የከተማዋ ነዋሪዎች በብዛት የሚሳተፉበት መነሻውን እና መድረሻውን መስቀል አደባባይ ያደረገው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቀው ወደ ስራ መግባታቸውን አስታውቀዋል።
በአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተደረገው ውይይት ላይ የፀጥታ ሁኔታ እቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል ።
በ2018 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የተከናወኑ የአደባባይ ኩነቶች ያለ ምንም የፀጥታ ችግር በሰላም መከናወናቸውን ያስታወሰው ጥምር የፀጥታ ሀይሉ ዘንድሮ በሚደረገው የታላቁ ሩጫ ውድድሩ ላይ ለመድገም ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን ተገልጿል ።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፋንታ እንደተናገሩት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የከተማውን ገፅታ ግንባታ ከማሳደግ አንፃር ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

ሩጫዉ እንደሌሎቹ የአደባባይ ኩነቶች ትኩረትን በሚጠይቅ ጠንካራ ፀጥታ የማስከበር ሥራ እንደሚከወን ገልፀዋል።
በሩጫ ውድድሩ አብዛኛው የከተማው ወጣቶች በስፋት የሚሳተፉበት በመሆኑ በትብብር መንፈሰ ፀጥታን የማስከበሩ ተግባር ይከናወናል ተብለዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው እንደተናገሩት የከተማውን ሠላም እና ፀጥታ በዘላቂነት ለማስጠበቅ የፀጥታ ሃይሉ እያከናወነ ባለው ተግባር ውጤት እየተገኘ መሆኑን ጠቁመው እየተገኘ ለሚገኘው ውጤት የህብረተሰቡ ተባባሪነት የላቀ አሰተዋፅኦ እንዳለው አስታውሰዋል ።
ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው አያይዘውም ህዳር 14 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄደው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በስኬት አንዲጠናቀቅ የፀጥታ ሃይሉ ለሚከናውነው ተግባር የህብረተሰቡ ተባባሪነት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።
አካላዊ ፍተሻን ጨምሮ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ጠንካራ ቁጥጥርና ክትትል እንደሚደረግ ገልፀዋል ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው በከተማው ዘላቂና አስተማማኝ ሠላም ለመምጣት መዲናችንን የሚመጥን ስራ እየተሰራ መሆኑን በመግለፅ የከተማችን ፀጥታ ሁኔታ የማይመቻቸው ህገወጦች ላይ ጥብቅ ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን ተናግርዋል ።
ለደህንነት ስጋት የሆኑ አካባቢዎችና ለፀረ ሰላም ሃይሎች ምቹ ሁኔታ የሚጥሩ ሁኔታዎችን በመለየት ከህብረተሰቡ ጋር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀው ለሩጫ ውድድሩ ሠላማዊነት የህብረተሰቡ በተለይም የተሳታፊዎች ተባባሪነት ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል ።
የፌዴራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ፣ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ፣ የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ከፍተኛ እና መካከለኛ የስራ ሀላፊዎች በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል።
በዕለቱ ከፕሮግራሙ ጋር የማይገናኙ የተከለከሉ ህገ ወጥ ነገሮችን እና ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን ማስተላለፍ ፈፅሞ የተከለከለ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን የፀጥታ ሃይሉ ተገቢውን የቁጥጥር ሥራ እንዲሰራ ለአባላቱ ኦሬንቴሽን ተሠጥቶ ሥምሪት መዉሰዱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አስታዉቋል።