AMN – ህዳር 16/2018 ዓ.ም
ውቧ ሲንጋፖር በቆዳ ስፋት ከአዲስ አበባ የማትበልጥ፣ በመጠንም ትንሽ ሀገር ናት፡፡ ይሁንና በእድገቷ ጠንካራ፣ ዘመናዊና ተመራጭ ከሚባሉ የዓለማችን ቀዳሚ ሀገራት ተርታ ትመደባለች፡፡
ሲንጋፖር ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት እኤአ በ1930ዎቹ በፍጥነት እየጨመረ በመጣው የህዝብ ቁጥሯ ምክንያት የመሰረተ ልማትና የመኖሪያ ቤቶች እጥረት አጋጥሟት ነበር፡፡
የሲንጋፖር ሪፐብሊክ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ግን የከተማ እድሳት ጉዳይ በብሄራዊ ማሻሻያ ፖሊሲ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል፡፡

የሲንጋፖር የህዝብ ቁጥር 6.1 ሚሊዮን የሚደርስ ሲሆን፣ የሀገሪቱ ሁለንተናዊ ልማት በአረንጓዴ ልማት የታጀበ በመሆኑ ለቱሪስቶች መዳረሻነት ተመራጭ ሀገር እንድትሆን አስችሏታል፡፡
ሲንጋርፖር ጽዱ ሀገር ስትሆን፣ በተለይም ቆሻሻን የሚሰበስቡበትና መልሶ ጥቅም ላይ የሚያውሉበት መንገድ ለበርካታ ሀገራት ምሳሌ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡
በሲንጋፖር ቆሻሻ የሚሰበሰበው በሮቦቶች አማካኝነት ነው፡፡
ሲንጋፖራዊያን የተፈጥሮ ፀጋን በኪነ ህንፃና በቴክኖሎጂ በማዳበር በኩል የተካኑ ሲሆኑ፣በተለይም ዘመናዊ ህንፃዎችን በመገንባት በዓለም ትንሿ ግን ፈርጣማ ኢኮኖሚ የገነባች ሀገር አድርጓታል፡፡
የሲንጋፖር የባህር ዳርቻዎች አስደናቂና ውብ ተደርገው የተሰሩ ሲሆን፣ በአረንጓዴ ልማት ላይ ጠንካራ ህግ አላት፡፡
በመሆኑም በሲንጋፖር ተክሎችን ማበላሸትና ዛፎችን መቁረጥ 50 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ያስቀጣል፡፡

ሲንጋፖር ሙስና እና የወንጀል ምጣኔዋም ከዓለም ሀገራት ትንሹ የሚባል ሲሆን፣ ይህ የሆነውም በህዝቡ ላይ በተሰራው የግንዛቤ ስራና በሀገሪቱ ህግ መሰረት ሙስና ሲሰራ የተገኘ ሰው የሞት ቅጣት ስለሚጠብቀው ነው፡፡
የሲንጋፖር ፓስፖርት ከሀያላኑ አሜሪካና ከሌሎችም ሀገራት ጠንካራ የሚባል ሲሆን፣ ሁሉንም የዓለም ሀገራት ያለምንም ቪዛ ማስኬድ ያስችላል፡፡
ሲንጋፖር ከሁሉም ሀገራት ጋር መልካምና ጠንካራ የሚባል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላት ሀገር ናት፡፡
የሲንጋፖርና የኢትዮጵያ ግንኙነት የሚጀምረው የሲንጋፖር መስራች አባት የሚባሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሊኪዋንዩ በፈረንጆች 1964 ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ነበር፡፡
የጉብኝታቸው ምክንያትም ሲነጋፖር በቅኝ ግዛት ስለነበረች፣ ነፃነቷን ለማግኘት የአፍሪካ ሀገራትን ለማግባባት ያለመ ነበር፡፡

በዚያን አመት በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ነፃነታቸውን ለመቀዳጀት ጫፍ ላይ የነበሩበት ወቅት በመሆኑና ተመሳሳይ የፀረ ቅኝ ግዛት አቋም በመኖሩ ለሲንጋፖር አፍሪካ ተመራጭ አህጉር ነበረች፡፡
ይህም ኢትዮጵያ ከሲንጋፖር ጋር ያላት ግንኙነት አሁን የተጀመረ ሳይሆን፣ የቆየና የጠበቀ ትስስር እንዳለው ያመላክታል፡፡
ሲንጋፖራዊያን ላለፉት 60 እና ከዚያ በላይ አመታት እጅግ ዝቅተኛ ከሆነ የእድገት ደረጃ ተነስተው አስደናቂ ማህበረ ኢኮኖሚያዊ እድገት በማስመዝገብ ከዓለም የበለፀጉ ሀገራት ተርታ መሰለፍ የቻሉ ህዝቦች ናቸው፡፡
የሲንጋፖራዊያን ያለፉት መንግስታት ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ ለሰብአዊ ልማትና ለኢኮኖሚያቸው እድገት የነበራቸው ወሳኝ ሚና፣ ለእድገትና ለብልፅግናቸው ቀጣይነት የማይተካ ድርሻ አበርክቷል፡፡
ኢትዮጵያና ሲንጋፖር በአረንጓዴ ልማት፣ በትምህርት፣ በቀልጣፋ የህዝብ አገልግሎት፣ በከተማ ልማት ስራዎች፣ በቴክኖሎጂ፣ በሎጂስቲክስና ትራንስፖርት እንዲሁም በቱሪዝም ዘርፎች በትብብር እየሰሩ የሚገኙ ሀገራት ናቸው፡፡
በንጉሱ በቃሉ