የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ አመራሮችና ሠራተኞች “ትውልድን በሥነ ምግባር፣ ተቋምን በአሠራር” በሚል መሪ ሀሳብ ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀንን አክብረዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ እንደገለጹት የሚዲያ ተቋማት መረጃን ለህዝብ ከማድረስ እና ከማዝናናት ባለፈ፣ ትውልድን በሥነ ምግባር ማነፅ፣ ማስተማርና ዜጎች ሀገር የሚረከቡ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው።
ለሁሉም ነገር መሰረቱ ትውልድ ነው ያሉት አቶ ካሳሁን፣ በትውልድ ላይ መስራት ሀገራችን የጀመረችውን የልማት ስራ ከግቡ ለማድረስ ያግዛል ነው ያሉት።
ዋና ስራ አስፈፃሚው አክለውም፣ “የሚዲያችንን መለያ የትውልድ ድምጽ ብለን ስንነሳ የተሻለ ትውልድ ለመፍጠር በማሰብ ነው፤ በተግባራችንም ትውልድ ላይ ሰርተን ማሳየት አለብን” ብለዋል።
ሙስና በጸሎት ሳይሆን በአሠራር የሚፈታ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በተቋም ደረጃ የተሻለ አሠራርን በመዘርጋት የሙስና ተጋላጭነትን ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑንም ዋና ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።
ትውልድ በጥሩ ስነ ምግባር የሚሰራውና የሚቀረጸው ቤተሰብ ውስጥ መሆኑን የተናገሩት አቶ ካሳሁን፣ ትምህርት ቤቶችና የሀይማኖት አባቶችም ትውልድን በሥነ ምግባር በመቅረጹ በኩል የጎላ ሚና አለባቸው አሉ፡፡
በተቋም ደረጃ የተጀመረውን ሙስናን የመከላከል ተግባር አጠናክረን እንቀጥላለን ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዉ ፣ ይንን ተግባር ሁሉም አካል የዕለት ተዕለት ተግባሩ አድርጎ እንዲንቀሳቀስም አሳስበዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ22ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ21ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የጸረ ሙስና ቀን በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ደግሞ ለ3ኛ ጊዜ ነው የተከበረው።
ዓለም አቀፍ የጸረ ሙስና ቀን በየዓመቱ ሕዳር 30 የሚከበር መሆኑ ይታወቃል።
በአስማረ መኮንን