ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት ዛሬ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የ2017 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም የእውቅና እና የምስጋና መርሃ ግብር ላይ ተገኝተናል ብለዋል፡፡
የለውጡ መንግሥት በግብርና ዘርፍ ለቡና ልማት በሰጠው ልዩ ትኩረትና በዘርፉ ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ርብርብ ባለፉት ዓመታት አስደማሚ ለውጦችን አስመዝግበናል።
ምርታማነት በእጅጉ ጨምሯል፤ ቡና አምራች አርሶ አደሮቻችንም በቡና ልማት ተስፋ ከመቁረጥ ወጥተው ዛሬ ላይ ሚሊየነር እየሆኑ ይገኛሉ።
በ2017 በጀት ዓመት በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ 470 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 2 ነጥብ 65 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝተናል፡፡ ይህ ውጤት በምርት መጠንም ሆነ በገቢ አዲስ ታሪክ የጻፍንበት ነው ብለዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት 600 ሺህ ቶን ቡና በመላክ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት የያዝነውን ግብ ለማሳካት ጥራትን ማሻሻልና ቡናን እሴት በመጨመር ወደ ውጭ መላክ ትኩረቶቻችን ናቸው።
ሀገራችንን በዓለም ግንባር ቀደም የቡና፣ የሻይና የቅምማ ቅመም አምራች ለማድረግ በፍጥነትና በጥራት መርህ የጋራ ጥረታችንን አጠናክረን ማስቀጠል አለብን ሲሉ ገልጸዋል፡፡