ሀሞት ከጉበት የሚመረት ተፈጥሮአዊ ፈሳሽ ሲሆን ቅባታማ የሆኑ ምግቦች በሚገባ ተፈጭተው ወደ ሰውነት እንዲዋሀዱ ያደርጋል፣ ቆሻሻን ከሆድ ውስጥ ያስወግዳል እንዲሁም ከጨጓራ የሚመነጭ አሲድን ለመቀነስ ይረዳል፡፡
በቀን ከግማሽ ሊትር በላይ ሀሞት በጉበት አማካኝነት ይመረታል፤ ከተመረተ በኃላ ለተወሰነ ጊዜ በሀሞት ከረጢት ውስጥ በመቆየት ለምግብ መፈጨት ሂደት በሚፈልግበት ወቅት ወደ አንጀት ይለቀቃል፡፡
የሀሞት ከረጢት የሚገኘው በጉበት የታችኛው ክፍል ሲሆን፣ ሥራውም ሀሞትን በማጠራቀም ምግብ በሚፈጭበት ጊዜ እየመጠነ ወደ ትንሹ አንጀት መልቀቅ ነው፡፡
የቀዶ ህክምና እና የላባራስኮፒ ስፔሻሊስት ሀኪም የሆኑት ዶ/ር ከንዙ በድሩ ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቆይታ የሀሞት ጠጠር በሀሞት ከረጢት ውስጥ የሚቀመጥ ቢሆንም አንዳንዴ ከጉበት ተመርቶ ወደ ሀሞት ከረጢት የሚያደርሰውን ቱቦ በመዝጋት ሀሞት መደበኛ ሥራውን እንዳይሰራ እንደሚያደርግ አብራርተዋል፡፡

በሀሞት ውስጥ የሚገኘው የኮሊስትሮል መጠን ከልክ ያለፈ ከሆነ እና ለረጅም ጊዜ ምግብ አለመመገብ ሀሞት ያለምንም እንቅስቃሴ በከረጢት ውስጥ ለረጅም ጊዜ መቆየቱ የሀሞት ጠጠር እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡
በተፈጥሮ የሀሞት ከረጢት የመኮማተርና የመዘርጋት ችግር ከገጠመው እዛ ውስጥ ያለው ሀሞት በሚገባ ሰለማይፈስ ይረጋል: በዚህም የሀሞት ጠጠር ይፈጠራል ሲሉ ዶ/ር ከንዙ ተናግረዋል፡፡
የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብል ለረጅም ጊዜ መውሰድ፣ በአጭር ጊዜ ከፍተኛ መጠን ያለው ክብደት መቀነስ ወይም መጨመር፣ ለረጅም ጊዜ ምግብ አለመመገብ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ እንዲሁም የስኳር ህመም ለሀሞት ጠጠር አጋላጭ ከሆኑ ምክንያቶች የሚመደቡ ናቸው፡፡
ህመሙ ሦስት አራተኛ የሚሆኑ ተጠቂዎች ላይ ምንም አይነት ምልክት የማያሳይ ሲሆን፤ በአንድ ሶስተኛው ተጠቂዎች ላይ ግን በቀኝ የሆድ ክፍል ይጀምርና ወደ ትክሻን ጀርባ የሚዛመት ከ1 እስከ 6 ሰዓት የሚቆይ የህመም ስሜት ሲኖረው፤ ህመሙ ከጨጓራ ህመም ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው ዶ/ር ከንዙ ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም የቀይ ደም ሴል አፈጣጠር ችግር፣ በጨጓራና የትንሹ አንጀት አካባቢ ቀዶ ጥገና የተደረገላቸው ሰዎች ከሌሎች በተለየ ሁኔታ በበሽታው የመጠቃት እድላቸው የሰፋ ነው፡፡
የአይን ቢጫ መሆን፣ ሽንት ወደ ቡናማ ቀለም መቀየር፣ ሰውነት የማሳከክ፣ የክብደት መቀነስ፣ ትኩሳት፣ ማስመለስ እና የምግብ ፍላጎት ማጣት የሀሞት ከረጢት በሽታ ምልክቶች ሊሆኑ ስለሚችሉ ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ በሽታው ሥር ሣይሰድ መታከም እንደሚገባ ዶ/ር ከንዙ መክረዋል፡፡
ፈጣንና ከመጠን በላይ የሆነ ክብደት መቀነስ ወይም መጨመርን መካላከል፣ ፈሳሽ በሚገባ መውሰድ፣ በእንክብል መልክ የሚወሰድ የወሊድ መቆጣጠሪያ አለመጠቀም፣ ለጨጓራ በሽታ የሚሰራ ቀዶ ጥገና ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ጤናማ የአኗኗርና የአመጋገብ ሥርዓትን በመከተል በሽታውን መከላከል ይቻላል፡፡
የሀሞት ጠጠሩን በጨረር ሰባብሮ ማውጣት፣ በቀዶ ህክምና ጠጠሩን ማስወገድ እና ወደ ሀሞት ከረጢት ውስጥ በካሜራ ታግዞ በኢንዶስኮፒ የሀሞት ጠጠሩን ለቅሞ በማውጣት በሽታውን አክሞ ማዳን እንደሚቻል ዶ/ር ከንዙ አብራርተዋል፡፡
በበረከት ጌታቸዉ