የትውልድ ድምፅ በሆነው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በሶስት ዘርፎች ማለትም በድምፅ፣ በትወናና በሰርከስ ሲካሄድ የቆየው የአዲስ ታለንት ሾው ውድድር በዛሬው ዕለት በሙዚቃው ዘርፍ አሸናፊዎችን ይፋ አድርጓል።
ወሎ ያበቀላት ኮምቦልቻ ከተማ ተወልዳ ያደገችው እና አሁን ላይ ነዋሪነቷን አዲስ አበባ ያደረገችው ሀያት በውድድሩ የሬጌ ፣ሶልና ብሉዝ የሙዚቃ ስራዎችን አቅርባለች ፡፡

በአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ምሩቅ የሆነችው ሀያት የሙዚቃ ህይወቷ የሚጀምረው በዩኒቨርሲቲው በተቋቋመው በብራና አርት ክለብ ውስጥ ነው፡፡
ሀያት በትምህርቷ ምስጉን እና ታታሪ ተማሪ እንደነበረች ይነገርላታል፡፡
ከልጅነቷ ጀምሮ መፅሃፍ ማንበብ እና ፅሑፎችን መፃፍ እንደምትውድ እና በነበረችበት ትምህርት ቤት ውስጥም መፅሃፍቶችን በማሰባሰብ የመፅሃፍ ክበብ እስከ ማቋቋም ደርሳላች ::
ለኪነ-ጥበብ የተሰጠችው ሀያት ከድምፃዊነቷ ባሻገር የሙዚቃ ግጥሞችን የመፃፍና ስዕል የመሳል ተስጥዖ ባለቤት ነች ።

በመጨረሻዎች 4 ተወዳዳሪዎች መካከል ከባድ ፍልሚያ የተደረገበት የአዲስ ታለንት ሾው ለሙዚቃ ዘርፍ አሸናፊነት በተደረገው ውድድር ላይ ሀያት ረመዳን ባቀረበቻቸው ሶስት ሙዚቃዎች ውድድሩን በአንደኝነት በማጠናቀቅ የ300 ሺ ብር ሽልማት አሸናፊ ሆናለች ፡፡
ብርቱ ፉክክር በታየበት በዚህ ዘርፍ አባይነሽ ሀይሌ ሁለተኛ በመውጣት የሁለት መቶ ሺህ ብር እንዲሁም ናትናኤል በየነ ሶስተኛ በመውጣት የአንድ መቶ ሺህ ብር ተሸላሚ መሆን ችለዋል።
ለሰባት ተከታታይ ዙሮች ሲካሄድ የቆየው የአዲስ ታለንት ሾው ውድድር ለበርካታ ወጣቶች ተሰጥዖዎቻቸውን ወደ መድረክ እንዲያመጡ ዕድል የሰጠ ነው። በውድድሩ የአብስራ ሳሙኤል አራተኛ በመሆን አጠናቋል።