9ኛው የኦዳ አዋርድ የሽልማት እና የእውቅና መርሃ ግብር የፊታችን ህዳር 30 ቀን 2018 በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬሽን ማዕከል እንደሚካሄድ በሻቱ ቶለማርያም መልቲሚዲያ አስታወቀ።
የሽልማት መርሃ ግብሩ ከቀደምት ዓመታት ውድድሮችም ለየት ባለ መልኩ ትኩረቱን ሙሉ በሙሉ በሙዚቃው ዘርፉ በማድረግ የሽልማት ስነ ስርዓት እንደሚያካሄድም ተገልጿል።
ህዳር 30 ቀን 2018 በሚካሄደው የኦዳ አዋርድ ላይ ለመታደም ከ12 የአፍሪካ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ባህላቸውን የሚያንጸባርቁ በመሆናቸው ሽልማቱ ለኪነ ጥበቡ የልምድ ልውውጥ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ተገልጿል።
የውድድር ሂደቱን በሚመለከት ከዚህ ቀደም 70 ነጥብ በዳኝነት እንዲሁም ቀሪውን 30 ነጥብ ለዚህ ተብሎ በተዘጋጀው አጭር የኤስ ኤም ኤስ ቁጥር ላይ ሕዝብ ድምጽ ይሰጥ እንደነበር ተገልጿል።
በዘንድሮው መርሀ ግብር ላይ እጩ ተሸላሚ የሚሆኑት ሙሉ ለሙሉ ከአድናቂዎቻቸው በሚያገኙት ድምጽ መሆኑን እና ለዚሁ ዝግጅት በሚያገለግለው የኦዳ አዋርድ ድረ-ገጽ እንደሚሆን የኦዳ አዋርድ አዘጋጅ ጋዜጠኛ በሻቱ ቶሎማርያም ገልጻለች።
1. የህይወት ዘመን ተሸላሚ
2.የአመቱ ምርጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ አርቲስት
3. የአመቱ ምርጥ ቪዲዮ ክሊፕ
4. የአመቱ ምርጥ ሴት ድምፃዊት
5.የአመቱ ምርጥ ወንድ ድምፆዊ
6. የአመቱ ምርጥ ሀገርኛ ዘፋኝ
የ9 ኛው ኦዳ አዋርድ ከሀገር ውስጥ የሙዚቃ ስራዎች ለሽልማት እጩዎችን የሚያቀርብበት 6 ዘርፎች ናቸው።
ከአፍሪካ ሃገራት በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ በ “AFRICAN SUPER STAR” ዘርፍ ላይ ተሸላሚ ለመሆን የሚሳተፉት 12 የአፍሪካ ሃገራት ሩዋንዳ፣ማሊ፣ምሮኮ፣አንጎላ፣ማዳጋስካር፣ኬንያ፣ጅብቲ፣ ሲሼልስ፣ጋና፣ቶጎ፣ደቡብ ሱዳን እና ኡጋንዳ መሆናቸውን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተገልጿል።
በብሩክታዊት ጥላሁን