ቼልሲ ከባርሰሎና ፡-የእለቱ ተጠባቂ ጨዋታ

You are currently viewing ቼልሲ ከባርሰሎና ፡-የእለቱ ተጠባቂ ጨዋታ

AMN-ህዳር 16/2018 ዓ.ም

የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የሊግ ምዕራፍ አምስተኛ ጨዋታዎች ዛሬ ይጀምራሉ፡፡ ዛሬ በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች ዘጠኝ ጨዋታዎች ይከናወናሉ፡፡

ምሽት 5 ሰዓት ላይ ቼልሲ በስታምፎርድ ብሪጅ ባርሰሎናን የሚያስተናግድበት ጨዋታ የተለየ ትኩረት አግኝቷል፡፡ ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም ከአእምሮ የማይጠፉ በርካታ ጨዋታዎችን አከናውነዋል፡፡

2009 ላይ በስታምፎርድ ብሪጅ 1ለ1 ሲለያዩ ማይክል ባላክ እና ዲዲዬር ድሮግባ በዳኛ ተበድለናል በሚል ያሳዩት ባህሪ በብዙዎች ይታወሳል፡፡

በ2012 ደግሞ ቼልሲ በሮቤርቶ ዲማቲዮ እየተመራ በካምፕኑ 2ለ2 ተለያይቶ በአጠቃላይ ውጤት 3ለ2 በማሸነፍ ለፍፃሜ የደረሰበት አጋጣሚም የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ደጋፊዎች የሚዘክሩት ነው፡፡

ሁለቱ ክለቦች በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ በአጠቃላይ 14 ጊዜ ተፋልመዋል የትኛውም ክለብ የበላይነቱን አልወሰደም፡፡ አራት አራት ጊዜ ሲሸናነፉ ስድስቱን ጨዋታ በአቻ አጠናቀዋል፡፡

ቼልሲ እና ባርሰሎና በዘንድሮው ውድድር አራት ጨዋታ አከናውነው በተመሳሳይ ሰባት ነጥብ ይዘዋል፡፡ በደረጃ ሰንጠረዡም 11 እና 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡

በዛሬ ጨዋታ በቼልሲ በኩል አዲስ የጉዳት ዜና የለም። ኮል ፓልመር ወደ ልምምድ ቢመለስም በዛሬው ጨዋታ አይሳተፍም።

በባርሰሎና በኩል ህመም ላይ ይገኝ የነበረው ማርከስ ራሽፎርድ የስብስቡ አካል ሆኖ ወደ ለንደን ተጉዟል።

ሀንሲ ፍሊክ ራፊንሃም ስለተመለሰላቸው በአጥቂ ክፍል ማንን እንደሚጠቀሙ ለማየት ያጓጓል።

በሌሎች ጨዋታዎች ማንችስተር ሲቲ በኢትሃድ ስታዲየም ባየር ሊቨርኩሰንን ያስተናግዳል፡፡ ሲቲ ከአራት ጨዋታ 10 ነጥብ ይዞ 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

ኦሊምፒክ ማርሴይ ከኒውካስትል ዩናይትድ ፣ ናፖሊ ከካራባግ ፣ ስላቪያ ፕራግ ከአትሌቲክ ቢልባኦ ፣ ቦሩሲያ ዶርትመንድ ከቪያሪያል እንዲሁም ቦዶ ከጁቬንቱስ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎችም ዛሬ ምሽት ይጠበቃሉ፡፡

ሁሉም ጨዋታዎች ምሽት 5 ሰዓት ላይ ይጀምራሉ፡፡

ከእነዚህ ጨዋታዎች ቀደም ብሎ አያክስ ከቤኔፊካ እንዲሁም ጋላታሳራይ ከሴንት ጂልዋስ ምሽት 2፡45 ላይ ጨዋታቸውን ይጀምራሉ፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review