የታላቁ ሩጫ የሩብ ክፍለ ዘመን ጉዞ ሲቃኝ

You are currently viewing የታላቁ ሩጫ የሩብ ክፍለ ዘመን ጉዞ ሲቃኝ

‘ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ’ (Great Ethiopian Run – GER) በአፍሪካ ትልቁ የ10 ኪሎ ሜትር የመንገድ ላይ ሩጫ ሲሆን፣ የተመሰረተውም በኦሎምፒክ ባለታሪኩ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ እና ባልደረቦቹ ነበር፡፡ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ከሲድኒ ኦሎምፒክ በኋላ ባገኘው መነሳሳት እና ሀሳብ የመጀመሪያው ሩጫ የተጀመረ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ሩጫ በ10 ሺህ ተሳታፊዎች ተጀምሮ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ትልቁ የመንገድ ላይ ሩጫ መሆን ችሏል፡፡

የኢትዮጵያ መለያ እየሆነ የመጣው ታላቁ ሩጫ ከተመሰረተበት ከ1994 ዓ.ም አንስቶ እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ በድምሩ ከ700 ሺህ በላይ ተሳታፊዎችን ማስተናገዱን መረጃዎች ያሳያሉ። በዓለም የአትሌቲክስ ውድድር የገዘፈ ስም ባለው አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ የተጀመረው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከ10 ሺህ ያነሱ ተሳታፊዎች የነበሩት ሲሆን፤ ባለፉት ዓመታት ውድድሩ 50 ሺህ የሚጠጉ ተሳታፊዎችን አስተናግዷል።

ከታላቁ ሩጫ በፊት ሩጫ የጥቂት ሯጮች ማለትም የእነ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ደራርቱ ቱሉ ስራ ተደርጎ ይወሰደ የነበረ ሲሆን፣ ዛሬ ላይ ታላቁ ሩጫ በፈጠረው ተጽዕኖ ምክንያት ለቤተሰቦች፣ ለተማሪዎች፣ ለቢሮ ሰራተኞችና በአጠቃላይ ሩጫ ለሁሉም ሰው ስለመሆኑ ጠንካራ ግንዛቤ ተፈጥሯል። አትሌት ኃይሌ እንደሚገልፀው ከሆነ የሩጫ ዝግጅት የመፍጠር ቀላል ህልም የነበረው ታላቁ ሩጫ፣ ባለፉት 25 ዓመታት ግን የኢትዮጵያን የአትሌቲክስ ባህል ሙሉ በሙሉ የቀየረ ሆኗል።

በዓለም ላይ ከሚከናወኑ የጎዳና ውድድሮች ምርጡ በመባል የተመረጠው ታላቁ ሩጫ፣ በኢትዮጵያ ለበርካታ አትሌቶች የስኬታቸው ምክንያት መሆን ችሏል፡፡ ውድድሩ መሰናዳት ከጀመረ በኋላ በርካታ አትሌቶች በዚህ ውድድር ላይ አልፈው ስኬታማ መሆን ችለዋል። አትሌት አሰለፈች መርጋን በዚህ ረገድ በአስረጅነት መጥቀስ ይቻላል። አትሌቷ መጀመሪያ ውድድር ማድረግ የጀመረችው በታላቁ ሩጫ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ሀገሯን ወክላ ከመካፈል ባሻገር ባመጣችው ስኬት ለሌሎችም መትረፍ ችላለች፡፡

በአፍሪካ ትልቁ የጎዳና ላይ ሩጫ እንደሆነ የሚነገርለት ውድድር ታላቁ ሩጫ ከኢትዮጵያውያን ባሻገር ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ የውጪ ሀገራት ዜጎችም የሚሳተፉበት ሆኗል። በተለያየ ወቅት የዓለም ታላላቅ አትሌቶች ውድድሩን በክብር እንግድነት በማስጀመር የተሳተፉ ሲሆን፣ ለአብነትም ፖል ቴርጋት፣ ገብርኤል ዛቦ፣ ካሮሊና ክሉፍት፣ ዴቭ ሞርክሩፍት እና ፓውላ ራድክሊፍ ይጠቀሳሉ፡፡ በውድድሩ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ስለሺ ስህን፣ ጸጋዬ ከበደ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ ወርቅነሽ ኪዳኔና ጥሩነሽ ዲባባ ማሸናፋቸው ይታወሳል፡፡

የቀድሞው የማራቶን የዓለም ሬኮርድ ባለቤት እና የቺካጎ ማራቶን የአራት ጊዜ አሸናፊው አሜሪካዊ ካሊድ ካኑቺ እንዲሁም የወቅቱ የማራቶን የዓለም ሻምፒዮን ኬኒያዊቷ ፔሬስ ጄፕቺርቺር ነገ (ህዳር 14 ቀን 2018 ዓ.ም) በአዲስ አበባ በሚካሄደው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 25ኛ ዓመቱን በሚያከብርበት ውድድር ላይ በእንግድነት እንደሚገኙ አረጋግጠዋል፡፡

ካኑቺ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ስለሚያደርገው ጉዞ ሲናገር “በተወዳዳሪነቴ ወቅት ከብዙ ኢትዮጵያውያን ጋር የመለማመድ እና የመወዳደር እድል ነበረኝ፡፡ ጠንካራ ሰራተኝነታቸው እና ለሩጫ ያላቸው ፍቅር ለስኬታቸው ዋነኛ ምክንያት ነበሩ። ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ መገኘት እና በዚያ ያሉ ጓደኞቼን ማግኘት አጓጉቶኛል” ብሏል፡፡

ለ2025 የሴቶች ከስታዲየም ውጪ የዓመቱ ምርጥ አትሌትነት የታጨችው ኬኒያዊቷ የማራቶን ኮከብ ፔሬስ ጄፕቺርቺርም ከ8 ዓመት ሴት ልጇ ናታሊያ ጋር ወደ አዲስ አበባ ትመጣለች። በቶኪዮ የኦሎምፒክ ማራቶንን ካሸነፈች አንድ ዓመት በኋላ በ2015 ዓ.ም በታላቁ ሩጫ ላይ ተገኝታ የነበረችው ጄፕቺርቺር፣ በእዚያው በቶኪዮ ኢትዮጵያዊቷ ተፎካካሪዋ ትዕግስት አሰፋን በጥቂት ሰኮንዶች ቀድማ በማራቶን የዓለም ሻምፒዮንነትን ከተቀዳጀች ሁለት ወራት ብቻ ተቆጥረዋል።

በሶስት የዓለም የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮናዎች ሶስት የግል የወርቅ ሜዳሊያዎችን ያሸነፈችው ጄፕቺርቺር አሁን የአራት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ስትሆን በቦስተን፣ ኒው ዮርክ እና ለንደን በማሸነፍ የሶስት-ጊዜ የዓለም ሜጀር ማራቶን ባለድል ነች ፔሬስ ጄፕቺርቺር፡፡

በየዓመቱ ህዳር ወር ላይ የሚካሄደው ታላቁ ሩጫ ከአትሌቲክስ ውድድርነቱ ባለፈ መልከ ብዙ ፋይዳዎች ያሉት ሲሆን፣ በተለይም የኢትዮጵያን በጎ ገጽታ ለዓለም በማስተዋወቅ በኩል ያለው አበርክቶ ከፍተኛ ስለመሆኑ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ማርኬቲንግ ማናጀር ወይዘሮ ህሊና ንጉሴ ይገልጻሉ፡፡ በተለይም በቱሪዝም፣ በኢኮኖሚ፣ ተተኪ አትሌቶችን በማፍራትና በሌሎች መስኮች ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎችን እያስገኘ እንደሚገኝ ተነግሮለታል፡፡ 

የታላቁ ሩጫ ኦፕሬሽን ዳይሬክተር ዳግም ተሾመ በበኩሉ የኮሪደር ልማቱ የውድድሩ ተሳታፊዎች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን ይገልጻሉ። አብዛኞቹ የከተማዋ መንገዶች ከኮሪደር ልማቱ በፊት ለእግረኞች የተለየ መሄጃ የሌላቸውና ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ ምቹ እንዳልነበሩ አስታውሰዋል፡፡ የኮሪደር ልማቱ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በተለይም የመሮጥ ባህልን ለማስፋፋት እና ሰፊ ህዝብ የሚሳተፍባቸውን ውድድሮች ለማዘጋጀት ከፍተኛ አቅም ፈጥሯል። የኮሪደር ልማቱ ለስፖርቱ የሚያገለግሉ መንገዶችን በመያዙ የታላቁ ሩጫ ውድድር ተሳታፊዎችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ እንዳስቻለ ተነግሯል።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋነኛ ዓላማ ሩጫን የአኗኗር ዘይቤው ያደረገ ማህበረሰብ መፍጠር ስለመሆኑ እና በየዓመቱም የተለያዩ መልዕክቶችን በመቅረጽ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች በታላቁ ሩጫ መድረክ እንደሚሰራ የታላቁ ሩጫ አዘጋጆች ያስረዳሉ፡፡ በሌላም በኩል ለአትሌቶች ውድድር ዕድል ከመፍጠሩ ባሻገር፣ በህብረተሰቡ ዘንድ ‘ፌስቲቫል’ ተደርጎ ተቆጥሯል፡፡ ጤናን ለመጠበቅና ለመዝናናት የሚካፈሉት በርካቶች ናቸው፡፡

ከአስር ጊዜ በላይ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር ላይ የተሳተፈው ቢኒያም  ምንዳዬ እንደሚያስረዳው የታላቁ ሩጫ ተሳትፎው ብዙ ማስታወሻዎችና ትዝታዎች እንዳሉትና በየዓመቱ እንደ አንድ መዝናኛ ፕሮግራም ቆጥሮት ተሳትፎ እንደሚያደርግ ያስረዳል፡፡ ከመዝናናቱም ጎን ለጎን የሩጫ ብቃቱን ለማሻሻል እንደረዳውና ስፖርታዊ እንቅሰቃሴን ልምድ እንዲያደርግ እንዳገዘው ይገልጻል፡፡

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለብዙ አትሌቶች ዋነኛ የውድድር ምንጭ ሆኖም ቆይቷል። በየዓመቱ የልጆችን ውድድር ጨምሮ ከስድስት በላይ የሩጫ ውድድሮችን በማስተናገድ የሚታወቀው ታላቁ ሩጫ፣ በእንጦጦ ፓርክም የስፖርት ማህበረሰብ ለመፍጠር በየጊዜው የብዙሃን ሩጫ በማካሄድም ይታወቃል፡፡ በዚህ ረገድ የታላቁ ሩጫ ማርኬቲግ ማኔጀሯ ወይዘሮ ህሊና እንዳሉት የመርሃ ግብሩ ዋነኛ ስኬት ተብለው ከሚጠቀሱ ጉዳዮች መካከል በርካታ ተሳታፊች ከውድድሩ አስቀድሞ ለወራት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረጋቸው ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡

የሩጫ ውድድሩ በአዲስ አበባ ብቻም ሳይወሰን በሐዋሳ፣ ጂማ፣ በቆጂ እና አርባ ምንጭ ተመሳሳይ ሩጫዎችን እንዲፈጠሩ ያነሳሳ ሲሆን፣ ዘንድሮ በደብረ ብርሃን እና በሐረር አዳዲስ ውድድሮች እንደሚጀመሩ ተገልጿል። በዚህም በርካታ የኢትዮጵያ ታላላቅ አትሌቶች የመጀመሪያ የውድድር ተሞክሯቸውን ያገኙበት ‘መነሻ ነጥብ’ ሆኖ አገልግሏል። ውድድሩ ለወደፊቱ ራዕዩ፣ በቀጣዮቹ 25 ዓመታት በ50ኛው የምስረታ በዓል አንድ ሚሊዮን ሯጮችን ለማሳተፍ ህልም እንዳለው ተገልጿል።

ከዓለም አትሌቲክስ ዓለም አቀፋዊው ተቋም የሌብል ደረጃ ሲል ከሰየማቸው ውድድሮች መካከል የሆነው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሚከተሉተን ጉዳዮች በመፈጸሙ እንደሆነም ተነግሯል። ውድድሮች መሥፈርቱ ዝግጅቶችን በጥራት ከማድረግ፣ ደህንነታቸው የተጠበቀ ከመሆንና የተሳታፊዎች ውድድሩ ላይ የነበራቸው ቆይታ፣ የከተማ አስተዳደሮች ለዝግጅቱ ያላቸውን ድጋፍ፣ እንዲሁም ዝግጅቱ በአትሌቲክስ ውድድር ዘርፍ አበረታች መድኃኒት ላይ ለመሥራት ያለውን ቁርጠኝነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከዓለም አትሌቲክስ ዕውቅና ተሰጥቶታል፡፡

በታላቁ ሩጫ ታሪክ የተመዘገቡት ክብረወሰኖች በሴቶች አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው በ2015 ዓ.ም 10 ኪሎ ሜትሩን በ31፡15.51 ያሸነፈችበት ሲሆን፣ በወንዶች እንደዚሁ በ1999 ዓ.ም ድሪባ መርጋ በ28፡18.61 ያሸነበት ውድድር ነው። በ24ተኛው ታላቁ ሩጫ ውድድር በወንዶች አትሌት ቢንያም መሐሪ እና በሴቶች አትሌት አሳየች አይቼው  አሸናፊ አትሌቶች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ25 ዓመት ጉዞ ከቀላል ውድድርነት አልፎ የኢትዮጵያን ስም ከማስጠራት፣ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን ከማስፋፋት፣ እንዲሁም ሀገራዊ አንድነትን እና ኩራትን ከማንፀባረቅ አንፃር ትልቅ ስኬት አስመዝግቧል።

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review