ወርቃማ ሰኞ’ በሚል መጠሪያ ዘወትር ሰኞ ማለዳ የሚካሄደው የመማማሪያ መርሃ-ግብር ሁለተኛ ዓመት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት ተከብሯል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዕለቱን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት ሳምንታችንን አጨልመን አንጀምርም: የሳምንቱ መጀመሪያ ሰኞ ለእኛ ፍካትና ተስፋ የሚሰጠን ቀን ነው ብለዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት በከንቲባ አዳነች አቤቤ ሃሳብ አመንጭነትና መሪነት የተጀመረው መርሃ-ግብር ‘ጥቁር ሰኞ’ን ወደ ‘ወርቃማ ሰኞ’ የቀየረ ሆኗል።
የከንቲባ ጽ/ቤት፣ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ፣ የሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤትና የኮሙኒኬሽን ቢሮ አመራሮችና ሰራተኞች የሚሳተፉበት ‘ወርቃማ ሰኞ’ ሦስት ግቦችን (ከተማችንን የብልጽግና ተምሳሌት እናደርጋለን፣ ስንተባበር ለውጥ እናመጣለን እና እዚህ ያለነው ለማገልገል ነው) በማነገብ የተጀመረ ነው ብለዋል።
በሁለተኛ ዓመት ክብረ በዓል አከባበር ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ የሳምንቱን መጀመሪያ ሰኞን በፍካትና በተስፋ እንጂ አጨልመን አንጀምረውም ብለዋል።
ይህ ለራስ እድገት አስፈላጊ የሆነው መርሃ-ግብር በአሁኑ ሰዓት ወደ ሁሉም የከተማዋ መዋቅሮች እንደተስፋፋ እና እየተተገበረ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በዕለቱ ከከንቲባ አዳነች አቤቤ መልዕክት ባሻገር ‘ወርቃማ ሰኞ’ በሚል ርዕስ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቲያትርና ባህል አዳራሽ ተውኔት ያቀረበ ሲሆን የሁለተኛ ዓመት የመርሀ-ግብሩ ጉዞም ለታዳሚው በገለጻ መልክ መቅረቡን ከከንቲባ ጽ/ቤት ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል።