በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ቦታው ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶችን ሲያዘጋጅ የነበረዉ ግለሰብ ተይዞ ክስ እንደተመሰረተበት ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ዳንኤል ሀይለጊዮርጊስ የተባለው ግለሰብ የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶችን እንደሚያዘጋጅ ከህብረተሰቡ የተሰጠውን ጥቆማ መነሻ በማድረግ በተደረገ የክትትልና የመረጃ ሥራ በተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት ስም የተዘጋጁ ሀሰተኛ ሰነዶች ተገኝተዋል፡፡

በኦሮሚያ ንግድ ቢሮ፣ የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት የሚገልፅ ማህተም፣ በሲ.ፒ.ዩ የቢዝነስ እና ቴክኖሎጂ ኢንፎርሜሽን ኮሌጅ ማስረጃ ፣ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ፣የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ሰነድ፣የንግድ ስራ ፍቃድ፣ የወሳኝ ኩነት ሰነዶችና በልዩ ልዩ ተቋማት ስም የተዘጋጁ ደብዳቤዎች ተገኝተዋል፡፡
ሀሰተኛ ሰነዶችን ለማዘጋጀት የሚገለገልባቸው 3 ፕሪንተሮች፣ላፕቶፕ እና የተለያየ አይነት ያላቸው ወረቀቶች በኤግዚቢትነት የተያዙ ሲሆን በግለሰቡ ላይ ተገቢውን ምርመራ በማጣራት ክስ መመስረቱን የፒያሳ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ አስታውቋል፡፡
ሀሰተኛ ሰነድ አዘጋጅቶ በመሸጥና ገዝቶ በመጠቀም በአቋራጭ ጥቅም ለማግኘት ጥረት የሚያደርጉ አካላትን ህብረተሰቡ ሲመለከት ለፀጥታ አካላት በማሳወቅ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው እያደረገ ያለውን አስተዋፅኦ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ መልእክቱን አስተላልፏዋል።