ህገ መንግስቱ ከአሁን ቀደም በብሄሮችና ብሄረሰቦች ላይ ሲደርስ የነበረዉን ጭቆና በማስቀረት ለኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ እና ማንነት እዉቅና መስጠቱ ተገለጸ፡፡
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ብዙአየሁ ደገፋ (ዶ/ር) ከኤ ኤም ኤን ፕላስ ጋር በነበራቸዉ ቆይታ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራዊያዊ ህገ መንግሥት የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን እኩል ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ሰነድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሕገ መንግስቱ ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም የጸደቀዉ የማንነት ጥያቄን ለመመለስ መሆኑንም ብዙአየሁ ደገፋ (ዶ/ር)ገልጸዋል፡፡
ህገ መንግስቱ ከጸደቀ በኋላ የማንነት ጥያቄዎችን በመመለስ ረገድ ትልቅ ድርሻ አበርክቷል፡፡
ህገ መንግስቱ ለህዝቦች ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ እዉቅና ከመስጠቱም በላይ፣ ሁሉም ዜጋ የፈለገዉን ሃይማኖት የመከተል መብት አግኝቷል ብለዋል፡፡
ፌዴራላዊ ህገ መንግስቱ ከአሁን ቀደም በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ላይ ሲደርስ የነበረዉን ዘርፈ ብዙ ጭቆና በማስቀረት በህገ መንግስቱ መሰረት ራሳቸውን በራሳቸዉ እንዲያስተዳድሩ ስልጣን የሰጠ መሆኑንም የፖለቲካ ምሁሩ ብዙአየሁ ደገፋ (ዶ/ር) ለኤ ኤም ኤን ፕላስ ተናግረዋል፡፡
የለዉጡ መንግስት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በሃገራዊ ጉዳዮች ላይ በእኩልነት እንዲናገሩና ሃሳባቸዉን እንዲገልጹ ማድረጉንም ጨምረዉ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ዉስጥ በርካታ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ ሃይማኖቶች እና ማንነቶች መኖራቸዉን በመገንዘብ በመከባበርና በመፋቀር እንዲሁም ህብረብሄራዊ አንድነትን በማረጋገጥ ለሃገራዊ ሰላምና ልማት በጋራ መስራት እንደሚገባም ምሁሩ ጠቁመዋል፡፡
በሹሚ በዳሶ