀፎ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ንብ የማነብ ስራን የጀመሩት ተጠቃሚው በተጠናከረ መንገድ መስራት የጀመሩት ግን ከሦስት ዓመት ወዲህ እንደሆነ ይናገራሉ። አሁን ከ20 በላይ ዘመናዊ ቀፎ ያላቸው አቶ መስፍን በማር ምርት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ንብ ማነብ ገጠር፣ ከተማ፣ ሰፊና ጠባብ ቦታ ሳይባል በየትኛውም ሁኔታና አካባቢ እንደሚቻልና ጠንክሮ ከተሰራ ከቤተሰብ ፍጆታ ባለፈ በኢኮኖሚ ረገድም ተጠቃሚ ያደርጋል የሚሉት አቶ መስፍን፣ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ብቻ ወደ 200 ሺህ ብር የሚጠጋ ገቢ ከማር ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ንብ የማነብን ስራ ቀደም ሲል በባህላዊ መንገድ ከቤተሰባቸው ጋር ሲያከናውኑ እንደነበርና አሁን ላይ ግን በግላቸው ስለዘርፉ ለማወቅና አስፋፍተው ለመስራት ባደረጉት ጥረት ከ20 በላይ ዘመናዊ ቀፎዎችን አዘጋጅተው ከእርሳቸው በተጨማሪ ለሁለት ሰዎች የስራ እድል በመፍጠር ስራቸውን እየሰሩ ይገኛሉ። በንብ ማነብ የተሻለ የማር ምርት ተጠቃሚ ለመሆን ለንቦቹ በቂ ውሃና ምግብ ከማቅረብ በተጨማሪ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ማሟላት ከምንም በላይ ደግሞ የራስ ተነሳሽነትን ይጠይቃልም ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 10 ነዋሪ የሆኑት አቶ ጥጋቡ ሽታነህ በንብ ማነብ ስራ ተሰማርተው የጥቅሙ ተቋዳሽ ሆነዋ፡፡ ለረጅም ጊዜ ንብ ማነብን ሲሰሩ እንደቆዩ የሚገልጹት አቶ ጥጋቡ፣ የሌማት ትሩፋት ከጀመረ ወዲህ በተቀናጀ መንገድ ንብ በማነብ በማር ምርት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
በ30 ባህላዊና ዘመናዊ ቀፎ ንብ የሚያንቡት እነ አቶ ጥጋቡ ከሶስት ዓመት ወዲህ “ጥጋቡና ጓደኞቹ የንብ እርባታ ማህበር” በሚል ስያሜ አምስት ሆነው በማህበር ተደራጅተው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ የንብ እርባታ ስራውን በዘመናዊ መንገድ የሚሰሩት እነ አቶ ጥጋቡ የራሳቸው የማር መጭመቂያ እና ማጣሪያ ማሽን አላቸው፡፡ የመብራት እና የውሃ አቅርቦት ድጋፍ ቢሟላላቸው ስራውን በደንብ በመስራት ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡
ለንቦች ምግብነት የተለያዩ አበባዎችንና የአበባ ዛፎችን በመትከል እንደሚመግቡ ገልጸው፣ በዚህም የተሻለ የማር ምርት እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡ በንብ ማነብ የማር ምርት ተጠቃሚ ለመሆን ቅድሚያ የራስ መነሳሳት እና ፍላጎት ወሳኝነት አለው የሚሉት አቶ ጥጋቡ፣ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ውጤታማ መሆን እንደሚቻልም አስረድተዋል። በማር ምርት ከምግብነት ባለፈ ለገበያ በማውጣት በሽያጭ ተጠቃሚ ለመሆን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
ንብ አናቢዎች ቀፎ ብቻ በማስቀመጥ በዓመት የማር ምርት ተጠቃሚ መሆን እንደማይቻል አቶ ጥጋቡ ገልጸው፣ የንብ መንጋውን በእንክብካቤ ጠብቆ በመያዝና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በዓመት ጥራትና ብዛት ያለው የማር ምርት ማግኘት ይቻላል ይላሉ፡፡
ባለፈው ዓመት 30 ኪሎ የማር ምርት እንዳገኙ እና አንድ ኪሎ በ700 ብር ሂሳብ እንደሸጡ አውስተው፣ የግብዓት ድጋፍ ቢደረግላቸው የንብ እርባታ ስራቸውን ከዚህ በበለጠ አስፋፍተው በመስራት የማር ምርትን በብዛት በማምረት ወደ ገበያ እንደሚያቀርቡ ይናገራሉ፡፡
ወይዘሮ ብርቱካን ሀይለማሪያም በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 7 ነዋሪ ናቸው፡፡ በወንዝ ዳርቻ አካባቢ ሸንኮራ ቁጥር 1 እና ቁጥር 2 በከተማ ግብርና ዘርፍ በማህበር በመደራጀት በንብ ማነብ እና በጓሮ አትክልት ስራ ተሰማርተዋል፡፡ 88 ሴቶች ሆነው በማህበር በመደራጀት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ንብ ማነብ የጀመሩት እነ ወይዘሮ ብርቱካን በንብ ማነብ የጥቅሙ ተጋሪ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 አርሶ አደርና የከተማ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ያደታ ዋቁማ፣ አካባቢው በደን የተሸፈነ በመሆኑ ለንብ ማነብ ስራ አመቺ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ንብ ማነብ ተፈጥሯዊ አካባቢን እንደሚፈልግ ጠቁመው፣ ወረዳው ለዚህ ስራ ተስማሚ አካባቢ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በተለምዶ ጂፋራ ተብሎ በሚጠራው የየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 አከባቢ የሚኖሩ 40 አርሶ አደሮች ከሌሎች የከተማ ግብርና ስራዎች ጎን ለጎን ንብ በማነብ ዘርፍ መሰማራታቸውን ጠቅሰው፣ በ70 ዘመናዊ ቀፎዎች የንብ ማነብ ስራን እያከናወኑ ያሉት አንድ አርሶ አደር ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የስራ እድል መፍጠራቸው በማር ምርት ረገድ ትልቅ ተስፋ መኖሩን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
ከነዚህ በተጨማሪም በወንዝ ዳርቻዎች አካባቢ ከ20 መቶ የሚበልጥ ዘመናዊ ቀፎ በመጠቀም ንብ በማነብ የተሰማሩ 15 አባላት ያሏቸው ሶስት ማህበራትና ግለሰቦች መኖራቸውን አውስተው፣ ከእነዚህም ከባለፈው በጀት ዓመት የተሻለ የማር ምርት እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
የጉለሌ ክፍለ ከተማ አርሶ አደርና የከተማ ግብርና ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሳልፋኮ ሻኖ የማር ምርት እንደ ከተማ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን በማንሳት ጉለሌ ክፍለ ከተማ የእንጦጦ ተራራን ጫካ የሚያዋስን አካባቢ በመሆኑ ለንብ እርባታ ተስማሚ ነው፡፡ በእንጦጦ ተራራ እና በዙሪያው ባሉ አካባቢዎች የንብ እርባታ በማከናወን በማር ምርት ተጠቃሚ ለመሆን እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለአካባቢ ጥበቃ ልማት በተሰሩ የውበት እና የአረንጓዴ ቦታዎች ላይ የንብ እርባታ ስራ እየተከናወነ መሆኑን በመጠቆም፣ የ120 ቀናት እቅድ በማቀድ በአዲስ መልኩ ወደ ስራ ለማስገባት እና ነባር ተጠቃሚዎችን ደግሞ ለመደገፍ የዘርፉን ባለሙያዎች በመመደብ እየተሰራ ነው፡፡ ነዋሪዎች እና ተቋማት በንብ ማነብ ተሳትፎ ለማድረግ ከጊዜ ወደ ጊዜ ፍላጎታቸው እየጨመረ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በጉለሌ ክፍለ ከተማ የእንስሳት ሀብት ባለሙያ አቶ በላቸው ንጉሴ አንድ ተጠቃሚ በአማካይ አምስት ቀፎች እንዳሉት ገልጸው፣ በማህበር ደግሞ ከአንድ ማህበር በአማካይ 20 ቀፎች እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡ ለንብ አናቢዎች የቀፎ፣ የአልባሳትና የስልጠና ድጋፍ እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ንቦች ምቹ ሁኔታ ስለሚፈልጉ ውጤታማ እንዲሆኑ ከቦታ ዝግጅት ጀምሮ አበባ እና ሌሎችን ግብዓቶችን እንዲያሟሉ ሙያዊ ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡
በክፍለ ከተማው በ2017 ዓ.ም 30 ሺህ 295 ኪሎ ግራም የማር ምርት መገኘቱን ጠቁመው፣ በ2018 ዓ.ም 38 ሺህ 384 ኪሎ ግራም የማር ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል፡፡ በ1ኛው ሩብ ዓመት በግልም ሆነ በማህበር ከተደራጁ አናቢዎች 7 ሺህ 50 ኪሎ ግራም የማር ምርት ተገኝቷልም ብለዋል።
በአርሶ አደርና የከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን የእንስሳት ሃብት ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ደጀኔ ጌታቸው በሌማት ትሩፋት ትኩረት ከተሰጠው አንዱ የማር ምርት መሆኑን አንስተው፣ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ወረዳዎች የንብ ማነብ ስራው እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
እንደ ዶክተር ደጀኔ ገለጻ፣ ለተጠቃሚዎች እና ለባለሙያዎች ስልጠና መስጠት፣ የቦታና የብድር አቅርቦት የማመቻቸት ስራ ይሰራል፡፡ ነባር የከተማ ንብ አናቢዎች፣ ሥራ-አጥ ወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎች ባለሃብቶች ማርና ሰም በማምረትና ህብረ ንቦችን አባዝቶ በመሸጥ ገቢያቸውን በማሳደግ የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡና ሀብት እንዲፈጥሩ ለማስቻል በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡
እንደ ኮሚሽኑ መረጃ በከተማዋ በንብ እርባታ በማህበር እና በግለሰብ ደረጃ 1 ሺ 801 ተጠቃሚዎች ይገኛሉ፡፡ በዚህም በ2017 ዓ.ም 420 ሺህ 46 ኪሎ ግራም የማር ምርት ተገኝቷል፡፡ በተያዘው የ2018 የምርት ዘመን ደግሞ 532 ሺህ 199 ኪሎ ግራም የማር ምርት ይገኛል ተብሎ ይገመታል፡፡
በይግለጡ ጓዴ