የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ኤግዚቢሽንና ባዛር በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ተከፍቷል ፡፡
የአዲስ አበባ ምክር ቤት “ሃገራዊ መግባባት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ የሚከበረው 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ ኤግዚቢሽንና ባዛር አዘጋጅቷል።
ላለፉት ሁለት ሳምንታት በወረዳ እና ክፍለ ከተማ ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች ቀኑን ሲያከብር የቆየው ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ብዝሃነትና አንድነት የሚንፀባረቅበት ኤግዚቢሽንና ባዛር በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ከፍቷል።
የተለያዩ የብሔሮ እና ብሔረሰቦች አልባሳት፣ እንዲሁም የተለያዩ ሸቀጦች በኢግዚብሽኑ የቀረቡ ሲሆን የደም ልገሳ መርሃ ግብርንም ይዟል።
መርሃግብሩን መርቀው የከፈቱት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር ከቅርብ አመታት ወዲህ የፌደራሊዝም ስርዓት ይበልጡኑ ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረገ መምጣቱን ገልፀዋል።
ብሔሮች እና ብሔረሰቦች ከስልጣን ባለቤትነት ባሻገር የሚታይ ተጠቃሚነትን ስለማግኘታቸውም ገልፀዋል ።
በመርሃ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ታድመዋል።
ኤግዚቢሽንና ባዛሩ እንዲሁም የደም ልገሳ መርሃ ግብሩ የሦስት ቀናት ቆይታ ይኖረዋል።
በመቅደስ ደምስ